Sunday, 2 March 2014

እስክንደር የጻፈው ለነጻነት ነው፤ የሞራል ድፍረት ያለው ነው – ጆን ኬሪ


March 1st, 2014                  
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ሽብርተኛ ነህ በሚል መስረት የሌለዉ ክስ ተከሶ የ18 አመት እስራት ፣ በፖለቲካ ዉሳኔ እንደተፈረደበት ይታወቃል። የአሜሪካው የዊጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይሄን ይቃወማሉ። ጋዜጠኛ እስክንደር ነጋን፣ ለነጻነቱ የጻፈ ሲሉ፣ ከሌሎች አንጋፋ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እኩል አስቀምተዉታል።1394241_527514827333456_269824761_n
የጆን ኬሪ ይፋዊ ዘለፋ፣ የጋዜጠኛ እስክንደር ሆነ የሌሎች በርካታ ጋዜጠኞችና የሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች መታሰር፣ ኢሕአዴግ በአገሩ ካሉ ዜጎቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከበርካታ የአለም አቀፍ ማህበረሰብና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጋር እንዲጋጭ እያደረገዉ እንዳለ የሚያመላክት ነው።
አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስት ዋና ደጋፊ እንደሆነች ይታወቃል። በርካታ የአገዛዙ ቱባ ቱባ ባለስልጣናር በአሜሪካ ቤት ያላቸው፣ በአሜሪካ ባንኮች ገንዘብ የሚያሰቀምጡ እንደሆነ ይነገራል። በአመት ከ370 ሚሊዮን ዶር እርዳታም አሜሪካ ለኢትዮጵያ እንደምትሰጥ ይታወቃል።
በአምባሳደሯ ወይም በስቴት ዲፓርትመንት በአፍሪካ ጉዳይ ሃላፊ ደረጃ ሳይሆን፣ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደረጃ የነ እስክንደር ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት፣ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ጆን ኬሪ፣ በአደባባይ እስክንደርን መጥቀሳቸው፣ ምን ያህል በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ከላይ ያሉ የአሜሪካ ባለስልጣናት እያሳሰበ እንዳለ የሚያሳይ ነው።
ጆን ኬሪ የሚከተለውን ነበር ያሉት፡
“The truth is that some of the greatest accomplishments in expanding the cause of human rights have come not because of legislative decree or judicial fiat, but they came through the awesomely courageous acts of individuals, whether it is Xu Zhiyong fighting the government transparency that he desires to see in China, or Ales Byalyatski, who is demanding justice and transparency and accountability in Belarus, whether it is Angel Yunier Remon Arzuaga, who is rapping for greater political freedom in Cuba, or Eskinder Nega, who is writing for freedom of expression in Ethiopia, every single one of these people are demonstrating a brand of moral courage that we need now more than ever.”

ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ለችግሮቻችን የመፍትሄው ቁልፍ ገለታው ዘለቀ

March 2nd, 2014                   
የሃገራቸው ነገር ሲነሳ የሚከነክናቸው ወገኖቻችን ኢትዮጵያ ላለባት ችግር መፍት ሄው ምንድነው? እያሉ ኣጥብቀው ሲጠይቁ ይደመጣል። መፍትሄውም ብቻ ሳይሆን ችግሩ ማለትም እውነተኛው ችግር የት ላይ ነው ያለው? ብለውም ኣጥብቀው ሲደመሙ ይታያል። በዛሬዋ ኣጭር ጽህፌ በነዚህ መራራ ጥያቄዎች ዙሪያ ቁንጥል ኣሳብ ለማቀበል ኣስቢያለሁ።
በርግጥም ሁላችን ኢትዮጵያዊያን የሆንን ችግሩ ምንድነው? ብለን ከጠየቅን ኣንዳንዶች ሊገረሙብን ይችላሉ። የችግሩ ተካፋይ ሆነን ሳለ፣ እየተጉላላን ያለነው እኛው ሆነን ሳለ፣ እንደገና መልሰን የሃገራችን ችግር የት ጋር ነው? ብለን ስንጠይቅ የምናወጋቸው ሰዎች ምናልባትም ግራ ሊጋቡ ቢችሉ ኣይደንቅም። ነገር ግን መጠየቃችን ትክክል ነው።
በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ትንቢተ ዳንዔል ላይ ኣንድ ናቡከደነጾር የተባለ ንጉስ ኣንድ ጊዜ ጠቢባንን ጠርቶ የህልም ፍቺ ይጠይቃል። ጥበበኞቹም ህልሙን ንገረንና ፍቺውን እንነግርሃለን ሲሉት ህልሙ ጠፍቶብኛል ስለዚህ ህልሙንም ፍቺውንም ውለዱ ብሎ ጉድ እንዳፈላ እናነባለን። እኛ ኢትዮጵያዊያን የዋናው ችግር ተጽእኖዎች የየእለት ኑሮኣችንን ሲያምሱት ብናይም ዋናውን የችግሩን ምንጭ መፈለጋችን ግን ኣሁንም ትክክል ነው።
የሃገራችንን ዋና ችግር የት ጋር ነው ብለን ኣጥብቀን ከጠየቅን በርግጥ የስርዓት ችግር ነው ወይ? ስርዓት በማጣታችን ነው ወይ የከፋ ችግር ላይ የወደቅነው? ብለን እንጠይቃለን። በዚህ ኣገባብ ስርዓት ስንል የኣይዲዮሎጂውን ጉዳይ ሳይሆን ፍትህና ተጠያቂነት፣ ግልጽነትና የህዝብ የበላይነት የሚንሸራሸርበት ሲስተም ተዘርግቷል ወይ ብሎ የመጠየቅ ያህል ነው። ስለ ስርዓት ስናነሳ ደግሞ በዋናነት የሚታየው ህገ- መንግስታዊ ስርዓቱ ነው። ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ምን ያህል ለዜጎች ይጨነቃል፣ ምን ያህል ለፍትህና ለነጻነት ለህዝቦች ጥቅም መንሸራሸሪያ ይህናል? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። በዚህ ረገድ በርግጥ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም በዋናነት ግን ችግራችን የስርዓት ችግር ሆኖ ኣናይም። ለኣብነት የ1955ቱን ህገ መንግስት ስናይ የፕሬስ ነጻነትን ይሰጣል፣ እኩል የህግ ከለላ ይሰጣል፣ የመሰብሰብ፣ ሰልፍ የማድረግ መብትን ሁሉ ይሰጣል። የደርጉም ቢሆን ለዜጎች የሚጨነቅ ኣይነት ነው። “ኢትዮጵያዊያን በህግ ፊት እኩል ናቸው” ይላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የ1995ቱን ስናይ “ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው” ብሎ እጅግ ኣጠንክሮ ለዜጎች መብት መቆሙን ይደነግጋል። በውነቱ ይህ ኣንቀጽ ብቻውን ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ዋስትና ይሆን ነበር። ይሁን እንጂ ተግባራዊው እውነት ደግሞ ለብቻው በተቃራኒው ተንሰራፍቶ ይታያል። ይህ ለምን ሆነ? እንዴት እንዲህ ሊሖን ይችላል? ብለን ነው መጠየቅ ያለብን። እንዲህ ስንጠይቅ የችግሩ ዋና ጉዳይም የስርዓት እጦት ሳይሆን ሌላ ጉዳይ መሆኑን እንረዳለን። በርግጥ ለወደፊቱዋ ኢትዮጵያ የተሻለ ስርዓት ማምጣት ያስፈልጋል። በተለይም ብዙህነቱዋን ተንከባክቦ የሚይዝ ማህበራዊ የፖለቲካ ስርዓት ያሻናል። ያ ማለት ግን ከችግራችን እንድንወጣ ብቻውን ዋስትና ነው ማለት ኣይደለም። የቱንም ያህል ጥሩ ስርዓት ዘርግተን ከችግራችን ሳንወጣ ልንቆይ እንችላለን። ርግጥ ነው የማንነት ፖለቲካ ማህበራዊ ቀውስን ያመጣ ችግሮች የበለጠ እንዲነዱ የሚያደርግ ጉዳይ በመሆኑ ከዚህ መንግስት ውድቀት በሁዋላ ከዚህ የፖለቲካ መዋቅር መውጣታችን ለመፍትሄ ትልቅ በር ኣለው። ይሁን እንጂ ኣሁንም ቢሆን የቱንም ያህል ቆንጆ ስርዓት እናምጣ ኢትዮጵያን ከመከራና ከርሃብ የሚያወጣት እሱ ብቻውን ኣይደለም። ታዲያ ምንድነው? የሚል ጥያቄ መምጣት ኣለበት። ኣዎ፣ ዋናው የሃገራችን ችግር ያለው የፖለቲከኖች ስብእና ተክለሰውነት ወይም ፐርሰናሊቲ ጋር የተገናኘ ነው።
ሃገራችን ከችግር እንድትወጣ ከተፈለገ የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። የችግሮቻችን ቁንጮም የፖለቲካ ቁርጠኝነት እጦት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል።የፖለቲካ ቁርጠኝነት ስንል ኣንድ ፓርቲ ስልጣን ከያዘ በሁዋላ የፍርድ ቤቱን ልጓም ለቀን መልሶ ከበላንም ይብላን፣ በራሳችን ላይ ይፍረድብን፣ ብሎ በራስ ላይ የመወሰን ኣቋም ነው። ወታደሩን ኣገርህን ጠብቅ የፓርቲ ጠባቂ ኣይደለህም ኣንተ ኣገር ጠባቂ ነህ ለማለት የፖለቲካ ሰዎችን ቁርጠኝነት ይጠይቃል። ፖሊሱን፣ ባንኩን፣ ሚዲያውን ሁሉ ልጓሙን ለቆ በሙያህ ኣገልግል ብሎ መወሰን ሲቻል ነው ከገባንበት ኣረንቋ የምንወጣው። የናፈቀንን ዴሞክራሲ በህይወት የምናየው። ጥያቄው ይህ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዴት ሊመጣ ይችላል ነው። የፖለቲካ ቁርጠኝነት ከጥቂት የፖለቲካ መሪዎች ከራስ ጥቅምና ዝና በላይ የህብረተሰብን ዝናና ጥቅም በተጠሙ ሰዎች ሊነቃነቅ ይችላል። ኣንድ ቁርጠኛ መሪ ኣገር ሊለውጥ ይችላል። በታሪክ የታዩ ኣንዳንድ ቁርጠኛ መሪዎች በየሃገሩ ተነስተው ጥሩ መሰረት እየጣሉ ኣልፈዋል። በሃገራችንም የተጠማነው ይህንን ነው።
በኣሁኑ ጊዜ ተቃዋሚው ክፍል መንግስትን ኣጥብቆ ማውገዙ ትክክል ነው። የህዝቡም ልብ ነጸብራቅ ነው። ይሁን እንጂ ይህ መንግስት በማንኛውም መንገድ ሲወድቅ ስልጣን ይዞ ጥሩ ስርዓት መዘርጋቱ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ቁርጠኝነት (political commitment) ያላቸውን ሰዎች ይዘዋል ወይ? ብለን እንድናስብ ያደርገናል። በዚህ ረገድ ተቃዋሚው ጥቃቅን በሆኑ ፖሊሲዎች ከመከፋፈል ይልቅ ወደ ጋራ እያመሩ ከሁሉ በላይ የፖለቲከኞችን ስብእና የመገንባቱ ላይ ማተኮር ለነገይቱ ኢትዮጵያ ዋስትና ይሆናል። ይህን ስብእና ወይም ተክለሰውነት የመገንባት ስራ ፓርቲዎችን ቢዚ የሚያደርግ ወቅታዊ ስራ መሆን ኣለበት። ኢትዮጵያ በኣሁኑ ደረጃዋ ጥቃቅን ፖሊሲዎችን በማነጻጸር የምታማርጥበት ጊዜ ላይ ኣይደለችም። መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ያጣች በመሆኑዋ የስካንዲኒቪያው ኣይነት ዴሞክራሲ ይሻልሻል የኣሜሪካው ኣይነት? ማለቱ ያልበላትን የማከክ ያህል ነው። ሁሉቱም ሆኖላትስ ነው?
ዋናው በኣሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጉዳይ ፓርቲዎች እኔ እሻላለሁ ለማለት ዋናው መመዘኛቸው የተሰባሰቡት በተለይም ኣመራር ላይ ያሉት ግለሰቦች የፖለቲካ ቁጠኝነት ኣላቸው ወይ? ቁርጠኝነት በሞላቸው ሰዎች ቁጥር የትኛው ፓርቲ ያይላል? የሚል ልብ ያለው ድጋፍ ነው በተግባር የሚታየው ወይም መታየት ያለብት።
በቲየሪ ደረጃ በኣሁኑዋ ኢትዮጵያ በፍርድ ቤት ጉዳይ መንግስት ጣልቃ ኣይገባም። ይሁን እንጂ በተግባር ይገባል። ይገባል ብቻም ሳይሆን ፍርድ ቤት የፖለቲካ መሳሪያ ነው። ኣሁን እዚህ ጋር የጎዳን የስርዓቱ ወይም የኣሰራሩ ጉዳይ ሳይሆን መከራ ውስጥ የከተተን ጉዳይ የግለሰቦች ስብእና ጉዳይ ሆኖ ነው የምናየው። ለምን እነዚህ ግለሰቦች ስርዓቱን ይጥሳሉ፣ ህጉ ለምን ኣቅም ያጣል? ካልን የፖለቲከኞቹ ላእላይ ስብስብ በተለያየ የግል ጥቅማጥቅም የተተበተበ በመሆኑ ነው። ድህነታችንም ኣንዱ ኣስተዋጾ ያደረገ ይመስላል። የተሻለ ስራ ለማግኝነት፣ ከድህነት ለመላቀቅ፣ ፖለቲካን መሳሪያ ማድረጉ የተለመደ መሆኑና ወደዚያ ጠጋ ያሉ ሃላፊዎች በዚህ ሞቲቭ የተሞሉ ስለበዙበት ስርዓቱ በቁሙ እንዲሞት ኣድርጎታል።
ባለፈው ጊዜ ኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን ማቋቋም ያስፈልጋታል የሚል ኣንድ ኣርቲክል ጽፌ ነበር። በርግጥም በኣሁኑ የነጻነት ትግል ኣሰላለፍ በኩል ጎድሎ የታየው ይሄ ነውና ይህንን ማቋቋም ተገቢ ነው። ይህ ኮሚሽን ፓርቲዎችን እያበራታታ ይህን ተፈላጊ ስብእና በመገንባቱ ረገድ ከፍተኛ ኣስተዋጾ ያደርጋል። ፓርቲዎችን በማቀራረብ ረገድ፣ የመፍትሄ ኣሳቦችን በማጠናቀር ረገድ፣ ለኣዲሲቱዋ ኢትዮጵያ የሚሆነውን ኣዲስ ሰውነት በመጠቆሙ ረገድ ከባድ ሚና ሊጫወት ይችላል። ከዚያ በተረፈ ደግሞ እኛ ተራ ዜጎች መሪዎቻችንን የማጎልበትና ወደ ህብረት የመግፋት እንዲሁም ስብእናቸውን የመገንባት ሃላፊነት ኣለብን።
የብዙ ኣፍሪካ ሃገሮች ችግር ይሄ ይመስለኛል። ታግለን በብዙ መስዋእትነት ኣንድ ኣምባገነን ከጣልን በኋላ መልሰን በሌላ ኣምባ ገነን እንተካለን። ሌላው ኣለም እየተሻሻለ ሲሄድ ይሄኛው ክፍለ ኣለም ወደ ኋላ የቀረበት ትልቁ ምክንያት የነጻነት ታጋዮች ራሳቸው በሚገባ ለኣመራር የሚበቃ ስብእና ሳያዳብሩ ወደ ስልጣን ስለሚመጡ ነው።ደቡብ ሱዳን ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናት። ለብዙ ኣመታት የነጻነት ትግል ታግለው፣ ብዙ ደም በመፍሰሱ ዓለም ሁሉ እነዚህ ሰዎች ቢገነጠሉ ይሻላል ብሎ ፈርዶላቸው ተገነጠሉ። የዳርፉሩን እልቂት የማያውቅ፣ ያልሰማ ያለም ክፍል የለም። ያ ሁሉ ሆኖ ኣዲስ ኣገር ከመሰረቱ በኋላ ገና ኣንድ ጊዜ እንኳን ምርጫ ሳያካሂዱ፣ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ሳይመሰርቱ፣ ከሁለት ዓመት ያልዘለለ እድሜ ያላትን ኣገር በጎሳ ከፋፍለው ማመስ ጀመሩ።
ያለ መታደል ሆኖብን በኣንዳንድ ኣፍሪካ ሃገራት የሚነሱ መሪዎች ስልጣን ላይ ከመጡ በሁዋላ ሁለት ነገር በጣም ይወዳሉ። ኣንደኛው ዝና ሲሆን ሁለተኛው ገንዘብ ነው። ሁለቱም እጆቻቸው ይዘዋል። ባንዱ ስልጣን በሌላው ገንዘብ። ዝናውን ወደው ገንዘቡን ችላ የሚሉ ቢሆኑ ትንሽ ይሻል ነበር። ነገር ግን ሁለቱንም በሃይል ስለሚወዱና ለዚህ የተሰጠ ስብእናቸው በውስጣቸው ስላልሞተ ክብ በሆነ ችግር ውስጥ እንድንወድቅ ኣድርጎናል።ኢትዮጵያዊያን በዚህ ላይ ልንነቃ ይገባናል። በተለይ የፖለቲካ ሰው መሆን የፈለጉ ወገኖቻችን፣ መሪ መሆን የሚሹ ወገኖቻችን በየጊዜው የባህርይ ለውጥ እያሳዩ በኣመለካከትና በሃላፊነት ስሜት እያደጉልን እንዲሄዱ እንሻለን። ከፍ ሲል እንዳልኩት እኛ ተራ ዜጎች ከውጭ ሆነን መፍረድ ብቻ ሳይሆን መሪዎቻችንን መንከባከብና ፍቅርን ክብርን ማሳየት ለፖለቲካ ቁርጠኝነታቸው ሃይል ይሰጣል።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ለአማራ ትግሬዎች የመጀመሪያና የመጨረሻ መልእክት

March 1, 2014
ነፃነት ዘለቀ (ከአዲስ አበባ)
“መልእክት” ያልኩት አቀራረቤን ቀለል በማድረግ የአንባቢያንን ቀልብ ላለመግፈፍ ነው፡፡ እንጂ መነሻየ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነው፡፡ ማስጠንቀቂያም ይባል መልእክት ዋናው ጉዳይ በግሌ የተሰማኝንና የማምንበትን ለወገኖቼ ድኅነት ስልም የምጽፈው ነገር ለባለአድራሻዎቹ መድረሱ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁሉንም ድረገጾች ትብብር በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ እባካችሁን ለሁሉም ካድሬ መልእክቴን አድርሱልኝ፡፡
ሰው ክርስቶስን መሆን እንዳይችል ጠላት መንገድ እየዘጋበት መቸገሩ የሚታወቅ ነው፡፡ መሆን  ቢፈልግ ግን ይችላል፤ የሚከለክለው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ክርስቶስ ራሱም ያለው “እንደኔ ሁኑ፤ እኔን ምሰሉ” ነው፡፡ ችግሩ ክርስቶስን ለመሆን ወይም ቢያንስ ለመምሰል የእምነት ጽናትና እውነተኛ ፍቅርን የተላበሰ ስብዕና ማጣት ነው፡፡ ተራራን ሊያዞር የሚችል እምነት፣ የሚጠላንን ብቻም ሳይሆን የሚገድለንንም ጭምር  የሚያፈቅርና ለጨካኞች የሚራራ ልብ፣ የማይወላውል እምነትንና የማያዳላ ፍቅርን የሚገልጥ በጎ ሥራ ካለ ከፈጣሪና ከአንድያ ልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ውህደት መፍጠርና ጓደኛ መሆን የማይቻልበት ምክንያት የለም፡፡ የሚጠይቀው እውነተኛ የልብ መሰበርን ብቻ ነው፡፡
ክርስቶሳዊ ተምሳሌትነትን በተወሰነ ደረጃ በመውሰድ አካሄድን ማረቅና ማስተካከል ይቻላል፡፡ ከወቅቱ አቢይ ሃይማኖታዊ ክንውን እንጀምር፤ ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከፆመ በኋላ በሰይጣን ሦስት ጥያቄዎች ቀርበውለት በአሸናፊነት ተወጥቷል፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ እንዲህ የሚል ነበር፤ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስኪ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ”፡፡ የክርስቶስም መልስ “ ‹ሰው የሚኖረው እግዚአብሔር በሚናገረው ቃል እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም› ተብሎ ተጽፏል፡፡” አዎ፣ ለአስተዋይ ሰው በእንጀራ ብቻ መኖር እንደማይቻል ግልጽ ነው፡፡ እርግጥ ነው ሰይጣን በሚያስፈልገን ነገር ይመጣብናል፡፡ ሰይጣንና የስለላ ድርጅቶች ተመሳሳይነት አላቸው፤ በምትወደው ነገር ይመጡብህና ወጥመዳቸው ውስጥ ይከቱሃል(cf. blackmailing)፡፡ ክርስቶስንም በዚያ ቀዳዳ የመጣበት አርባ ቀንና አርባ ሌሊትን ካለምንም ምግብ በመክረሙ ተርቦ ነበርና ይሸነፍልኛል ብሎ ነው፡፡ እንዳሰበው ግን አልሆነለትም፡፡ ያ ምናልባት ሥነ መለኮታዊ ጣጣ ስላለው ለምድራዊ ሕይወት ጥሩ አብነት ላይሆን ይችላል፡፡ እናም የአርባ ቀኑን የክርስቶስ ፆም እንርሳውና አብዛኛው የአሁኑ ዘመን ሰው አንድ የምግብ ሰዓት አልፎበት አይደለም ትንሽ ሆዱ ጎደል ካለ እናቱን ከመሸጥ እንደማይመለስ እናስብ፡፡ አሰብን?…
