Thursday, 23 January 2014

አንድነት – እነ አንዷለም አራጌ ነገ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ም/ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ አንዷለም አራጌ፣ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ናትናኤል መኮንን እንዲሁም አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ነገ ጥር 16 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚቀርቡ ታወቀ፡፡
andu_udj
ከዚህ በፊት የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በማቀድ በሚል የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ወጣቱ ፖለቲከኛ እነአንዷለም አራጌና ሌሎች ፍርዱን ባለመቀበል ለታሪክና ለሕዝብ ፍርድ ለመተው ጉዳዩን ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት ወስደውታል፡፡ ከቅርብ ቤተሰቦቻቸው ለማረጋገጥ እንደቻልነው ሰበር ሰሚ ግራና ቀኙን በመመልከት ሚዛናዊ ፍርድ ይሰጣል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ገዢው ፓርቲ “ሽብርተኛ“ ብሎ ያሰራቸው ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎች የዓመቱ ምርጥ ሰው ተብለው እየተመረጡና የተለያዩ የክብር ሽልማት እንዳሸነፉ በተለያዩ ሚዲያዎች መዘገቡ ይታወቃል፡፡
ነገ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት የፍርድ ሂደቱን መከታተልና ለእስረኞችም አጋርነቱን መግለጽ ይችላል።

የአንድነት ፓርቲ ወጣት አመራሮች ከኢሳት ጋር ያደረጉት ጠንካራ ቃለ ምልልስ – ክፍል 1

January 23rd, 2014      
የአንድነት ፓርቲ ወጣት አመራር አባክላት ም/ፕሬዘዳንቱ አቶኢ በላይ በፍቃዱና የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊዉ አቶ ሃብታሙ አያለው ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልሶች ጠንካራ ጥያቄዎች ቀርበዉላቸዋል። ቢሳት የቀረቡት ጥያቄዎች ተመሳሳይነት ያላቸው ከመሆናቸውም በተጨማሪ የአንድነትን ፓርቲ አመራሮችን ተስፋ ለማስቆረጥና ኮርነር ለማድረግ ሆን ተብሎ ተመርጦ የተዘጋጁ ጥያቄዎች እንደሆኑ ብዙዎች እየተናገሩ ነዉ።
ከኢሳት የተነሱ ጥያቄዎች ይዘት ተመሳሳይነት መኖራቸው የኢሳትን ገለልተኝነት የማይንጸባርቁ እንደሆኑ ብዙዎች ቢናገሩም፣ የአመራር አባላቱን በሳል መልስ ሳያደንቁ አላለፉም።
መደመጥ ያለበት አቶ በላይ በፍቃዱና አቶ ሃብታሙ አያሌው፣ ያደረጉትን ክፍል 1 ቃለ ምልልስ ለማዳመጥ እዚህ ይጫኑ

ሀገርን ቆርሶ በመስጥት በስልጣን መቆየት አይቻልም

January 22, 2014
ብሌን ንጉሴ (ከጀርመን)
