Friday, 31 January 2014

ህወሓት የፈሪዎችና የጨካኞች ስብሰብ መሆኑ አውቅ ነበረ::(አብርሃ ደስታ )

January 30, 2014                                          
በሌሎች ላይ የምትፈፅሙት ተግባር ሁሉ በራሳቹ ላይ እንደምትፈፅሙ (እንደሚፈፀም) አስቡ። በስልጣን ላይ ያለ ሁሉ በስልጣን አይኖርም። የስልጣን ዕድምያቹ በጣም አጪር መሆኑ እናንተም ታውቁታላቹ። በሰዎች ላይ ግፍ ስትፈፅሙ ሰዎች ይጠሏችኋል። በሰዎች ስትጠሉ የስልጣን ዕድምያቹ ያጥራል። እናንተ ያላቹ የህዝብ ድጋፍ ሳይሆን ጠመንጃ ነው። ጠመንጃ ስልጣን ለመያዝ ይረዳ እንደሆነ እንጂ በስልጣን ለመቆየት አያስችልም። ስለዚህ በጠመንጃ አፈሙዝ የስልጣን ዕድምያቹ ለማራዘም የምታደርጉት ጥረት ከንቱ ልፋት ነው። እናንተ ከስልጣን ወርዳቹ ስልጣን የህዝብ ሲሆን፣ ፍትሕ ሲነግስ፣ እኩልነት ሲሰፍን ለፈፀማችሁት ወንጀልና ላደረሳችሁት በደል በሕግ እንደምትጠየቁ አያጠራጥርም። በስልጣን የኖረ የለም። እንኳን አምባገነኖች ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶችም በስልጣን ኮረቻ ተቀምጠው ለዘላለም አይኖሩም።
ምናልባት እናንተ ምግባራችሁ አውቃቹ በህዝብ ስትተፉ ሀገር ለቃችሁ በመውጣት ለማምለጥ ትሞክሩ ይሆናል። ገንዘቡም አላቹ። ሁሉም ካድሬዎች (በሰዎች ላይ ግፍ እንዲፈፅሙ እየታዘዙ ያሉ የህወሓት አባላት) ግን እንደናንተ (እንደ ህወሓት መሪዎች) ከሀገር ወጥተው ለማምለጥ ዓቅሙ የላቸውም። ደግሞ ዓቅሙ ቢኖራቸውስ ለምን በሰሩት ጥፋት ከሀገራቸው ለመሰደድ ይወሰንባቸባል? የህወሓት ባለስልጣንናት ከስልጣን ወርደው በሀገራቸው በሰላም የሚኖሩበት ሁኔታ ለምን አያመቻቹም? ለምን መርሃቸውን ከ «ስልጣን ወይ ሞት» ወደ «ስልጣን ለህዝብ አስረክቦ በሀገር በሰላም መኖር» አይቀይሩም? ለካድሬዎቹስ አያስቡም እንዴ? የህወሓት ዕድሜኮ ትንሽ ነው። ህወሓት ሲሞት የህወሓት አባላትም ከህወሓት ድርጅት ጋር አብረው መሞት የለባቸውም። ህወሓትም ስልጣን ለህዝብ አስረክቦ ተቃዋሚ ፓርቲ ሁኖ መቀጠል ይችል የለ?! ዕድምያችሁ ከህወሓት ድርጅት ዕድሜ በላይ እንዲሆን አድርጉ።
እኛ ሰለማዊ ታጋዮች ነን። ያላቹ ሃብትና ጠመንጃ በመጠቀም እኛን መደብደብ፣ ማሳሰር፣ ማሰቃየት፣ መግደል ትችላላቹ። አምባገነን ስርዓት የሚችለው ነገር ቢኖር ሰው ማሳሰርና መግደል ነው። የዓላም አምባገነን መሪዎች በማሳሰርና በመግደል የስልጣን ዕድምያቸው ዘለአለማዊ ማድረግ ከቶ አይቻላቸውም። ዛሬ እኛን ብትደበድቡና ብትገድሉ ዕድምያቹ እያሳጠራቹ እንጂ እያሸነፋቹ አይደላችሁም። እኛ ብንገደል ሌላ ሰው አለ። ሁሉም ሰው መግደል አይቻልም። ምክንያቱም ሁሉም ሰው ከተገደለ ማንን ትጨቁናላቹ? የሚጨቆን ሰው ያስፈልጋችኋል። ሰው ጭቆና ሲበዛት በመሪዎቹ ላይ ያምፃል። እናም ትሸነፋላቹ። አምባገነን ተሸናፊ ነው። የማይሸነፍ ህዝብ ብቻ ነው። ምክንያቱም ህዝብ ለጭቆና አይነሳም። እኛን በማሰቃየት ሰለማዊ ትግሉ መግደል አይቻልም። ሰለማዊ ትግሉ በመግደል የሰዎች የነፃነት ጥያቄ መግደል አይቻልም። የሰዎች የነፃነት ጥያቄ በመግደል ሰዎችን ለዘላለም መጨቆን አይቻልም። ስለዚህ መሸነፋቹ አይቀርም።
የሰለማዊ ትግል በር ባትዘግቡን መልካም ነው። ምክንያቱም ደም መፋሰሱ፣ ጦርነቱ፣ መጠፋፋቱ አንፈልገውም። እኛ የምንፈልገው ሰላም ነው። መንገዳችንም ሰለማዊ ነው። የሰላም በር ሲዘጋብን እጆቻችንና እግሮቻችን አጣጥፈን እንቀመጣለን ማለት ግን አይደለም። አንድ በር ሲዘጋ ሌላ በር ማንኳኳታችን ግድ ነው። ነፃነት እንፈልጋለንና። «መታፈን ይብቃን!» ብለን ተነስተናል። ስለዚህ ትግላችን በምንም ዓይነት ስትራተጂ ማስቆም አይቻልም። የሚቻለው ስልጣን ለህዝብ ማስረከብ ነው። ዴሞክራሲ ማስፈን ነው። ገዢዎች በሐሳብ መከራከር ሳይችሉ ሲቀሩ ወደ ሀይል እርምጃ እንደሚወርዱ እናውቃለን። ሐይል መጠቀም የሽንፈት ምልክት ነው። ህወሓት የፈሪዎችና የጨካኞች ስብሰብ መሆኑ አውቅ ነበረ፤ ወደ ድንጋይ ውርወራ ፖለቲካ ይወርዳል የሚል ግምት ግን ፈፅሞ አልነበረኝም። መንግስት ወንጀልን መከላከል ሲገባው ወንጀል ፈፃሚ ሆነ። ህወሓት ዉስጧ መበስበሱ እየሸተተን ነው። ምናለ ድንጋይ ባለመወርወር ገመናችሁ ባታጋልጡ? ለማንኛውም አደብ ግዙ የምትሰሩትን እወቁ። በሃይል የሚሆን ነገር እንደሌለ ተረዱ። ካለፉ ስርዓታት ታሪክ ተማሩ። ህዝብ እያያቹ ነው።

