Thursday, 13 March 2014

ሰንደቅ – የአውሮፓ ኅብረት መንግስትና ተቃዋሚዎችን እያነጋገረ ነው

March 13th, 2014
የፖለቲካ ምህዳር መስፋት፣
የ2007 ምርጫ፣ የታሳሪዎች ጉዳይ በአጀንዳነት ተነስቷል
በአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካና የኢትዮጵያ ቋሚ አምባሳደር የኢትዮጵያ መንግስትንና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እያነጋገረ ነው። የኅብረቱ ቋሚ አምባሳደር አማካኝነት መካሄድ የጀመረው ውይይት በሀገሪቱ የፖለቲካ መህዳር መስፋት፣ በ2007ቱ ምርጫ፣ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የታሰሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እንዲሁም በሀገሪቱ ስላለው የሰብአዊና የዴሞክራሲ መብቶች ዙርያ መሆኑ ታውቋል።
ባለፈው ዓመት የኅብረቱ ቋሚ አምባሳደር በመሆን የተሾሙት አምባሳደር ቻንታል ሔብሪች ኅብረቱን በመወከል በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የበለጠ የሚከበሩበትን ገንቢ አማራጭ እያፈላለጉ ነው። በዚህም የአምባሳደሯ እንቅስቃሴ መሠረት የካቲት 26 ቀን 2006 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በመገኘት ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር በመሆን በሀገሪቱ አጠቃላይ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ውይይት አካሂደዋል። አምባሳደሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ውይይት ካካሄዱ ከአምስት ቀናት በኋላ በሀገሪቱ ካሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ ከሆነው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር አባላት ጋር በጽ/ቤታቸው ውይይት አካሂደዋል።
በአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካና የኢትዮጵያ አምባሳደር ቻንታል ሔብሪች ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር በተወያዩበት ወቅት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ ዴሞክራሲያዊ ሕጋዊ መሠረት የተከተለ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ላይ ቢሆንም፤ የበለጠ መሻሻል በሚገባቸው ቀሪ ስራዎች መወያየታቸው መዘገቡ ይታወሳል። በተጨማሪም በመጪው ዓመት የሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ በሚሆንበት ጉዳይ ላይ መወያየታቸው አይዘነጋም።
በተመሳሳይ ባለፈው ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2006 ዓ.ም በአውሮፓ ኅብረት ጽ/ቤት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውና የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ከኅብረቱ አምባሳደር ቻንታል ሔብሪች እንዲሁም በአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድና የህንድ ውቅያኖስ ክፍል ኃላፊ ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱም በአጠቃላይ ፓርቲው እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴና “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነት” በሚለው የፓርቲው ክፍል ሁለት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ላይ ማብራሪያ መጠየቃቸውን፣ የገዢው ፓርቲ የመሬት ፖሊሲ በሀገሪቱ መሬት የጥያቄ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ጥያቄ በመሆኑ በጥቅሉ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጤናማ እንዳይሆንና መንግስታዊ የሙስና ሥርዓት እንዲጎለብት መደረጉን አርሦ አደሩም ከድህነት እንዳይወጣ በማድረግ ዋነኛ የዴሞክራሲ ማፈኛ መሆኑን ማስረዳታቸውን በውይይቱ የተሳተፉት አቶ ሀብታሙ አያሌው ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልፀዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በእስር ስለሚገኙ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች የፓርቲው አመራሮችን በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን፣ አቶ አስራት ጣሴ ስለታሰሩበት ምክንያት፣ ምርጫ 2007 ላይ ፓርቲው ስላለው አቋም፣ በኢትዮጵያ የመብት ጥሰቱ በምን ደረጃ ላይ እንዳለና በስቴት ዲፓርትመንት ሪፖርት፣ የሚዲያ ሞኖፖሊና የግል ፕሬሱ ወዳከም ጋር የተያያዙ ችግሮች ዙሪያ ውይይት ማካሄዱን ከአቶ ሀብታሙ ገለፃ መረዳት ተችሏል።
በመጪው ሚያዚያ ወር ብራስልስ ላይ የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት በሚያካሂዱት የግራ ስብሰባ ላይ የአንድነት ፓርቲ ተወካይ ተገኝቶ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ንግግር እንዲያደርግ ጥያቄ መቅረቡንም አቶ ሀብታሙ አያይዘው ገልፀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በገዢው ፓርቲ እና በተቃዋሚዎች መካከል ገንቢ ውይይት ተደርጎ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ከፍ ማድረግ አለበት ያሉት አቶ ሀብታሙ፣ ይህ ካልሆነ ግን በምስራቅ አፍሪካ አደገኛ ወደሆነ የፖለቲካ አለመረጋጋት ሊፈጠር እንደሚችል ገልፀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ሰፊ የልማት፣ የቴክኒክ ድጋፎች እንደሚያደርግ ይታወቃል። በምትኩ ሀገራቱ የዜጎቻቸውን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲያከብሩ ከፍተኛ ግፊት ያደርጋል። ኢትዮጵያም የሎሜ ኮንቬንሽንን እ.ኤ.አ በ1975 ዓ.ም ከፈረመች ጊዜ አንስቶ ከኅብረቱ ጋር የልማት ትብብር መስርታለች፤ ኅብረቱም በአውሮፓ የልማት ፈንድ (European Development Fund) (EDF) እገዛ ያደርጋል። በተለይ በትራንስፖርት፣ በገጠር ልማት፣ ባልተማከለ የማኅበራዊ አገልግሎት ድጋፍ፣ በንግድ፣ በጾታ በሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እና በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ሀገሪቱን ይደግፋል። የድጋፍ መጠኑም በቅርቡም ወደ 600 ሚሊዬን ፓውንድ ይደርሳል።
አዲሲቷ የኅብረቱ ቋሚ አምባሳደር በመንግስትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የተካረረውን ግንኙነት በማለዘብና ወደ ገንቢ ውይይት እንዲመጡ ማበረታታታቸው በበጎ ዓይን እየታየላቸው ነው። አምባሳደር ቻንታል ባለፈው ዓመት የሹመት ደብዳቤአቸውን ከማስገባታቸው በፊት በአውሮፓዊቷ ኪርጊስታን ሀገር የኅብረቱ ቋሚ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። የቤልጂየም ተወላጅ የሆኑት አምባሳደር ቻንታል በኢትዮጵያ የኅብረቱ ቋሚ አምባሳደር የነበሩትና ባለፈው ግንቦት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የሀገራቸውን ልጅ አምባሳደር ቫቪየር ማርሻልን ተክተው ወደ ኢትዮጰያ መምጣታቸው ይታወሳል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምርጫ 2007 ያላቸው ብቃትና ዝግጅትን በተመለከተ ከሰንደቅ የተወሰደ

March 13th, 2014
አንድነት ን በተመለከተ
=============
አንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ ወይም አንድነትን በተመለከተ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነቱ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩላቸው ተጠይቀው በቅድሚያ ፓርቲያቸው በምርጫ የሚያምን ፓርቲ እንደመሆኑ ሕዝቡ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተጠቃሚ መሆን አለበት ብሎ እንደሚያምን ገልፀዋል። ለ2007ቱም ምርጫ ፓርቲያቸው የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እያደረገ መሆኑን፣ የመጀመሪያው ፓርቲው የቆመለትን ፖሊሲ ለሕዝብ ለማቅረብ በሚመች መልኩ የአማራጭ ፖሊሲ ትንተና እየተሰራ መሆኑን፣ የፓርቲው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ክለሳም ከምርጫው እና ወቅቱ ከሚጠይቀው ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተብራርቶ ተዘጋጅቶ በቅርቡም ለሕዝቡ ለውይይት እንደሚቀርብና ጎን ለጎንም ማኒፌስቶ የሚያዘጋጅ ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።
የፓርቲውን ድርጅታዊ አቅም በማጎልበት በኩል አዲሱ የፓርቲው አመራር ከተመረጠ በኋላ በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ በመላ ሀገሪቱ 34 ጽ/ቤቶች ይከፍታል ያሉት አቶ ሀብታሙ በቅርቡም በአዳማ፣ በሻሸመኔ፣ በሐዋሳ፣ በአዴት እና በደብረ ማርቆስ ከተሞች ላይ አዳዲስ ጽ/ቤት ተከፍተዋል ብለዋል። በአዲስ አበባም የፓርቲው የአዲስ አበባ ም/ቤት መቋቋሙን የጠቀሱት ሕዝብ ግንኙነቱ የአዲስ አበባው ም/ቤት 138 መቀመጫ እንዲኖረው በማድረግ ለአዲስ አበባ አስተደደር አቻ ቁጥር ም/ቤት መቋቋሙን ገልፀዋል። ከ23 ወረዳዎች ስድስት አባላት ተወክለው ም/ቤቱ መሰየሙን አስረድተዋል። በተመሳሳይ 24 ወረዳዎች ተመሳሳይ ም/ቤቶች ተመስርተው ወደ ቀበሌ ደረጃ እየወረድን ነው ብለዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዳያስፖራው ተሳትፎ አግባብ ባለው ሁኔታ እንዲመራና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲሰፍን አዳዲስ የድጋፍ ቻፕተሮችን ይከፍታል ብለዋል። በቅርቡም የፓርቲው ልዑክ ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን አሜሪካ እንደሚያቀና ገልፀዋል።
ጎን ለጎን ከዲፕሎማሲው ማኅበረሰብ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ልዩ የመረጃ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ድረገፅ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል። በተያያዘም የምርጫ ሂደቱ አካል ነው ያሉት ፓርቲዎችን ወደ ውህደትና ትብብር የማምጣት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል። የፓርቲውንም ልሳን ወደ ሕትመት ለመመለስ የማተሚያ ማሽን ተገዝቶ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ሕትመት ይገባልም ብለዋል።
አንድነት ፓርቲ የቤት ስራውን ሳይሰራ በገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ ላይ ስንፍናውን አያላክክም የሚሉት አቶ ሀብታሙ ፓርቲያቸው ከወዲሁ የዕጩ ምልመላና ታዛቢዎችን ማደራጀት መጀመሩን ጠቅሰው ነገር ግን ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ምህዳሩን ማጨለሙን መቀጠሉ ግን ያሳስበናል ብለዋል። ገዢው ፓርቲ የአውራ ፓርቲ ሚናነቱን በመተው ወደ መድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲመጣ አሳስበዋል።
በቅርቡም የተጀመረው “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነት” የሚለውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ለማካሄድ በ14 ዋና ዋና ከተሞች እንዲሁም በሦስት ተጓዳኝ አነስተኛ ከተሞች የምናደርገው እንቅስቃሴ ከወዲሁ ለመግታት እንቅፋቶች እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚሁ ሕዝባዊ ንቅናቄ ላይ በአዲስ አበባ ሕዝባዊ ውይይት ለማድረግ በኢትዮጵያ ስብሰባ ማዕከልና በመብራት ኃይል አዳራሽ ሕዝባዊ ውይይት ለማድረግ ከፍተኛ ችግር ማጋጠሙን ጠቅሰዋል። ይህም የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብና የጉልበት ፖለቲካ መቀጠሉን ማሳያ ነው ብለዋል።