አንባገነኑ የኢትዮጵያ  መንግስት የሀገሪቱ እና የህዝቦችን ጥቅም ያላአንዳች ይሉኝታ ለባእዳን አሳልፎ ሲሰጥ እነሆ 22 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ መቼም እያንዳንዱን የወያኔ ጉድ መዘርዘር አንባቢን ማሰልቸት ቢሆንም ከሰሞኑ ደግሞ የአቶ መለስን ራዕይ ከማስፈጸም ውጭ የራሱ የሆነ አመክንዮ የሌለው ጠ/ር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በአያት ቅድመ አያቶቻችን አጥንት ተከብሮ የቆየውን የሀገራችን ለም መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት ሙሉ ፈቃደኝነቱን አሳይቶ ተፈራርሞ ተመልሷል፡፡ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ በምንም ጉዳይ ላይ አማክሮት አያውቅም፡፡ሀገሪቱን ለማስተዳደር መጀመሪያም ውክልና ስላልተሰጣቸው ምንም ጎጅ ውሳኔ በሀገር ላይ ሲያስተላልፉ ህዝቡ ምን ይለናል ብሎ የሚያስብ ህሌና የላቸውም፡፡ባለፉት 2 ወራት በመቶ ሺ በላይ ኢትዮጵያውን በአሰቃቂ ሁኔታ ከሳውዲ አረቢያ ሲባረሩ በቦታው በመገኘት ወገናቸውን ለመርዳት ያልሞከሩ ባናዳዎች ዛሬ ሱዳን ድረስ በመሄድ ዳር ድንበራችን ለሱዳን ለመስጠት ሽር  ጉዱን ተያይዘውታል፡፡ወያኔ ተደብቆ የሚቀር እየመሰለው ሀገራዊ ክህደት ሲፈጽም  ከህዝቡ የሚመጣውን ተቃውሞ ለማርገብ ምንም የማይቆፍረው ድንጋይ የለውም፡፡Ethiopian government to hand over land to Sudan
የአሰብን ወደብ ለኤርትራ አሳልፎ በሰጠበት ወቅት የክህደት አባት የሆነው ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ለአንድ ሀገር እድገት ወደብ ምንም ሚና አይጫወትም ፡፡በገንዘባችን አማርጠን  ወደብ መከራየት እንችላለን በማለት አያናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ አይነቱን የደንቆሮ ፕሮፖጋንዳ እንዳላዘኑ ህይወታቸው ቢያልፍም ዛሬም ድረስ አሰብ ከኢትዮጵያውያን ህሌና ሳይፋቅ አብሮን ተቀምጡዋል፡፡  ጦርነት ላለመግባት አሰብን አሳልፎ የሰጠው ወያኔ ውሎ አድሮ ሸአቢያ  ባድመ ላይ ወረራ ሲፈጽም የማይቀረውን ጦርነት ተገባ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን ትንቀሳቅሰው መተኪያ  የሌለው ህይወታቸውን ከፍለው ባድሜን በቁጥጥር ስል ቢያውሉም የህዝቡን ይሁንታ ሳያገኝ በደም የተገዛውን መሬት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው በሄግ  አለም ፍርድ ቤት ለትግል አጋራቸው  አስረክበው ተመለሱ፡፡ ድንበሩን ማስረከባቸው ሳያንስ ደሙን አፍሶ አጥንቱን ከስክሶ  ድል የተቀዳጀውን ወታደር ፤ ጡዋሪ ቀባሪ ልጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ወላጆችን እና ባሉዋን በሞት ተነጥቃ በሀዘን የተጎሳቆለች የሙዋች ወታደር ባለቤትን ሰብስቦ ባድሜ ለኢትዮጵያ ተፈረደልን ወጥታችሁ በሰላማዊ ሰልፍ  ደስታችሁን ግለጹ በማለት የሀሰት ከበሮ እያስደለቀ ህዝቡን አታለዋል፡፡ዛሬም በሱዳን ድንበር ዙሪያ እውነታውን በመደበቅ  እያታለሉት ይገኛሉ፡፡
