Monday, 3 February 2014

ሳልቫ ኪር እና ሬክ ማቻር ለደቡብ ሱዳን ቀውስ ተጠያቂዎች ናቸው – ኦባንግ ሜቶ

obang metho1

በቦዲና በኮንሶ ብሄረሰቦች መካከል በተነሳው ግጭት የ4 ሰዎች ህይወት አለፈ

ጥር ፳፮ (ሃያ ስድት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ግጭቱ የተከሰተው ባለፈው ሳምንት ሲሆን፣ ለግጭቱ መነሻ የሆነውም ኮንሶዎች ባጋጠማቸው የመሬት እጥረት ሳቢያ ወደ ቦዲዮች አካባቢ ሄደው በመስፈራቸው መሆኑን የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።
በግጭቱ ከሁለቱም ወገኖች 4 ሰዎች ሲሞቱ፣ 3 ኮንሶዎች እና አንድ ፖሊስ ቆስለዋል። 72 ቤቶችም እንዲሁ ተቃጥለዋል።
ከዚህ በፊት ሁለቱ ብሄረሰቦች በተደጋጋሚ ሲጋጩ ቆይተዋል። ቀደም ሲል መንግስት የኮንሶ ሰፋሪዎችን ወደ ቦዴ አካባቢ በመውሰድ ማስፈሩ በአካባቢው ለሚታየው ችግር መንስኤ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜ የፌደራል ፖሊስ ገብቶ አካባቢውን ተቆጣጥሮታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጅንካ መብራት ለረጅም ጊዜ በመቋረጡ ህብረተሰቡ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጧል። የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት በአራት ቀናት አንድ ጊዜ የሚመጣው መብራት፣ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ዳርጓቸዋል።

በርካታ የአዲስ አበባ ቤት ተመዝጋቢዎች ገንዘባቸውን ከባንክ እያወጡ ነው

ጥር ፳፮ (ሃያ ስድት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ለማዎቅ እንደተቻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውን የመኖሪያ ቤቶች ችግር በዘላቂነት ለማቃለል በሚል ከዚህ በፊት ከነበረው የ 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ልማት ፕሮግራም በተጨማሪ በአማራጭ የ 10/90 አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እና ለመለስተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው በ40/60 የቁጠባ ቤት ፕሮግራም መቅረጹን ተከትሎ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ተመዝግቦ ነበር።
ይሁን እንጅ በአሁኑ ወቅት እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራም ተሳታፊ ዜጎች ከፕሮግራሙ እየወጡ መሆኑ ታውቋል። ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ከ30 ሺ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ገንዘባቸውን ከባንክ አውጥተዋል።
ባንክ ቤቶች ከዚህ በፊት ለምዝገባ ስራ ሲጨናነቁ ከነበረው ባልተናነሰ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ የስራ ጫና ውስጥ እንዳሉና ለዚህ አገልግሎት ብቻ አንድ መስኮት ለመልቀቅ እንደተገደዱ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የ20 /80፣ የ10/90 እና የ40/60 ቤቶችን ለመገንባት ከገንዘብ እጥረት በተጨማሪ የቦታ እጥረት ማጋጠሙን ኢሳት የውስጥ መረጃዎችን በማሰባሰብ መዘገቡ ይታወሳል። በተለይም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን በአዲስ አበባ ታላቁ ካርታ ውስጥ ለማስገባት ፈቃደኛ ሆኖ ባለመገኘቱ የፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት አደጋ ውስጥ ወድቋል።
መንግስት ወደ 10 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከባንክ በመበደር ቤቶችን ለመስራት ቢያስብም፣ ንግድ ባንክ በርካታ የብድር አገልግሎቶችን በመሰረዝ ለማግኘት የቻለው 6 ቢሊዮን ብር ነው። መንግስት በተለይ 40 በ60ን ተግባራዊ ለማድረግ ያወጣው እቅድ ቅጅው ለኢሳት ደርሶአል። በዚህ እስካሁን ይፋ ባልተደረገው እቅድ የቤቶች ዋጋ ቀድሞ ከተያዘለት በእጥፍ ጨምሮ በግል ከሚሰሩ ቤቶችም ጋር ሲነጻጸር እጅግ ውድ ሆኖ ተግኝቷል።

ሰበር ዜና-የአንድነት ስራ አስፈፃሚ በዛሬው እለት ጥብቅ ውሳኔዎች አስተላለፈ

February 3, 2014
1. የአድዋ ድል በአልን በተመለከተ ከአረና ፓርቲ ጋር በአድዋ ለማክበር ጥያቄው ለፓርቲው እንዲቀርብ ወሰነ፡፡ በአድስ አበባ ከትብብር ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ፣ መኢአድ፣ መድረክና ለሌሎች ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር ለማክበር ከወዲሁ የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም እና ለፓርቲዎቹ በደብዳቤ ጥሪ እንዲያቀርብ ወሰነ፡፡Andenat Party UDJ
2. በመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ላይ በጠበቃ ተማም አባቡልጉ በኩል ፓርቲው የመሰረተው ክስ ለህዝብ ይፋ እንደረግ ወሰነ፡፡
3. የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ቁጥር ሁለት ፕሮጀክትን በመመርመር አፅድቆ ወደ ምክርቤቱ መራው፡፡
4. በብአዴን/ ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር በአቶ ዓለምነው መኮንን ተፈጸመ የተባለውን ድርጊት ለመቃወም በባሕር ዳር ከተማ ህዝባዊ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ በተጨማሪም በነገው እለት ከጥር 27 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ የብአዴኑን ከፍተኛ አመራር ድርጊት በመቃወም ግለሰቡ በአስቸኳይ ከፓርቲና ከመንግስት ኃላፊነቱ እንዲነሳ፤ እንዲሁም ለፍርድ እንዲቀርብ ለመጠየቅ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ያሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሳተፉበት “online” የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰብ ስርዓቱ በይፋ እንዲጀመር የወሰነ ሲሆን ገፁ በፓርቲው ልሳን እና በሌሎች ማህበራዊ ገፆች ከማለዳ ጀምሮ ይተዋወቃል፡፡