የሀገሪቱ ስርዓት በምርጫ መለወጥ አለበት የሚለውን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ አክብረው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሀብታሙ፤ ፓርቲያቸው ለምርጫው በሙሉ አቅሙ ተዘጋጅቶ ሲያበቃ ገዢው ፖርቲ አፈናውን ከቀጠለ በዓለም ላይ ያሉትን ከ150 በላይ የሰላማዊ ትግል ስልቶች አሙዋጦ እንደሚጠቀሙ ገልፀዋል። ገዢው ፓርቲ የአፈና ስርዓቱን ከቀጠለ በሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እናስገድዳለን ብለዋል። ይህንንም ከምርጫው ዝግጅት ጎን ለጎን ገዢው-ፓርቲ በሕገ-መንግስቱ በተቀመጠው መልኩ ስልጣን በምርጫ መያዝ ያለበት የሚለውን ድንጋጌ እየሻረ የአፈና ስልት የሚጠቀም ከሆነ ሕዝቡ እምቢ እንዲል በማድረግ የኢትዮጵያ አደባባዮች በሰላማዊ ታጋዮች እንዲሞሉ እናደርጋለን። ከዚህ ሁሉ በፊት ግን እኛ የውስጥ የቤት ስራችንን በመስራት ላይ ነን ብለዋል፡፡ በቀጣይ ሳምንት የኢህአዴግን ጨምሮ የሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የቅድመ-ምርጫ ዝግጅት ለመቃኘት እንሞክራለን።
መኢአድን በተመለከተ
=============
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትም (መኢአድ) በአሁኑ ወቅት በክልል፣ በዞንና በወረዳ ያሉ መዋቅሮቹን መልሶ የማጠናከር (revisit) ከማድረግ ባለፈ ለ2007ቱ ጠቅላላ ምርጫ የተለየ የምርጫ ሰትራቴጂ አለማዘጋጀቱን የገለፁት ደግሞ የፓርቲው ፕሬዚደንት አቶ አበባው መሐሪ ናቸው። አቶ አበባው እንደ ሌሎቹ የፓርቲ አመራሮች የቀጣዩ ዓመት ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት ሊለካ የሚችለው ገዢው ፓርቲ በሚከፍተውና በሚያጠበው የፖለቲካ ምህዳር ብቻ የተወሰነ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ አቶ አበባው ገለፃ፤ ፓርቲያቸው ሙሉ በሙሉ ወደ ምርጫ ሲገባ አባላቱ ከስራ እንዲፈናቀሉ፣ ገበሬዎችም መሬታቸውን የሚነጠቁበት ሁኔታ በመሆኑና በምርጫው ውስጥ ከሚደረገው የተሳትፎ ጥረት ጎን ለጎን አባላቱ ላይ የሚደርሰውን ማዋከብ ዋነኛውን የምርጫ ጊዜአቸውን እንደሚሻማ ነው ያስረዱት።
በአቶ አበባው እምነት፤ በምርጫው ጠንካራ ዝግጅት ለማድረግ በቅድሚያ የፖለቲካ ምህዳሩ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ አበባው፣ የፖለቲካ መድረክ ነፃ እስኪሆን ድረስ ሕዝቡን ለማንቀሳቀስ እንኳ አስቸጋሪ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
በአሁኑ ወቅት ተዋህዶ በጋራ የመስራት እና በክልል ያሉ መወቅሮችን የማጠናከር ስራ ጎን ለጎን እየተካሄደ እንደሆነ አቶ አበባው የጠቀሱ ሲሆን፤ የፓርቲው የምርጫ ማኒፌስቶ ወቅታዊ ከማድረግ ባለፈ በመሰረታዊነት የሚለወጥ አለመሆኑን ነው የገለፁት። ዋናው ችግር ምርጫው መምጣቱን ተከትሎ አባሎቻችን ላይ የሚደርሰው ማዋከብ ነው ብለዋል።
የ2007ቱ ጠቅላላ ምርጫ ሥርዓት የመለወጥ አቅም ይኖረዋል የሚል ግምት ለመያዝ ከወዲሁ አስቸጋሪ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበባው፤ የፖለቲካ ለውጥ ተለዋዋጭ በመሆኑ ጊዜውን መጠበቅ ነው ብለዋል። ለአሁኑ ግን ፓርቲያቸው ለምርጫው ሲል የተለየ ዝግጅች እያደረገ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ይልቁኑ ኢህአዴግ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከር ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት መክረዋል።