ፈተናዎች በጥቅሉ የሥጋና የነፍስ ተብለው በሁለት ዐቢይ ክፍሎች ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ በአማርኛ ፈተናን የሚገልጡ ቃላት ውሱን ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ እንግሊዝኛው ሳይሻል አይቀርም፡፡ “test, quiz, exam, examination, temptation, assessment …” የሚባሉ ቃላት አሏቸው፡፡ እነዚህ ቃላት በዐውድ ውስጥ መገኘት ሳያስፈልጋቸው በቁማቸው የሚሰጡት የተወሰነ ምስል አለ፡፡ እኔ አሁን እዚህ ላይ ልጠቅሰው የምፈልገው የፈተና ዓይነት በእንግሊዝኛው አጠራር temptation የሚለውን ነው፡፡ የአባታችን ሆይ ጸሎት ውስጥ “ Our Father who art in heaven … lead us not into temptation but deliver us from evil.” እንደሚል፡፡
ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳንወጣ የክርስቶስን ደቀ መዝሙርና የግምጃ ቤት ኃላፊ የአስቆሮቱ ይሁዳን እናስታውስ፡፡ ከገቢ ገንዘቦች አሥር መቶኛውን ለራሱ እንዲያደርግ ተፈቅዶለት የነበረው ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር ክፉኛ የተለከፈ ነበር – ልክ እንደወያኔ፡፡ ይህ በሽታው ተባብሶበት በመጨረሻው ክርስቶስን ራሱን በሠላሣ አላድ ለጠላቶቹ አሳልፎ ሸጦታል፡፡ ገንዘቡን ግን አልተጠቀመበትም፡፡ ያልተጠቀመበትም ምክንያት ክፍያውን እንደተቀበለና ክርስቶስን ያሳድዱት በነበሩ አይሁዳውያን እንዳስያዘው የሰረፀበት ሰይጣን ለጸጸት አጋልጦት በመለየቱ ምክንያት ራሱን ሰቅሎ ስለሞተ ነው፡፡ የይሁዳ ነፍስ አልተማረችም፡፡ ይህን እውነት ከመጽሐፍ ቅዱስ እናገኘዋለን – ሊማር አለመቻሉንም ጭምር፡፡
ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ወደፈተና ይገባል፡፡ ለሆዱና ስለሆዱ በሆዱ የሚፈተን አለ፤ በሆድ መፈተን መጥፎ ፈተና ነው፡፡ ሀገርን የሚያሸጥ የሆድ ፍቅር የተጠናወተው ሰው ደግሞ በሕይወት ዘመኑ በሚኖረው የስብዕና መመሰቃቀል ብቻም ሣይሆን ልጆችን ወልዶ ቢያልፍ በሀፍረት አንገታቸውን ይደፋሉ፤ በሕዝብ ዘንድም መጠቋቆሚያ ይሆናሉ፡፡ታሪኩ የጠቆረና የትውልድ ማፈሪያ ይሆናል – አሁንም እንደወያኔ፡፡
አንድ ሰው ፈተናን ወደቀ የምንለው ነባር እምነቱንና ታማኝነቱን ለሆነ ጥቅም ሲል ክዶ ከትክክለኛው መንገድ ሲወጣ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ታሪክ ስንመለከት ሁለት በፈተና የወደቁ አካላትን እናገኛለን፡፡
ዋናው ተፈታኝና ፈተናውን ከመነሻው የወደቀው ከትግሬው ብሔር የወጣውና ሕወሃት በመባል የሚታወቀው ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ሕዝብ ኃይል ነው፡፡ ለዚህ ድርጅት በፈተና መውደቅ መንስኤው ዓላማና ለጥቅም ነው፡፡ የሚታወቅን ነገር መዘርዘር አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡
ሁለተኞቹ ተፈታኞች ሁሉን ነገር እያወቁ ለፍርፋሪ እንጀራና ለማያዙበት የይስሙላ ሥልጣን ሲሉ በሕወሃት ሥር በባርነት አድረው የወጡበትን ሕዝብ ለወያኔ የሸጡ ይሁዳ አማሮች – ብአዴን ተብዬዎቹ – ናቸው፡፡ በሃይማኖታዊ አገላለጽ ሕወሃትን ልምጭ አስይዘውና በሁለንተናዊ ዘመናዊ መረጃ ደግፈው ጃዝ ብለው የላኩት የታላቁ ወንድም (The Big Brother) ባለሟሎችን የሉሲፈር ደቀ መዛሙርት ልንላቸው እንችላለን፡፡ ታሪካዊ ቂም በቀል አርግዘው ኢትዮጵያን ለማጥፋትና በእግረ መንገድም ቤት ያፈራውን ሥልጣንና ሀብት በግል ለመቆጣጠር የተነሡ የትግሬ ወያኔዎችን  በሉሲፈር አጣማጅ በሰይጣን በራሱ ልንመስላቸው እንችላለን፡፡ ለሆዳቸው ያደሩ በተለይም የዕልቂት ዐዋጅ ከታወጀበት የአማራው ሕዝብ እንደተገኙ የሚነገርላቸው ከሃዲዎችን ደግሞ በሰይጣን አገልጋይነት ልንፈርጃቸው እንችላለን፡፡ የሆነው ሆኖ ትግሬም ይሁን አማራ ወይም ሌላ ከእውነተኛው የጤናማ ኅሊና መንገድ ወጥተው ኢትዮጵያን ለማውደም እስከተሰለፉ ድረስ ሁሉም የጥፋት ወኪሎችና የክፉ መንፈስ ምርኮኞች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ያለው አጥፊ ኃይል ደግሞ የዓለም አቀፉ የጥፋት ኃይል ቅርንጫፍ ነው፡፡ ይህ በከፍተኛ ጥንቃቄና የሸር ጥልፍልፍ ወይም ሤራ (Conspiracy) የሚካሄድ የዓለምን ፖለቲካና ኢኮኖሚ የመቆጣጠር ዕቅድ ጅማሮው ቀደም ቢልም በሁሉም አቅጣጫ በተቀነባበረ ዘመቻ ወደስኬት ጫፍ የደረሱ የመሰሉት ግና አሁን በምንገኝበት የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው – የመሠረት ግንባታው ደርዝ መያዝ የጀመረው ግን የዛሬ 300 ዓመታት አካባቢ በ18ኛው መ/ክ/ዘመን መግቢያ አካባቢ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የሚያሠማሯቸው ጉዳይ አስፈጻሚ ተላላኪዎች ዘርና ቀለም፣ ፆታና ሃይማኖት ሳይገድባቸው እንደ እስስት ከየሚሄዱበት አካባቢ ሕዝብ ጋር እየተመሳሰሉ ሀገርንና ሕዝብን በቅርበት ይቆጣጠራሉ – ሲያሻቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲያሻቸው ደግሞ ሽጉጥ በመያዝ በመስቀል ከቀላጤ ‘politico-psuedo-religious’ ዘመቻ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስና የባሕርይ አባታቸውን ሊቀ ትጉሃን ዲያብሎስን ለማስደሰት ይጥራሉ፡፡ በመንግሥታት ጀርባ ሥውር መንግሥታትን በማቋቋም ሁሉንም ነገር በዐይነ ቁራኛ ይከታተላሉ – ሊያውም በ“ሁሉን ተመልካች” አንዲት ዐይናቸው! በዓለም አቀፍ ግዙፍ ካምፓኒዎቻቸው አማካይነትም የዓለምን ሀብትና ንብረት ይዘርፋሉ፤ ነዳጅና የተፈጥሮ ማዕድናትን እያሰሱ ለማይጠረቁት ሥውር ቱጃሮቻቸውና የምሥጢራውያን ድርጅቶቻቸው አለቆች ያስረክባሉ – ሁሉ በጃቸው ሁሉ በደጃቸው፤ ጦሩም ስለላውም አስተዳደሩም ምኑም ምናምኑም በነሱው ቁጥጥር ስለሚገኝ የ‹ሪሶርስ›ና የሰው ኃይል ችግር የለባቸውም፡፡ ጦርነቶችን ይፈጥራሉ፤ ሲፈልጉ ያጣላሉ – ሳይፈልጉ ያስታርቃሉ፡፡ መሣሪያዎቻቸውን ለተዋጊ ወገኖች በግልጥና በድብቅ ይሸጣሉ፡፡ ትውልድን ከሃይማኖትና