ወያኔ መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስን በ30 ብር አሳልፎ የሸጠውን ይሁዳን እና ለምስር ንፍሮ ብሎ ብኩርናውን የሸጠውን ኢሳውን ይመስል፡፡ ይሁዳ ፈጣሪውን ለገንዘብ አሳልፎ ቢሰጥም በገንዘቡ እንኩዋን ሳይጠቀምበት ህይወቱ እንዳለፈው ሁሉ ወያኔም ምንም ያክል በስልጣን ለመቆየት ሀገርን እየቆረጠ ቢሰጥም በክህደት የሚገኝ ስልጣን እንደይሁዳ ሞትን ይዞላቸው እየመጣ ነው፡፡ ይሁዳ በደም የገዛውን መሬት አኪልዳማ ብሎ እንደሰየመው ወያኔም በስልጣን የሚቆይበትን ጊዜ አኪልዳማ ነው፡፡
ለሱዳን መሬትን ቆርሶ በመስጠት በስልጣን ለመቆየት የሚደረግ የቀቢጸ-ተስፋ ተግባራት በምንም መልኩ ህዝባዊ ጥያቄን አዳፍኖ ማስቀረት አይችልም፡፡ወያኔ ህዝቡን ሳያውቀው አንድ ቀን እንኩዋን በድፍረት ክህዝብ ሳይወያይ ሌባ እና ፖሊስ ድብብቆሽ በመጫወት ወደ ግብአተመሬቱ እየተቃረበ ይገኛል፡፡ሁሉንም የመጫወቻ ካርዶች ወደመሬት ጥሎ ፋርዳ የወጣው አንባገነን የዘር ጥላቻውንም፤የእምነት ጥላቻ ዘመቻውን በግልጽ እና በስውር ቢያካሂድም ከልዩነት ይልቅ  አንድነቱ እና ወገናዊነቱ እያመዘነ የመጣውን የህዝቦችን ህብረት መቋቋም ተስኖታል፡፡ለዚህም እንዳበደ ውሻ ያገኘውን ሁሉ እየነከሰ ይገኛል፡፡መጻፍ ፤መደራጀት ሽብርተኛ እያሉ  ዜጎችን በጅምላ በማሰር በመግደል የህዝብን አመጽ ማስቆም አይቻልም፡፡ሀገርን እየቆረሱ ለባእዳን በመስጠት በስልጣን መቆየት አይቻል፡፡በስልጣን ለመቆየት የሚያስችለው የማሸነፊያ ካርድ በሱዳን እጅ ሳይሆን በተባበሩት የኢትዮጵያ ህዝቡች እጅ ነው ሚገኘው፡፡

ከቃሊቲና ቂሊንጦ እስር ቤቶች በላይ የሚያንጸባርቁ ከዋክብት (ዳዊት ከበደ ወየሳ፣ አትላንታ)

January 23, 2014

(ይህ ጽሁፍ የርዕዮት አለሙ የልደት በአል በአዲስ አበባ በተከበረበት ወቅት; ከውጭ አገር ንግግር እንዳደርግ በተጋበዝኩበት ወቅት… የስራ ባልደረቦቼን እስክንድር, ውብሸት እና ርዕዮትን በማሰብ የተዘጋጀ ነው)
ይህ ሳምንት የታላቁ ማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት በአል በመላ አሜሪካ የሚከበርበት ነው:: በአሜሪካ ከክርስቶስ ልደት ቀጥሎ ስራ እና ትምህርት ቤት ተዘግቶ ልደቱ የሚከበርለት አንድ ሰው ቢኖር ማርቲን ሉተር ኪንግ ብቻ መሆኑን ልብ ይበሉ:: የማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት በአል በሚከበርበት ወቅት በህይወት ዘመኑ ለጥቁር ህዝብ ነጻነት ያደረገው አስተዋፅኦ ይታወሳል:: በህይወት በነበረበት ወቅት ለሰው ልጅ እኩልነት ተሟግቷል; የነጻነት ቀንዲልን ለኩሷል:: ሆኖም እኩልነት እና ነጻነትን ሳያጣጥም በበርሚንግሃም እስር ቤት ተጥሎ ፍዳውን እንዲቆጥር ተፈርዶበት ነበር:: በመጨረሻም የሰውን ልጅ ክብር እና ነጻነት በማይደግፉ ሰዎች ህይወቱ ማለፉ ይታወቃል – መልካም ስራዎቹ ግን አላለፉም::Reeyot Alemu, the 31 year-2012 Courage in Journalism Award winner.