በአሁኑ ወቅት እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት ችግር፣ ሥራ አጥነትና ውስብስብ የሆነው የማኅበራዊ አገልግሎት ችግሮች ስር እየሰደዱ በመምጣታቸው የራሱ የኢህአዴግ ካድሬዎች በማጉረምረም ላይ መሆናቸውን አቶ አበባው አስረድተዋል። አሁን ካለው የተባባሰ ችግር አንፃር በ2007ቱ ምርጫ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ሊቀጥል የሚችለው ምርጫውን በዱላ ወይም በኃይል ከተጠቀመ ብቻ በመሆኑ ሁሉም ነገር በገዢው ፓርቲ እጅ ነው ብለዋል።
ኢዴፓን በተመለከተ
===========
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲ (አዴፓ) መድረክና ሌሎች ፓርቲዎች የሚያነሱዎቸውን አቤቱታዎች ያነሳል። አቤቱታዎቹን የሚያነሳባቸው የአገላለፅ መጠን (tone) እንደሌሎቹ ፓርቲዎች አይደለም። ይሄ ፓርቲ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ከሌሎች ተቃዋሚዎች ዘንድ የተአማኒነት ጥያቄ ስለሚነሳበት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከሰጠው ሕጋዊ እውቅና በተጨማሪ ከሌሎች ፓርቲዎች ዘንድ የፖለቲካ እውቅና ይፈልጋል።
የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ወጣት ኤርምያስ ባልከው የሚያረጋግጡትም ይሄንኑ ነው። ፓርቲያቸው በቅርቡ ጉባኤ አድርጎ አዲስ አመራር በመረጠበት ወቅት ጉባኤው ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል በ1997ቱ ምርጫ የተፈጠሩ ስህተቶችን በማረምና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአዴፓ የፖለቲካ እውቅና የሚሰጡ ከሆነ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁነት መኖሩን አስታውቀዋል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ፓርቲው ቀደም ሲል በየክልሉ የነበሩ መዋቅሮቹን ለማጠናከር በሰሜን፣ በምስራቅና በደቡብ የሀገሪቱ አንዳንድ ክፍሎች መጠነኛ እንቅስቃሴ ከማድረጉ ባለፈ፤ አንድ ዓመት ለቀረው የ2007 ምርጫ አመርቂ እንቅስቃሴ እያደረገ አለመሆኑን ከፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ገለፃ መረዳት ይቻላል። በቀጣይ ጊዜአት የ2007 ምርጫ ማኒፌስቶ ዝግጅትና የዕጩ ምልመላ ስራዎች ለማካሄድ ገና በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አቶ ኤርሚያስ ሳይገልፁ አላለፉም።
የ2007ቱ ጠቅላላ ምርጫ ስርዓትን የመለወጥ አቅም ይኖረዋል ብሎ ለመገመት አስቸጋሪ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኤርሚያስ ፓርቲያቸውን ግን ኅብረተሰቡ ውስጥ ካሉ ስር የሰደዱ ችግሮች አንፃር ሕዝቡ በገዢው ፓርቲ ላይ ካለው ቅሬታ አንፃር ጠንካራ ተፎካካሪ የመሆን እድል እንዳለው ገልፀዋል። ፓርቲው የመራጬን ልብ ለመግዛት የሚያዘጋጀው ማኒፌስቶ እንዳለውም አቶ ኤርሚያስ የጠቀሱ ሲሆን፤ በተለይ ፓርቲያቸው ኢህአዴግን ጨምሮ አዴፓ በሚሳተፍበት የጋራ መድረክን ደንብ በማሻሻል ጭምር በ2007 ምርጫ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።
ለምርጫው አጀንዳ የሚሆኑ በርካታ የኅብረተሰቡ ችግሮች መኖራቸውን ያወሱት አቶ ኤርሚያስ የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የኢኮኖሚ ጥያቄዎችና የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበር ጨምሮ በርካታ አጀንዳዎች ተዘርዝረው የሚቀርቡበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
መድረክን በተመለከተ
============
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የ2007ቱን ምርጫ በተመለከተም አመርቂ ዝግጅት እያካሄደ አይመስልም። የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባልና የሕዝብ ግንኙነት አባል አቶ ጥላሁን እንዳሻው ግን መድረክ “የዝግጅት ችግር የለበትም” ይላሉ። የመድረክ መሰረታዊ ችግር የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብና ዜጎችን አንድ ለአምስት የሚጠረንፈው የገዢው ፓርቲ “የምርጫ ሠራዊት” የምርጫ ስትራቴጂ ነው ብለዋል።