ከባህል አውጥተው መና ለማስቀረት፣ ከሞራልና ሥነ ምግባር ማዕቀፎች ለይተው ባዶ ለማስቀረት እነሆሊውድን ከመሳሰሉ ተቋሞቻቸው ባፎሜታዊ ፊልሞችንና ሙዚቃዎችን በዓለም ይበትናሉ፡፡ ሀሺሺንና መጠጦችን በማምረት በሥውር ያሰራጫሉ፡፡ የሚገርመው እነዚህ ኃይሎች ፀረ-ሀሽሽ መስለው ቢቀርቡም ውሸታቸውን ነው፤ ከአፍጋስታን እስከ ኮሎምቢያና ሜክሲኮ የዐደንዛዥ ዕፅ ምርትና ገበያን የተቆጣጠሩት እነሱው መሆናቸውን የሚገልጡ መረጃዎች የአደባባይ ምሥጢር ከሆኑ ሰንብተዋል፡፡ ወያኔም እንደዚሁ ወጣቱን በጫትና በመጠጥ እያደነዘዘ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖር መጣሩን አንርሳ፡፡ በብዙ ነገር መመሳሰላቸውን ልብ እንበል፡፡ ወያኔን የሚገዛ ህግ እንደሌለ ሁሉ እነሱንም የሚገዛ ህግ የለም፡፡ የነሱን ደንቆሮ በሀሰት የዶክትሬት ዲግሪ የምስክር ወረቀት ለዓለም አቀፍ ተልእኮ ቢያሰማሩት ታማኝነቱ እንጂ ትምህርቱ ብዙም ፋይዳ ስለሌለው በአጭበርባሪነት የሚጠይቀው የለም – በወያኔ ቤትም ለባለሥልጣን ያልተበተነ የዲግሪ ዓይነት የለም – ባዶ ጭንቅላት ላይ ጥቁር ቆብና ጥቁር ካባ፡፡ ከነሱ ቁጥጥር የሚወጣን ሀገር መሪ(ዎች) በስለላ ድርጅቶቻቸው ልዩ ኮማንዶና በጨረር አነጣጥሮ ተኳሽ የፓራትሩፐር እስኳድ ያስወግዳሉ – ለሀገሩ የሚቆምን ሀገር ወዳድ ግለሰብም በዚህ መልክ ደመ ከልብ ሆኖ እንዲቀር ያደርጋሉ (ነፍስ ይማር – ኢቅእ(?))፡፡ (ቅን ታዛዦቻቸው ሊያፈነግጡ ወይም ጌታ ሊለውጡ ካሰቡም ይሄው የቅጣት በትር አይቀርላቸውም (ነፍስ ይማር – መዜአ (?))፡፡ … በሚያስወግዷቸው ምትክም የነሱን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስከብር መለስ ዜናዊን የመሰለ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ሀገር ወሮበላ በዴሞክራሲ ጭምብላቸው ለላንቲካው ይጎልቱታል – ዋናውን መዘውር በእጅ አዙር የሚይዙት ግን እነሱው ናቸው፡፡ በዓለም ባንክና በአይ ኤም ኤፍ፣ በኔቶና በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አማካይነትም በማይወዱት ሀገር ላይ የኢኮኖሚና ወታደራዊ ማዕቀብ ይጥላሉ፤ እንዳስፈላጊነቱም ጦርነት ያውጃሉ፡፡ ከነሱ ዕይታና ቁጥጥር ውጪ የሚሆን አንዳችም ነገር የለም፡፡ ነፍስና ሥጋህን ብቻ ሳይሆን የምታስበውንም ሁሉ ጭምር በ“Mind Control system”  ሊቆጣጠሩ ይሞክራሉ፡፡ ከፈለጉም በሰው ሠራሽ የመሬት መናወጥና ሱናሚ አንድን ሀገር ሊያደባዩ፣ አለዚያም በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መራጃ ዝናብን ከልክለው በድርቅ ሊመቱ፣ በሌላም በኩል ከመጠን በላይ ዝናብን አዝንበው በጎርፍና በመሬት መንሸራተት ናዳ ሕዝብንና መንግሥታትን ሊያስለቅሱ ይችላሉ፡፡ በአጭሩ የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ ደግሞም እውነት ነው፡፡ ወያኔዎችስ? ሥልቱና አፈጻጸሙ ይለያይ እንጂ አንድና አንድ ናቸው፡፡
የወያኔዎች የአንድ ለአምስት የጥርነፋ ሥልት የዚሁ የዓለም አቀፍ ዘመቻ አካል ነው፡፡ በአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ዕዳ ውስጥ የሚዶሉህም በዐይናቸው ሥር አውለው ሊቆጣጠሩህ ነው፡፡ በብድር የተያዘ ሰው ደግሞ ታውቃለህ – ውልፊት ሊል አይችልም፡፡ ሌላ ነገር አምሮህ ብታንጋጥጥ- ማንጋጠጥም አይደለም ለማሰብም ብታስብ ራሱ ያስወነጅልሃል፡፡ ያኔ በአሸባሪነት ባትጠየቅ እንኳን በገንዘብ ዕዳ ያለህን ንብረት ያሸጡሃል ወይም የፍትሃ ብሄር ወንጀልህ ተቀባብቶ ወደ ተሟላ ደረቅ ወንጀል ይዞርብህና ቃሊቲ ልትወርድ ትችላለህ፤ ለማንኛውም እሥር ቤት ውስጥ ነህ – የእሥር ቤቱ ስፋትና ጥበት ላይ የጋራ መግባባት ላይ እስከደረስን ድረስ፡፡ በቤትህ ውስጥ ሳይቀር ከአንተ ዕውቀት ውጪ ተከታታይ ሊመደብብህና መላ እስትንፋስህ ወደ ማዕከላዊ መረጃና ደህንነት መሥሪያ ቤት ሊያመራ ይችላል፤ ስልክህ ሊጠለፍ፣ ኢሜልህ ሊጠለፍ፣ ፌስቡክህ ሊጠለፍ፣ ሚስትህ ልትጠለፍ፣ ልጆችህና ጓደኞችህ ጭምር ሊጠለፉ፣ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ሁሉ አንተ ራስህም ልትጠለፍና የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ብዙ ሰይጣናዊ ነገሮች ሊደርሱብህ ይችላሉ፡፡ የእነአልማዝ ሠይፉን፣ የእነብርቱካን ሚዴቅሳን፣ የእነደበበ እሸቱን፣ የነስዬ አብርሃን ዝምታ ያዬ አንዳች ነገር ቢጠረጥር ሊፈረድበት አይገባም፡፡ በስማም የተባለበት ሰይጣን ይመስል በአርምሞ የተቀመጡበትን ምክንያት ከነሱ በስተቀር ማንም አያውቅም፡፡ አሣሪህና የስቃይህ ምንጭ ሲደርቅ ጮቤ መርገጡ ዲያብሎሳዊ መሆኑ እርግጥ ቢሆንም ለሰባት ቀን ሀዘን መቀመጡና በፈጣሪ ሥራ ገብቶ በ“ለምን ወሰድክብኝ” እዬዬ ማለቱ ሃይማኖታዊ መደላድል ያለው አይመስለኝም – የቃል መቀነት መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ የተገኘውም ይህን ዕንቆቅልሽ በአመስጥሮ ለመጠቆም ነው (አመስጥሮው እዚህ ላይ አበቃ እንጂ)፡፡ ለማንኛውም በዲያብሎስ ግዛት መብቴ ተረገጠ ሰው መሆኔ ተዘነጋ ብሎ መጠየቅ ሞኝነት ነው፡፡ ከሁሉ በባሰ ሁኔታ የጎንህ ፍላጭ ሚስትህ ወይም የአብራክህ ክፋይ ልጅህ ሊሰልሉህ ቢችሉ የዘመኑ የትልቁ ወንድምህ ፋሽን ነውና አይግረምህ፡፡ ወያኔ የትልቁ ዓለም አቀፍ ዘመቻ የምሥራቅ አፍሪካ ዋና መሥሪያ ቤት (Head Quarter) ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡ ከጆርጅ ኦርዌል ድንቅ መጽሐፍ (ከ “1984” ውስጥ) እስኪ ቀጣዩን ጥቅስ እንመልከት፡፡
He [Winston Smith] took a twenty-five cent piece out of his pocket. There, too, in tiny clear lettering, the same slogans were inscribed, and on the other face of the coin the head of Big Brother. Even from the coin the eyes pursued you. On coins, on stamps, on the covers of books, on banners, on posters, and on the wrappings of a cigarette packet—everywhere. Always the eyes watching you and the voice enveloping you. Asleep or awake, working or eating, indoors or out of doors, in the bath or in bed—no escape. Nothing was your own except the few cubic centimetres inside your skull.