ዛሬም በአገራችን ስለፍትህ, ስለነጻነት የሰበኩና የደሰኮሩ; የጻፉና የመሰከሩ… ለሃቅ ቆመው፣ ግፍ የተሰራባቸው፣ ከአገር የተሰደዱና የወጡ፤ በግፍ ሰንሰለት ለጨለማ እስር የተዳረጉ ወገኖቻችን ብዙ ናቸው:: እስክንድር፣ ውብሸት፣ ርእዮት፣ አንዷለም እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በሰብአዊነት መሰረት ላይ ስላነጹ እና ሃሳባቸውን በነጻነት ስለገለጹ መጨረሻቸው እስር እና እንግልት ሆኗል::
እንደ እውነቱ ከሆነ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ… ብሎም የህዝብ ልሳን ሆኖ ለህዝብ የቤዛነት ዋጋ መክፈል የሚያስከብር እንጂ የሚያሳስር አልነበረም:: በመሆኑም ለነጻ ፕሬስ መክፈል የሚገባቸውን ዋጋ ከመጠን አሳልፈው የከፈሉት፤ ርዕዮት አለሙ፣ እስክንድር ነጋ እና ውብሸት ታዬ… ሶስቱም ከአገራቸው አልፈው በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተዋል:: በአለም አቀፍ ደረጃም በልዩ ልዩ አለም አቀፍ የጋዜጠኞች ማህበራትና ተቅውውማት ለሽልማት ታጭተው አሸናፊ ሆነዋል::
የ’ነዚህ የስራ ባልደረቦቼ ብዕር… ህዝብን ሳይሆን የተወሰኑ ወገኖችን አሸብሮ ሊሆን ይችላል:: እነርዕዮት አለሙ በዚህ አይነት ሰበብ አስባብ በቃሊቲ እና በቂሊንጦ እስር ቤት ታግተው፤ ነጻነታቸውን አጥተውና ህክምና ተነፍገው ይታሰሩ እንጂ፤  ለእውነት የቆሙ ወገኖች ግን ለመልካም ስራቸው ሽልማትን አልነፈጓቸውም::
ማርቲን ሉተር ኪንግ በበርሚንግሃም እስር ቤት ታስሮ ቢማቅቅም የአሜሪካም ሆነ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አልዘነጋውም:: ቆይቶም ቢሆን የአለም አቀፉ ኖቤል ተሸላሚ እስከመሆን ደርሷል:: ዛሬ በእስር ላይ የሚገኙት የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች የኖቤል ተሸላሚ ባይሆኑም አለም ግን አልረሳቸውም:: ከታሰሩበት የጨለማ ወህኒ ቤት ጀርባ፤ ከብረት ፍርግርግ እና ከግድግዳዎቹ ባሻገር በመቶዎች፣ በሺዎች እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን ጋዜጠኞች በመልካም ስራቸው ያስታውሷቸዋል; ይዘክሯቸዋል:: ስለሆነም የጻድቃን ሞት፤ የሰማዕትነት ጽድቅ ተደርጎ እንደሚቆጠረው ሁሉ… የነ እስክንድር፣ ውብሸትና ርዕዮት እስር፤ ከቶውኑ ዋጋ ቢስ እና ፍሬ አልባ ሊሆን አይችልም::