መድረክ እንደ መድረክ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ገዢው ፓርቲ ውጤታማ ሆኜበታለሁ የሚለውን “የምርጫ ሠራዊት” ስትራቴጂ ሊያስለውጥ ወይም ሊፈትን የሚችል አዲስ ስትራቴጂ ይዞ መቅረብ አልቻለም። ፓርቲው ምርጫው ሊካሄድ የአንድ ዓመት ጊዜ ያህል ቢቀረውም በፓርቲ ደረጃ የምርጫ ስትራቴጂና እቅድ አላዘጋጀም። ከዚህ ይልቅ አቶ ጥላሁን ቀደም ሲል ይነሱ የነበሩ አቤቱታዎችን አሁንም የማስተጋባትን ስልት ቅድሚያ የሰጡት ይመስላል። በአቶ ጥላሁን ገለፃ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና የተወዳዳሪነት መንፈስ እንዲኖረው ገዢው ፓርቲ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። የአቶ ጥላሁን አቤቱታ (Old Complain new election) እንደሚባለው የ2007ቱ ምርጫ በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ ለአምስተኛ ጊዜ ቢካሄድም ምርጫውን በተመለከተ መድረክ አዲስ ነገር መፍጠር እንዳልቻለ አመላካች ሆኗል። በመድረክ በኩል የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ እንደ ፓርቲ የቀየሰው ስልት እንደሌለም ከአቶ ጥላሁን ገለፃ መረዳት ይቻላል። በእሳቸው አገላለፅ ኢህአዴግ የዘጋውን የፖለቲካ ምህዳር ለማስከፈት ከፓርቲው ይልቅ በአግባቡ ያልተደራጀው ሕዝቡ እንዲወጣው የሚፈልጉ ይመስላል።
ከዚህ በተጨማሪ “የሕዝብ ድጋፍ ችግር የለብንም” የሚሉት አቶ ጥላሁን ሕዝብ መድረክን በደፈናው ይደግፋል ከማለታቸው ባለፈ የሚደግፋቸውን ሕዝብ በአግባቡ ስለማደራጀታቸው የሰጡት ማረጋገጫ የለም። መድረክ እንደ መድረክ ሕዝብን ከማደራጀት ይልቅ የብሶት ጋጋታ በገዢው ፓርቲ ላይ ከማጧጧፍ ባለፈ ጠንካራ ሕዝባዊ መደላደል የፈጠረ አይመስልም። የሕዝባዊነት መደላድል ለመፍጠር የሄደበት እርቀት ገዢውን ፓርቲ ለመውቀስ ከሄደበት እርቀት አንፃር ሊመጣጠን የቻለ አይመስልም። ገዢው ፓርቲ በስልጣኑ ለመቀጠል ሲል ይፈጥራቸዋል የሚባሉትን የአስተዳደር፣ የፖለቲካ የሕግና አልፎ አልፎ ሕገወጥ የኃይል እርምጃዎችን በማጋለጥ ብቻ የፖለቲካ ትግል ማድረጉ ውጤታማ እንደማያደርግ በቂ ግንዛቤ የተያዘ አይመስልም።
በ2007ቱ ምርጫ የአባይ ግድብ ለምርጫ ፍጆታ መዋል የለበትም ሲሉ አጠንክረው የተከራከሩት የመድረክ ተወካይ አቶ ጥላሁን ፣ ግድቡ የኢህአዴግ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን የባንዲራ ፕሮጀክት ነው ብለዋል። መድረክ በ2001 ባዘጋጀው ማኒፌስቶ ውስጥ አባይን እና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሾችን ለመገደብ አቅዶ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
መድረክ ከኢህአዴግ የሚለይባቸው ሌሎች የፖሊሲ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ዋነኛ አጀንዳው የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መክሸፉን፣ በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ በኅብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ያለው ጫና እንዲሁም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ማኅበራዊ ችግሮች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ አስከፊ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አጉልቶ እንደሚያወጣ ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ያሉትም የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ገቢና ጥቅም ጋር እየተገለፁ አለመምጣታቸው፤ በዚያው መጠን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እያስከተሉ መሆኑን ሕዝቡ እየተገነዘበ የመጣበት በመሆኑ የመድረክ ትኩረት በሕዝቡ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ ችግሮች ላይ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። ለሁሉም የምርጫ ሂደቱ ስኬታማና ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ግን ኢህአዴግ የዘጋውን የፖለቲካ በር ሲከፍት እና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ታማኝ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው ብለዋል። “ተዘግቷል” ያሉትን የፖለቲካ በር ለማስከፈት ግን ፓርቲያቸው የነደፈው ስልት እንደሌለ በደፈናው “ሕዝቡን ይዘን” ከማለት ባለፈ ምንም አይነት ዝግጅት እንደሌለ ከአጠቃላይ ገለፃቸው መገንዘብ ይቻላል።

በሐረር ክልል ሕዝብ ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት አንድነት በቸልታ አይመለከተውም!! – ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

የካቲት 30 ቀን 20006 ዓ.ም በታሪካዊቷ የሐረር ከተማ በጀጎል ሸዋበር በደረሰው ቃጠሎ እና ከዚያም በኋላ የክልሉ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ በዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱ የፓርቲያችንን አመራሮች፣ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ያሉ አባላትና ደጋፊዎችን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡
ምንም እንኳን የቃጠሎው መንስኤ ተጣርቶ ይፋ ያልተደረገ ቢሆንም በጀጎል ሸዋ በር እየደረሰ ያለው ተደጋጋሚ ቃጠሎ ድንገቴ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡ በተለይም በየካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም የተነሳውን ቃጠሎ በተገቢ ፍጥነት ለመቆጣጠር የክልሉ መንግስት ፍላጎት ያልታየበት መሆኑ፤ ይልቁንም ግሬደር መኪና አስጠግቶ ቦታውን ለማፅዳት መሞከሩ አጠያያቂ ነው፡፡

 የክልሉ መንግስት ቃጠሎውን ለመቆጣጠር ተገቢውን ሁሉ ባለማድረጉ የጉዳቱ ሰለባ የሆነው ህዝብ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበት ክፉኛ እንደ ተማረረ በዚሁ ምክንያትም ቁጣ ተቀስቅሶ ፖሊስ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱንም በክልሉ የሚገኙ የፓርቲያችን አመራሮች መረጃውን አድርሰውናል፡፡


UDJ-SEAL


በመሆኑም ፓርቲያችን የክልሉ መንግስት ትክክለኛው የቃጠሎ መንስኤ በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ፤ በማንኛውም ምክንያት ኃላፊነታቸውን በብቃት ያልተወጡ የመንግስት ኃላፊዎች በግልፅ ለተጠያቂነት እንዲቀርቡ፤ የክልሉ ፖሊስ በህዝቡ ላይ የወሰደው የኃይል እርምጃ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ይፋ እንዲደረግ፤ የክልሉ ፖሊስ በወሰደው የኃይል እርምጃ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ብዛትና የጉዳቱ መጠን በአስቸኳይ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ተገቢ ህክምና እና ካሳ እንዲከፈላቸው፤ ይህንን የፈጸሙ አካላትም ለፍርድ እንዲቀርቡ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡
በአንድነት ፓርቲ በኩል ይህንኑ በህዝብ ላይ የደረሰ ጉዳት ለማጣራትና ለመከታተል በስራ አስፈጻሚው አስቸኳይ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡ ግብረ ኃይሉ ወደ ቦታው በማቅናት ጉዳዩን ካጣራ በኋላ የደረሰበትን መረጃ እና በፓርቲያችን የሚወስደውን ተጨማሪ አቋም በተመለከተ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን፡፡