ተዛማጅ ትርጉም፡- (ዊንስተን ስሚዝ) ሃያ አምስት ሳንቲም ከኪሱ አወጣ፡፡ በዚያች ሣንቲም ላይም በአንደኛው ገጽ በጥቃቅን ፊደላት የተለመደው መፈክር ተጽፏል፤ በሌላኛው ገጽ ላይ ደግሞ የታላቁ ወንድም የራስ ምስል ጉብ ብሏል፡፡ [(መፈክሩ - ‹ ጦርነት ሰላም ነው፤ ነጻነት ባርነት ነው፤ ድንቁርና ጥንካሬ ነው፡፡› የሚል ነው1፡፡)] ከዚህች ትንሽዬ ሣንቲም የምታየው የታላቁ ወንድም ዐይኖች ትክ ብለው ሲያዩህ መግቢያ ያሳጡሃል፡፡ በሣንቲሞች፣ በቴምብሮች፣ በመጽሐፍ ሽፋኖች፣ በዓርማዎች፣ በፖስተሮች፣ በሲጋራ ወረቀቶች፣ የትም ይሁን የትም እነዚህ የታላቁ ወንድም ዐይኖች ያፈጡብሃል፡፡ ምን ጊዜም ዐይኖቹ መግቢያ መውጫህን ይከታተላሉ፤ ድምፆቹም የጆሮ ታምቡርህን ያለ ዕረፍት ይጠልዛሉ፡፡ ተኝተህም ሆነ ሳትተኛ፣ ሥራ ላይም ሆንክ ምግብ ላይ፣ ከቤት ውስጥም ሆንክ ከቤት ውጪ፣ መታጠቢያ ቤትም ውስጥ ሁን በአልጋህ ላይ … የትም ሁን የት ከታላቁ ወንድም ዐይኖችና የዘወትር ክትትል ማምለጫ የለህም፡፡ ጭንቅላትህ ውስጥ ከሚገኘው ነጭ አንጎል ውጪ የኔ ነው የምትለው የግል ንብረት እንዲኖርህ አይፈቀድልህም፡፡ [እርሱንም ቢሆን አንተ አታዝበትም!]
በዲያብሎስ መንፈስ የሚነዳውን የአፍራሽ ኃይል (The Negative Energy) ዓለማቀፋዊ የጥፋት አድማስ በአጭሩ ለማሳየት የሞከርኩት የሀገራችን ጉዳይም ከዚሁ ኃይል ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ከዘመን ፍርድ ማምለጥ አስቸጋሪ ነውና፡፡ ዓለማችን የሁለት ተፃራሪ ኃይላት መስተጋብራዊ ውጤት ናት፤ እነሱም ገምቢ ወይም አወንታዊ ኃይልና አፍራሽ ወይም አጥፊ ኃይል ናቸው፡፡ ማንም ሰው ከነዚህ ሁለት እርስ በርስ ተጠፋፊ ነባራዊ ሁኔታዎች ውጪ አይደለም፡፡ በምንገኝበት መሬታዊ/ምድራዊ ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት አንዱ ካለ ሌላው አይኖሩም፡፡ ገምቢ ካለ አፍራሽ አለ፡፡ በዬቋንቋዎቻችንም ደግ – ክፉ፣ ፍቅር – ጥላቻ፣ ቸር – ንፉግ፣ ሃቀኛ – ዋሾ፣ ወዘተ. የመኖራቸው እውነታ ይህንን ለማጠየቅ ይመስላል፡፡ ችግሩ ምጣኔያቸው ላይ የሚታየው የሚዛን መዛነፍ ነው፡፡ አንዱ ከሌላው ግዘፍ ነስቶ ከታዬ ለምሳሌ የክፋት መንፈስ ከተንሠራፋ ሀገርና ሕዝብ ይጎዳሉ፤ እንደሀገረ ኢትዮጵያ ለአጠቃላይ ውድመት ሊዳረጉም ይችላሉ፡፡ ይህ ዓይነት አስቀያሚ ሁኔታ የሚፈጠረው ኅሊናን በመሸጥ ለሆድና ለጥቅም ማደር ሲከሰት ነው፡፡ ሰዎች ኑሯቸውን ያሸነፉና ያለፈላቸው እየመሰላቸው ብዙ ጣጣ ውስጥ ይገባሉ፤ በዚያም ሳቢያ ከፍለው የማይጨርሱት ዕዳ ውስጥ ይነከራሉ፡፡ የብአዴኖች ወንድምና እህቶቻችን ዕኩይ ተግባርም ከዚህ የሚመደብ ነው – በደቂቃዎች ውስጥ ዕዳሪና ሽንት ለሚሆን የሆድ ቀለብ (እህልና ውኃ)  ሀገርንና ሕዝብን የመሰሉ ዘላለማውያን ኅላዌያት ሲክዱ ማየት የታሪክ አሰቃቂ ፍርድና ምፀት ነው፡፡
ሕወሃት ኢትዮጵያን እያጠፋ ያለው ለዓላማና ለጥቅም ነው፡፡ የሕወሃት ተባባሪዎች የሆኑት ብአዴንና ሌሎቹ ኢትዮጵያን በማጥፋት ላይ ከሚገኘው ሕወሃት ጋር እየተባበሩ ያሉት ወገኖች ግን ለዓላማ ሣይሆን አንድም በድንቁርና ነው፤ አንድም በሆዳምነት ነው፡፡ አማራ አማራን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ዓላማ ነድፎ ከፀረ-አማራ ኃይሎች ጋር በማበር ሊንቀሳቀስ ይችላል ተብሎ መቼም አይጠበቅም፤ በውነቱ የብአዴኖችን ነገር ስናጤነው የእርግማን ካልሆነ የሌላ አይመስልም፤ ዕንቆቅልሽ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ አማራ ካልታመመ በስተቀር ዘመዶቹን ለመፍጀት በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ ሳይቀር በመታገያ ዓላማና ግብነት ቀርፆ የሚንቀሳቀስን ሰይጣናዊ ኃይል ሊተባበር አይችልምና ነው፤ በምንም ዓይነት መንገድ፡፡ ተጠየቃዊ አካሄዱም ይህን ታሪካዊ ህፀፅ ሊዳኝበት የሚያስቸለው ክፍተት የለውም – “ዕብደት ነው!” ብሎ የሚያልፈው ካልሆነ በስተቀር፡፡ በመሆኑም ብአዴን ውስጥ የሚገኙ አማሮች በየትኛውም ሚዛን ቢለኩ አንድም የለየላቸው ዕብዶች ወይም የለየላቸው ደናቁርት ማይማን ወይም ደግሞ ፀላኤ ሠናያት የሠፈረባቸው የክፉ መናፍስት ዋሻዎች ቢሆኑ እንጂ ለአማራ የሚቆረቆሩ አማሮች ሊሆኑ አይችሉም – ቃል ቢቸግረኝ እንጂ “ማይም” ማለቴ ራሱ ስህተት ነው፡፡ ማይምነት ከሀገር መሸጥና መለወጥ አይገናኝምና፡፡ ብአዴኖች አማራ አይደሉም ሲባል ደግሞ የደምና የአጥንት ጉዳይ ሳይሆን በፍካሬያዊ ትርጉሙ ነው፡፡ አማራን ከሚያጠፋ፣ ኢትዮጵያን ለመቅበር ጉድጓድ ከማሰ፣ ሀገርን ከሸጠና ከለወጠ ኃይል ጋር ያለ ሀፍረት አብሮ እየሠራ የሚገኝ “ሰው” አማራ ነኝ ቢል እንዴት ማመን እንደሚቻል ብአዴኖችን ራሳቸውን መጠየቅ ነው፡፡ በጣሊያን ጊዜ ከቅኝ ገዢው ባዕድ ወገን ጋር በባንዳነት ያገለግሉ የነበሩ ብዙዎቹ የዛሬዎቹ ገዢዎቻችን ወላጆች በንጽጽር ከብአዴኖች ይሻላሉ፡፡ ምክንያቱም የዚያኔዎቹ ባንዳዎች የካዱት መላዋን ኢትዮጵያን እንጂ የወጡበትን ጎሣና ነገድ አልነበረምና፤ በዚያ ላይ ጣሊያንም ቢሆን የወያኔን ያህል ቀርቶ ካልነኩት የማይነካና በጭካኔው ከወያኔ ፍጹም የማይወዳደር በአንጻራዊ አነጋገር እጅግ ሲበዛ ሰብኣዊ የነበረ ኃይል ነው፡፡ የኒህኞቹ ድርጊት ግን ዘግናኝ ወንጀል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ወንድምህን፤እህትህን፤ አባትና እናትህን፣ በጥቅሉ በዘመኑ ቋንቋ ዘርህንና ቤተሰብህን እንደዐይጥ ከሚጨፈጭፍ የባንዳ ውላጅ ጋር መተባበር፣ ከዚያም ባለፈ ሰሞኑን እንደምንሰማው የጠላትን አንደበት በመዋስ በእንደራሴነትም ቢሆን የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ በአደባባይ መዝለፍ በምንም ዓይነት መለኪያ ጤናማነትን አያሳይም፡፡ (Shall we say proxy badmouthing or insulting?) ይህ ዓይነቱ የብአዴን ድፍረት የኅሊና መታወርንና የአንጎል ጤንነት መቃወስን በግልጥ የሚያመለክት ነው፡፡ የአእምሮ ህክምናም ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡…
አሁን ምን ማድረግ ይቻላል? በዚህ መቀጠሉ ያዋጣል ወይ? እስከመቼስ በባለ አንድ ጥርስ ማርሽ ብቻ ማሽከርከር ይቻላል?