ኢትዮጵያ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት በፕሬስ ጉዳይ ተደጋጋሚ የሆነ እስር ደርሶብኛል:: በ’ነዚህ የእስር እና እንግልት ጊዜያት ግን… ከጨለማው እስር ቤት ማዶ ለምን እንደታሰርኩ የሚረዱ ሺዎች በመኖራቸው ሁልጊዜ እጽናና ነበር:: በተደጋጋሚ እስር ቤት እየመጣ የሚጠይቀኝ እና የዋስ መብቴን አስጠብቆ ከእስር እንድወጣ ያደርገኝ የነበረው ወላጅ አባቴ፤ “የታሰርከው ሰርቀህ ወይም ሌላ ወንጀል ሰርተህ ሳይሆን፤ እውነትን ስለተናገርክ ነው:: ስለዚህ አንገትህን ቀና ልታደርግ እንጂ ልትሸማቀቅ አይገባህም::” የሚል አጽናኝ ቃል ሁሌ ይነግረኝ ነበር:: ዛሬ አባቴ በህይወት የለም:: ቃሉ እና ምክሩ ግን አብሮኝ አለ:: በእስር ላይ ለሚገኙ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ “አንገታችሁን ቀና አድርጉ!” የሚለውን መልዕክት አጋራቸዋለሁ::
ዛሬ በጋዜጠኞቻችን ላይ የተለያዩ ክሶች ተመስርቶባቸው መታሰራቸው ሳያንስ; ከታሰሩም በኋላ በሃሰት ሊወነጅሏቸው የሚሹ ብዙ ግራ ዘመም ሰዎች መኖራቸውን ታዝበናል:: በአሜሪካ ከፍተኛ የአየር ሽፋን አግኝቶ ዲሞክራቶችን በመሳደብ የሚታወቀው ራሽ ሊምቦ የተባለ ጋዜጠኛ በቅርቡ ኔልሰን ማንዴላ በሞት ሲለዩ… “ብታምኑም ባታምኑም ኔልሰን ማንዴላ አሸባሪ ነበሩ::” ብሎ ሰፊ ሙግት ፈጥሮ ነበር:: ይህ አባባሉ ለኛ እና ለሌሎች አፍሪቃውያን ሊገርመን ይችል ይሆናል:: ነገር ግን የራሳቸው አመዛዛኝ ህሊና ያልፈጠረባቸውና ይህን ሰው በጭፍን የሚከተሉት ሰዎች “አዎ ማንዴላ አሸባሪ ነበሩ” ብለው ቢሉ ሊገርመን አይገባም::
ዛሬም ባገራችን በተመሳሳይ መልኩ የነርዕዮት አለሙን መልካም ስም ጥላሸት ለመቀባት እላይ ታች የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ… እኛ ግን እንላለን:: “ወንጀል አልሰራችሁምና አንገታችሁን ቀና አድርጉ!” ስማችሁ ከቃሊቲና ከቂሊንጦ እስር ቤቶች በላይ፤ በጠራው ሰማይ ላይ ያንጸባርቃል፤ ቃለ ሃቃቹህ በአየር ናኝቶ… ኢትዮጵያዊያን ባሉበት ሁሉ በመላው አለም ላይ ተሰራጭቷል::
የማርቲን ሉተር ኪንግ ልደት ሲከበር መልካም ስራዎቹ እንደሚወደሱ ሁሉ፤ ዛሬም ሆነ ወደፊት የነርእዮት አለሙ ልደት ሲከበር መልካም ስራዎቻቸው በተደጋጋሚ ይነሳሉ ይዘከራሉ:: ዛሬ ማንዴላን አሸባሪ ብለው የሚከሱ ሰዎች እንደመኖራቸው መጠን; በተመሳሳይ መልኩ ለነርእዮት አለሙ ተመሳሳይ ስም የሰጡና ያሰጡ… ለመስጠት እና ለማሰጠት የሚጥሩ ሰዎች አሉ:: እኛ ግን የተለኮሱ ሻማዎች ይዘን ልደት ስናከብር; የብርሃናችን  ጮራ፤ ሌሎች የፈጠሩትን የጨለማ ድባብ ሰንጥቆ… አንዳች ብርሃን እንደሚፈነጥቅላቸው በማመን ነው:: ዛሬ የርዕዮት አለሙን የልደት ቀን ስናከብር፤ ያለፍትህ የታሰሩትን ፍትህ የሚፈልጉትን፤ ነጻነት የተጠሙትን ነፍሶች በማሰብ ጭምር ነው::