ESAT Daily News Amsterdam Jan 31 2014 Ethiopia | ESAT Tube

ESAT Daily News Amsterdam Jan 31 2014 Ethiopia | ESAT Tube

በሀረማያ ዩኒቨርስቲ በርካታ ተማሪዎች በፖሊሶች ተደበደቡ

ጥር ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ማክሰኞ  የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ትናንት የዩኒቨርስቲ ግቢውን ለቀው በመውጣት ላይ በነበሩ  ተማሪዎች ላይ የፌደራል ፖሊስ በወሰደው እርምጃ  የአንዲት ተማሪ ጆሮ መቆረጡንና በርካታ ተማሪዎች እጆቻቸውና እግሮቻቸው መሰበሩን ተማሪዎችና የዩኒቨርስቲው መምህራን ለኢሳት ገልጸዋል።
ችግሩ የተፈጠረው የውሃ ኢንጂነሪንግር ተማሪዎች የትምህርት ዘርፍ ለውጥ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው። ዩኒቨርስቲው የትምህርት-ዘርፍ  ለውጥ እንደማያደርግ እና መማር የማይፈልጉ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣት እንደሚችሉ ማስታወቂያ መለጠፉን ተከትሎ፣ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው በሚወጡበት ጊዜ የፌደራል ፖሊሶች መንገድ ላይ በመጠበቅ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ደብደባ ፈጽመዋል።
በአሁኑ ጊዜ የውሃ ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ከግቢ እንዳይወጡ በፖሊሶች እየተጠበቁ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ የዩኒቨርስቲውን አስተዳደር ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የአማራው ክልል መሪ በአማራው ህዝብ ላይ ተሳለቁ