ሰዎች ከፈለጉ ለማንኛውም ችግራቸው መፍትሔ መፈለግና ማግኘትም ይችላሉ፡፡ ዋናው ነገር ችግር ውስጥ መገኘትን ማወቅ ነው፡፡ ይህ በራሱ የመፍትሔውን ግማሽ መንገድ እንደመጓዝ ይቆጠራል፡፡ ከዚያም ንስሃ መግባት ነው፡፡ ንስሃ መግባት ሲባል በዚህ ዐውድ መሠረት በሆነ ታሪካዊ አጋጣሚ በተፈጠረ ስህተት ገብተው የሚዋኙበትን የጥፋት ባህር ተረድቶ ከዚያ ለመውጣት ከልብ መጸጸት ማለት ነው፡፡ ጥፋት ሰብኣዊ ነው፡፡ ማንም ሰው ትንሽም ይሁን ትልቅ ስህተት ይሠራል፡፡ ከስህተት ጎዳና ለመውጣትና ተበዳይን ከልብ ይቅርታ ጠይቆ ለመካስ የሚተጋን ሰው ደግሞ ፈጣሪ ይወደዋል፡፡ ሰው ሲባል ከሌሎች እንስሳት የሚለየውና ክፉንና ደግን መለየት የሚያስችለው አንጎል ያለው በመሆኑ ከስህተቱ እየተማረ፣ ደካማ ጎኑን እያስወገደና ጠንካራ ጎኑን ይበልጥ እያሻሻለ ወደበለጠ አእምሯዊና አካላዊ ዕድገት መራመድ ይጠበቅበታል፡፡ ጥፋቱን እንደልማት ቆጥሮ በኩራት የሚጀነን ሰው ከወያኔ የሚመደብ የመከነ አእምሮ ባለቤት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደምናነበው ብዙዎች ቅዱሳንና ሰማዕታት ስህተትን ይሠሩ ነበር፡፡ ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ እነቅዱስ ዳዊት፣ እነሶሎሞን፣ እነጴጥሮስ … ሁሉም ይሳሳቱ ነበር፡፡ ግና በጸጸት ዕንባቸው ስህተታቸውን እያጠቡ ከእግዚአብሔር ምሕረትን እንዳገኙ ቅዱሣት መጻሕፍቱ ያስረዳሉ፡፡ ክርስቶስንና ክርስቶሳውያንን በጦር ያሳድድ የነበረው ኃጢኣተኛው ሳዖል፣ በኋላ ላይ በደገኛው የኢየሱስ መንፈስ ተመርቶ አንገቱን ለሠይፍ እስኪሰጥ ድረስ የክርስቶስ አገልጋይ ሊሆንና በቅዱስ ጳውሎስነቱ ሊታወቅ በቅቷል፡፡ አንድ ነገር እንድገም፡- አንዱ “ወንድሜ ሰባት ጊዜ ስህተትን ቢሠራብኝ ሰባት ጊዜ ሁሉ ይቅር ልለው ይገባኛልን?” ሲል ክርስቶስን ይጠይቀዋል፤ በርሱ ቤት ሰባት ብዙ ቁጥር መሆኑ ነው፡፡ ክርስቶስ ግን በሚገርም ሁኔታ “ሰባት ጊዜ ብቻ አይደለም፤ ሰባት ጊዜ ሰባም ቢሆን ይቅር በለው” ሲል ነው የመለሰለት፡፡ አራት መቶ ዘጠና ጊዜ ቆጥረህ ይቅር በል ለማለት አይደለም – ይቅር ባይነት ገደብ እንደሌለው ነው የዚያ አስተምህሮ ማዕከላዊ አንድምታ፡፡ ይህ ምሳሌ ሁለት መልእክት አለው፡፡ አንዱ ለበዳዮች – ሌላኛው ለተበዳዮች፡፡ በበዳይ ወገን በኩል ያየነው እንደሆነ “ብዙ በድያለሁና ይቅር ስለማልባል በጥፋት ጎዳና እንደተጓዝኩ ዕድሜየኝ ልፍጅ” ከማለት ያድናል፡፡ በተበዳይ ወገን በኩል ሆነን ያየነው እንደሆነ “ዕድሜ ልኩን ሲጫወትብኝ ኖሮ አሁን እንዲህ እንዲህ ያለ ነገር እንዳይደርስበት ስለፈራ ልታረቅህ ይለኛል፤ ደግሞስ ለስንት ጊዜ ያህል ከበደለኝ በኋላ ለምን ብዬ ነው ይቅርታውን የምቀበለው?” ከሚል ሰይጣናዊ ግብዝነት ይታደጋል፡፡ እናስ ምን እናድርግ?
ንስሃ ለመግባት ቅድመ ሁኔታ የለውም፡፡ አንድ ሰው ንስሃ መግባት የሚያስፈልገው ጥፋት በማጥፋቱ ነው እንጂ ባያጠፋማ ለምን? ለይቅርታ ደግሞ የጥፋት ደረጃ ማነስ ወይ መብዛት ለድርድር አይቀርብም፡፡ ዋናው ከልብ መጸጸትና ጥፋትን እርግፍ አድርጎ መተው ነው፡፡
በኢሳት እንደምንከታተለው ከብአዴኖች ምሥጢር እየሾለከ ወደተቃውሞው ጎራ እንደሚገባ ተነግሯል – ከኢሳት አንጻር የመረጃ ምንጭን የማጋለጥ ምሥጢሩ እስካሁን ባይገባኝም (ይህ ዓይነቱ ልበ ሙሉነት የመረጃ ምንጭን በማድረቅ ረገድ አሉታዊ ሚና እንደማይጫወት ባውቅ ደስ ባለኝ)፡፡ ለማንኛውም ይህ መልካም ጅምር ነው፡፡ በራሱ ግን በቂ አይደለም፡፡ በጣም ኢምንት ነው፡፡ ሙሤን ማስታወስ ይገባል፡፡ ሙሤ በፈርዖን መንግሥት ውስጥ ሆኖ ወገኖቹን ከሚጨፈጭፍ ኃይል ጋር – ሳያውቅ ነው – ይሠራ ነበር፡፡ ማንነቱን ከተረዳ በኋላ ግን 40 ሺህ እስራኤላውያንን ይዞ ከምድረ ግብጽ በመውጣት ሕዝቡን ከአስከፊ አገዛዝ ነጻ አውጥቷል፡፡ ብአዴኖችም ይህን ለማድረግ መረጃ ከመስጠት ባለፈ ብዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሰፊው የአማራ መሬት የአፓርታይድንና የፋሺዝምን ሥርዓት ሕዝባቸው ላይ መጫናቸውን ትተው ከነፃነት ታጋዮች ጋር በኅቡዕ ኅብረት መፍጠርና የነፃነትን ጊዜ ማፋጠን አለባቸው፡፡ እስካሁን የሠሩት ጥፋት ፊታቸው ላይ እየተደቀነ ሊረብሻቸው አይገባም፡፡ ያን በንስሃ ማጠብ የሚቻለው የሠሩትን ስህተት የሚክስ መልካም ሥራ ሢሰሩ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ንስሃ ሲገባ ያጠፋ የነበረውን ጥፋት ዳግመኛ ላለመሥራት ቃል የሚገባበትና የዚያን ተቃራኒ ደግ ሥራ ለመሥራት በዚያውም በደሉን ለማካካስ (atonement) ሌት ተቀን የሚተጋበት ዕድል ያገኛል፡፡ ንስሃ መግባት ሲጀመር ከሙስናና ከደም ማፍሰስ፣ ንጹሓንን በፖለቲካ ሰበብ ከማሰርና ከማንገላታት መቆጠብ ይገባል፡፡ በተመሳሳይ ቅኝት የሚጓዝ ሕይወት መጨረሻው አያምርም፡፡ ብአዴንም ሆነ ሌላው የወያኔ ተባባሪ እሚበላው ያው አንዲት እንጀራ ናት – ከዚያች አታልፍም፡፡ በተረፈ በቅንጦቱ ረገድ ቢጠጣ ዊስኪና ቢራ ነው፡፡ ቢተኛ ሞዝቮልድ አልጋ ላይ ነው፡፡  ይህ ደግሞ ይሰለቻል፤ በወንጀልና በኃጢኣት ወገንን ሸጦ በሚገኝ የደም ገንዘብ ተንፈላስሶ መኖር የሚቻለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ሰው የሆነ ሰው በደም ደለል ውስጥ መንቦራጨቁ እየተከሰተለት ሲመጣ በሂደት አእምሮውን የሚያስጨንቅ ነገር ይገጥመዋል፡፡ ጭንቀትን ለመሸፈን ከጧት እስከማታ በመጠጥ ብርጭቆ ውስጥ ቢወተፉ ኅሊና ቀስ እያለ መንቃቱ አይቀርምና በሁለትዮሽ የዞረ ድምር – በመጥፎ ሥራና በመጠጥ – መሰቃየት ይከተላል፡፡ ያኔ የሚከሰተውን የኅሊና ጅራፍ ደግሞ የሚቋቋመው የለም፡፡ ስለዚህ ብአዴኖች ከገባችሁበት አረንቋ በአፋጣኝ እንድትወጡ ብታውቁትም ባታውቁትም በኅያው እግዚአብሔር ስም እማጸናችኋለሁ፡፡ ይህን የምላችሁ ለሕዝብ በማዘን ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ የምትሠሩት መጥፎ ሥራ ከሚያመጣባችሁ የዕልቂት ማዕበል እንድትተርፉ በቅንነት ለእናንተም በማሰብ ጭምር ነው፡፡ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ግን ማትረፍ ካልተቻለው ምን ይጠቅመዋል? ይላል መጽሐፉ፡፡ የምሕረት በር ሳትዘጋ አሁኑኑ በንስሃ ታጠቡ፡፡ ሕዝባችሁ አምርሮ ጸልዮኣል፤ ጸሎቱም ተሰምቷል፡፡ እግዚአብሔር ይመስገንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ክብርንና ሞጎስን አግኝቶ መልስ የሚሰጥበት ጊዜ ተቃርቧል፡፡ ምልክቶቹም ሁሉ እየታዩ ነው፡፡ አንዱን ልንገራችሁ – ያ ወጣት ብላቴና ረዳት አብራሪ – ምንም ነገር ሳይቸግረው – ከነአውሮፕላኑ ለምን ያን የመሰለ ታሪክ የሠራ ይመስላችኋል? አስቡት፤ አስቡበትም፡፡ በዚህ መልክ ጥሪው የሚተላለፍላቸውና የነፃነት ፍልሚያውን የሚቀላቀሉ ወጣቶች በሠልፍ እየተጠባበቁ ናቸው፡፡
አፄ ቴዎድሮስ በጣም ጨካኝ እንደነበሩ ይነገራል፤ ምናልባትም በሁኔታዎች አስገዳጅነት ወደዚያ ደረጃ ተገፍተውም ሊሆን ይችላል፡፡ እርሳቸውም ያን ጠባያቸውን እንደሚያውቁና ሕዝብን ለመቅጣት ከፈጣሪ እንደተላኩ ለሚቀርቧቸው ይናገሩ እንደነበር ተጽፏል፡፡ አንድ ወቅት መነኮሳትን ከያሉበት ይጠሩና በየተራ እያስገቡ “ለመሆኑ እግዚአብሔር አሁን ምን እየሠራ ነው?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሁሉም የመሰለውን ይመልሳል፡፡ እርሳቸውን ያስደሰተች መልስ ግን አንድ ኮሣሣና ለነፍሳቸው ያልሳሱ (ሞትን የናቁ ማለቴ ነው) መነኩሴ “እግዚአብሔር በአሁኑ ሰዓት ቁናውን እየሰፋ ነው!” ሲሉ የተናገሩት ነው፡፡ አዎ፣ እሳቸውም አመኑበት፡፡ የሠሩትን ጥፋት ስለሚያውቁ፣ በሠፈሩት ቁና መሠፈርም ደንብ መሆኑን ስለሚረዱ አንገታቸውን ነቅንቀው በአግራሞት ነበር ያን መልስ የተቀበሉትና ባህታዊውን አመስግነው ወደመጡበት በክብር የሸኙት፡፡ ሌሎችን በትዝብት ዐይናቸው መግረፋቸውን ማስታወስ ካስፈለገ ግን ይሄውና አስታወስኩ፡፡
ወያኔንና ግብረ አበሮቹን ለመቅጣት እግዚአብሔር ቁናውን ሠፍቶ ጨርሷል፡፡ ወያኔን ያሣወረው ትዕቢት መቃብር ካልከተተው የማይለቀው ሆኖ እንጂ የወያኔ ጉድጓድ ከተማሰ፣ ልጡም ከተራሰና የመግነዝ በፍታውም ከተዘጋጀ ቆይቷል፡፡ የሚቀረው ሥርዓተ ግንዘቱና ጉዞ ፍትሃቱ ብቻ ነው፡፡ ያም በቅርቡ ይከናወናል፡፡ ለመሆኑ አሁን ሀገሪቷን ማን እያስተዳደራት እንደሆነ በግልፅ የሚያውቅ አለ? እኔ ከፈጣ ውጪ በሰው ደረጃ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድር ሰው አላውቅም፡፡ እርግጥ ነው የሆነ የወያኔ ቡድን መኖሩን አልክድም፤  ዋናው ግን በኪነ ጥበቡ እንደምንለው በዚያ ልዩ መለኮታዊ ኪነ ጥበብ ነው ውለን የምንገባው፡፡ ለማንኛውም መላው የኢትዮጵያ ጠላቶች ሂሳባቸውን የሚያወራርዱበትና በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ወያኔ የናኘው ማንኛቸውም የዘረኝነትና የጎሰኝነት አቧራ እንደጉም በንኖ የሚጠፋበት የነፃነት ዘመን ደጅ ላይ ቆሟል፡፡ ይህን ነፃነት ማንም ፈቅዶ አይሰጠንም፤ ማንምም ታግሎ አይነጥቀንም፡፡ የዕንባችን፣ የጸሎታችንና የመገፋታችን ውጤት፣ በወያኔዎች ደባ ለዓመታት የፈሰሰው ደማችን የሚያመጣልን መለኮታዊ ፀጋ እንጂ የሰው ስጦታ አይደለም፡፡ በየከተማው እንደሚያፋድሱት እነአባ መሸ በከንቱን የመሰሉ ሳይሆን በሩቅ ገዳማትና በሥውር ሥፍራዎች ቀን ከሌት ወደፈጣሪ የሚያለቅሱ አባቶችና እናቶች አሉን፡፡ ቢያንስ እነሱን አያሣፍራቸውምና መልሱን በቅርብ እንጠብቃለን፡፡ ኢትዮጵያችን ጥቂቶች በቁንጣን የሚሰቃዩባትና ሚሊዮኖች በጠኔ የሚረፈረፉባት ሀገር ሆና እንደማትቀር ቃል ኪዳን አለ፤ ሀገራችን የቃል ኪዳን ምድር ናት፡፡ እናም አይዞን!!!
ብአዴኖች ግን ወደ ኅሊናችሁ ተመለሱ፡፡ ይህ ጥሪየ ዘርን መሠረት ባያደርግብኝ ደስ ባለኝ፡፡ ነገር ግን ይበልጥ የሚያሣዝኑኝ እነሱ በመሆናቸው ነው ይህን የተለዬ ጥሪ እነሱ ላይ በማተኮር ማስተላለፍ የወደድኩት፡፡ ፈጣሪ መንሹን ሊጨብጥ – ገለባን ከምርቱ ሊለይ የማበራያ ዐውድማውን ለቅልቆ ጨርሷል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፤ ከያዘው አሼሼ ገዳሜና አሥረሽ ምቺውም ይመለስ፡፡ የዚህ ዳንኪራና ጮቤ ወጪ የሚሸፈነው ከምሥኪኑ ሕዝብ እየተመዘበረና በሙስና እየተዛቀ መሆኑ የማይካድ ነው፡፡ በዚህ የጥፋት መንገድ እየነጎዳችሁ ያላችሁ ወገኖችም ለቁሣዊ ፍላጎቶቻችሁና ለሰይጣናዊ ሱሶቻችሁ ልጓም አብጁላቸው፡፡ ይህን ስል ወንድም በወንድሙ ላይ የሚፈጽመውን ግፍና በደል ያቁም፣ ወደኅሊናውም ተመልሶ ለሁሉም እኩል በሆነ ህግ ይተዳደር ለማለት እንጂ ሃይማኖታዊ ንስሃ ግቡና ፁሙ ቁረቡ ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ ለዚያ ዓይነቱ ስብከት ይህ መድረክ ምቹ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ሰላም ክረሙልኝ፡፡

እቴጌ ጣይቱ ብጡል «እኔ ሴት ነኝ፣ጦርነት አልወድም፣ሆኖም ግን ኢትዮጵያን የጣሊያን ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ ፡፡ »


Image
* የጦርነቱ መነሻ ምክንያት …
     የዓድዋ ጦርነት መነሻ ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ሲሆን ይህ አንቀጽ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተን ሆኖ በመገኘቱ እንዲሰረዝ የተደረገው ሙከራም በጣሊያን እምቢተኝነት በመክሸፉ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
* የጣሊያን ወረራ መሰማትና እቴጌ ጣይቱ …
    የጣልያንን እምቢተኝነት ተከትሎ ሚኒስትሮች፣ የጦር አለቆችና መኳንንቱ ባካሄዱት የምክክር ጉባኤ ላይ እቴጌ ጣይቱ ብጡል «እኔ ሴት ነኝ፣ጦርነት አልወድም፣ሆኖም ግን ኢትዮጵያን የጣሊያን ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ ፡፡ » ሲሉ የሰጡት አስተያየት ነበር፡፡
* የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት የዳግማዊ አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ …
      ጣሊያን ውል አፍርሶ ኢትዮጵያን ሲወርር በጉልበቱ የጀግኖችን ሃገር ሊፈታው እንደማይችል ያውቅ ነበር። ጣልያን በልዩነታችን ገብቶ ሊለያየን እቅድ አቅዶም ነበር ። ይህንንም ለማሳካት በተለያየ አስተዳደር ግዛት ለይተው በሚቆራቆሱ የጦር አበጋዞችና በንጉሱ መካከል የነበረውን የከፋ ልዩነት መጠቀም ለድል እንደሚያበቃው አልሞ መነሳቱ እውነት ነበር ። ያም ሆኖ የንጉሰ ነገስቱ መኳንንቱን ፣ ሹመኞችን እና የጦር አለቆችን ሰብስበው በመምከር ብሔራዊ ክብርን ማስጠበቁ ይቅደም አንድምታ ያለው ሃሳባቸው ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ በሰለጠነ መንገድ ከመግባባት ላይ ደረሱ። ይህም ምክክርና ስምምነት ሁሉም በአንድነት ለነጻነትና ክብሩ ይተጋ ዘንድ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደርግ ዘንድ ሁሉም በየስራ ድርሻው ተመድበው መስራት ጀመሩ ።
መስከረም 1888 ዓ.ም  ወር ላይ ንጉስ ምኒሊክ ጣሊያንን ለወረራ መዘጋጀቱን በስለላ ባለሟሎቻቸው በቅርብ አረጋገጡ። በወረራ ዝግጅቱ የተቆጡት ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ እንዲህ በማለት አስነገሩ …
  ‹‹እግዚአብሄር በቸርነቱ  እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአ ብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡  ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም…››
* ዓድዋና የጦሩ ዝግጅት …
  የዓድዋው ጦርነት በጣልያኖች በኩል የቆየ የቀኝ ግዛት ጥማቸውን ለማሳካት ቀድሞ የተጠነሰሰ ነበር። በኢትዮጵያውያን ዘንድ ግን የጦርነት ዝግጅቱ እስከ ሰባት ወር የፈጀ እንደነበር ይነገራል። ዝግጅቱ ተጠናቆ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ጎህ ቀዶ እስኪጠልቅ በቀድሞዋ ትግራይ ጠቅላይ ግዛት በዛሬዋ ክልል አንድ ትግራይ ውስጥ በምትገኘው በዓድዋ ከተማ ይገጥም ዘንድ ቀኑ ደረሰ !  በዓድዋው ዘመቻ በመቶ ሺሕዎች ሆኖ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኛው ጦር፣ ሰይፍ፣ ጋሻና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ይዞ እንደ ነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።  ጣሊያን በአስር ሽዎች የሰው ሃይል ፣ በዘመናዊ የጦር መሳሪያና በወታደራዊ ሳይንስ የሰለጠነ አውሮፓዊ ጦር ነበርና ከፍ ባለ ስንቅና ትጥቅ ተደግፎ ወረራ መጀመሩ ይጠቀሳል።
* አንጸባራቂው የዓድዋ ድል  … የጥቁሮች ድል !
      የጣሊያን ጦር  በጄኔራል ባራቴሪ እየተመራ ባህር ተሻግረሮ ሲመጣ የተወረረችው የኢትዮጵያውያን ጦር የሚመራው በንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ነበር።  ጀግና ብልህና አርቆ አስተዋይዋ ባለቤታቸው እትየ ጣይቱ ብጡል በዚያ ባልሰለጠነ ዘመን ስልጡን ነበሩና በባለቤታች ከሚመራው የአርበኞች ግንባር እኩል  ተሰልፈው ሃገሬውን ስንቅ ትጥቅ በማስታጠቅና በማበረታታት የከፈሉት መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም። ኢትዮጵያውያን በንጉሱ ብልህ አመራርና ክተት ብለው በህብረት ተነሱ ። ከሽኩቻና ዝብሪት ተዘፍቀው የባጁት የየግዛቱ ሹሞች እና የጦር አበጋዞችም በንጉሰ ነገስት አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ ልዩነታቸውን አስወግደው በህብረት ተመሙ  !
       የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከ118 ዓመታት በፊት በዕለተ ሰንበት ክብሩ የተነካው አርበኛ ህዝብ ዓድዋ ላይ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተንቀሳቅሶ ባካሔደው ውጊያ እብሪተኛውን ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ የጣሊያን ጦር ጋር ገጠመ ! ከማለዳ አንስቶ ጀንበር እስክታዘቀዝቅ ባለው ጊዜ የተካሄደው ጦርነት እልፍ አእላፍ መስዋዕት ሆነው በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት በዓድዋ ተደመደመ  !
ጣሊያን ከአንባላጌ እስከ አድዋ ተጠራርጎ እንዲወጣ ያደረገው  ” የጥቁሮች ድል!” በሚል አለም ባወደሰው የዓድዋ ድል የጣሊያን መንግስት የሃፍረት ማቅን በግዱ ተከናነበ። የዓድዋ ድል በመላ በአለም ከተበሰረ በኋላ የወረራው መነሻ የሆነውን የውጫሌ ውል ፈርሶ የጣልያን መንግስት በውጫሌ ውል የነበረውን አጉል ምኞቱን ይሰርዝ ዘንድ ግድ ሆነበት ።  ወራሪው በሽንፈቱ አፍሮ የኢትዮጵያን ሙሉ ነፃነት አውቆ እና ተቀብሎ የሰላም ስምምነት ያደርግ ዘንድ ተገደደ !  የስምምነት ውሉም ለአለም መንግስታት ተሰራጨ። ውሉ የደረሳቸው መንግስታት እና ሃገራት የኢትዮጵያን የተረጋገጠ ሉአላዊ መንግስትነት በውድም ሆነ በግድ ተቀብለው አረጋገጡት !
* የዓድዋ ድል በዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ድብዳቤዎች  …
   ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ የዓድዋን ድል አስመልክተው ለፈረንሣዊው ሙሴ ሞንዶን የዛሬ 118 ዓመት የጻፉለት  የምሥራች ደብዳቤ እንዲህ ብለው ነበር “የምሥራች  በእግዚአብሔር  ቸርነት  የየካቲት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዕለት  ኢጣልያንን ድል አድርጌ መታሁት፡፡ በጨረቃ ሲገሰግስ አድሮ እሰፈሬ ድረስ መጥቶ ገጠመኝ፡፡  አምላከ ኃያላን ረድቶኝ ፈጀሁት፡፡ ደስ ብሎኛል  ደስ ይበልህ››
     አጤ ምኒሊክ በመጋቢት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. ለፈረንሳዊው ሙሴ ሸፍኔ በላኩለት ደብዳቤ ያቸው እንዲህ ብለዋል  ‹‹… ከአላጌ ጦርነት በኋላ፣ ጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያንም ደም በከንቱ አይፍሰስ፣ እርቅ ይሻላል ብላቸው እምቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግ ተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም፡፡ ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን…፡፡›› በማለት ያስታወቁ ሲሆን ምኒልክ ለሞስኮብ ንጉሥ ኒቆላዎስም መጋቢት 23 ቀን 1988 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤያቸውም ‹‹እንደ አውሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቀኝ፣ እንደ ወምበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ ሲነጋ ግምባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ጀመረ፡፡ ጥንት ከአህዛብና ከአረመኔ አገራችን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከእኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረግሁት…››  ብለው መጻፋቸው ይጠቀሳል ፡፡
* አልፋና ኦሜጋ የማይረሳው መስዋዕትነት   … አልፋና ኦሜጋ በክብር ይዘከራል  !
ልክ የዛሬ 118 ኛ አመት እሁድ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓም ታላቁ የዓድዋ ድል በዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ ተበሰረ !  ይህ የጥቁር ህዝብ በቅኝ ገዥዎች ከተቀዳጃቸው የዓድዋ ድል እውን እንዲሆን አቀበት የወጡ ፣ ቁልቁለት የወረዱ ፣እርጥብ የጨሰባቸው ፣ ደረቅ የነደደባቸው ፣ ከቤታ ቸው የተፈናቀሉ ፣ የቆሰሉ ፣ የሞቱ ፣ መዳረሻቸው የጠፋ  ጀግኖቻችን አልፋና ኦሜጋ የማይረሳው መስዋዕትነት  ነው … ይህ አንጸባራቂ ድልም እነሆ አልፋና ኦሜጋ በክብር ይዘከራል  !
     ልክ የዛሬ 118 ዓመት ከዘመነው የፋሽሽት ጣሊያን ጦር እና ጦር ሰራዊት በላይ የጥቁር ህዝብ ብሔራዊ ክብርና ኩራት ልቀው የታዩበት  የጦርነት አውድማ ነው !  ዓድዋ  !
በዓድዋ ድል እንኮራለን ! የዓድዋን ድል በክብር እናዘክራለን  !
ክብር ለደሙ ለቆሰሉና በክብር ለሞቱ ሰማዕታት !
ክብር ለጀግኖቻች አርበኞቻችን  !
ከብር ለእምየ ምኒሊክ ! ክብር ለእቴጌ ጣይቱ !
ክብር ለኢትዮጵያ !
እንኳን ለታላቁ የዓድዋ የድል በአል አደረሳችሁ  !
የመረጃ ምንጮቸ  : 
* በታዋቂ የታሪክ አዋቂዎች ከተጻፉት የታሪክ መዛግብት፣
*ከአድዋው ጦርነት ዙሪያ ከቀረቡት የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ፣
* በተለያዩ በጊዜ ስለ ዓድዋ ድል ገድል ዙሪያ ከተጻፉ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሲሆን ለአንባብያን እንዲመች አድርጌ አቅርቤዋለሁ ።