ጥር ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአማራ ክልል ም/ ፕሬዚዳንት እና የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን “የአማራው ህዝብ ሰንፋጭ የሆነ ትምክተኝነት የተጠናወተው በመሆኑ በቤንሻንጉልና በሌሎችም ቦታዎች ለመሰደዱ ምክንያት ሆኖታል” በማለት፣ ለብአዴን ነባርና አዳዲስ ካድሬዎች ተናግረዋል።
ካድሬዎቹ “የአማራው ህዝብ ለምን ይሰደዳል? ለምን በእየክልሉ ጥቃት ይደርስበታል? አማራውን ከጥቃት ለመከላከል ለምን ሙከራ አይደረግም በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ም/ል ፕሬዚዳንቱ የአማራው ህዝብ በቅድሚያ እንዳይሰደድ ለማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፣ ነገር ግን ከተሰደደ በሁዋላም ቢሆንም ሰንፋጭ የሆነውን ትምክህተኝነቱን በመተው ከሌላው ጋር ለመኖር መልመድ አለበት ብለዋል።
አማራው “በባዶ እግሩ እየሄደ የሚናገረው ንግግር ግን መርዝ ነው” ያሉት ምክትል አስተዳዳሪውና የብአዴን የጽህፈት ቤት ሃላፊው፣ ይሄ መርዝ ንግግሩ አንድ የሚያደርግ አይደለም ሲሉ አክለዋል።
ከኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ለመኖር አማራው  የትምክህት ለሃጩን ማራገፍ አለበት ያሉት አቶ አለምነው፣ ይሄ ለሃጭ ሳይራገፍ በጋራ መኖር አይቻልም ሲሉ ድምድመዋል።
ማንኛውም ስም ያወጣ ሙትቻ ፓርቲ ሁሉ መንገሻው አማራ ክልል ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ምክንያቱንም ሲገልጹ ትምክህትን እንደ ምግብ ስለሚመገበው ነው ብለዋል። ያንን ምግብ እየተመገበ እንደሚያቅራራም ገልጸዋል።
አንዳንድ የብአዴን አባላት የምክትል ፕሬዚዳንቱ ንግግር እጅግ እንዳበሳጫቸው ለኢሳት ተናግረዋል።
የብአዴን ካድሬዎች አንቀጽ 39 ለምን አይወጣም በማለት ላነሱት ጥያቄ፣ እኝሁ ፕሬዚዳንት ሲመልሱ አንቀጽ 39 ባይኖር ኖሮ ኢትዮጵያ  ደቡብ ሱዳን እንደሆነቸው ትሆን ነበር በማለት መልሰዋል ። አንቀጽ 39 በህዝቦች ዘንድ መተማመን መፍጠሩን፣ አቶ መለስ ዜናዊ በሞቱበት ጊዜ በገሃድ መታየቱን ም/ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል

ልፋ ያለው በሕልሙ ዳውላ ይሸከማል! ጠርናፊና ተጠርናፊ ,,,,,,,,,

January 31, 2014
መስፍን ወልደ ማርያም
ጥር 2006
ሰሞኑን እንደአዲስ ሆኖ የሚወራው ስለጥርነፋ ነው፤ ጥርነፋ ከዲያብሎስ ፋብሪካ የወጣ የክፋትና የጭቆና መሣሪያ ነው፤ ሰዎችን በመጨቆንና በማሰቃየት፣ ምቾትና እንቅልፍ በማሳጣት፣ ፍርሃትንና ስጋትን በማሰራጨት ሕዝብን ለጥ-ጸጥ አድርጎ ለመግዛት የሚፈልጉ ጠርናፊዎች፣ አምባ-ገነኖች፣ ጨቋኞች፣ አፋኞች፣ ዘራፊዎች፣ ወሮበሎች፣ ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ሕግ የማይገዛቸው፣ አምላካቸው አድርገው የሚያገለግሏቸው ሎሌዎችን በሆዳቸው ገዝተው የሚያሰልፉ ናቸው፤ እንኳን የገጠር ልጆችና አኛም የአዲስ አበባዎቹ መሰንከል ምን እንደሆነ እናውቃለን፤ እንስሳትን (በቅሎዎችንና አህዮችን፣ አንዳንዴ በገግና ፍየልም) የፊት እግር ከኋላ እግር ጋር በአጭር ገመድ እያሰሩ እንደልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ ነው፤ ሀብት በመሆናቸው ቢጠፉ ባለቤቶቹ ይጎዳሉ፤ ስለዚህ በየአካባቢያቸው ያለውን እየጋጡ ችለው እንዲኖሩ ለማድረግ ቀላሉ ዘዴ መሰንከል ነው፡፡Prof. Mesfin Woldemariam : is an Ethiopian Human Rights activist and philosopher
ለሰውም ቢሆን ዓላማውም ዘዴውም አንድ ነው፤ ልዩነቱ የሰው ልጅ እንቅስቃሴው አካላዊ ብቻ ሳይሆን አእምሮም መንፈስም ስላለው መሰንከሉ አካላዊ ብቻ አይሆንም፤ እንዳያስብ አእምሮውን ማፈን ግዴታ ይሆናል፤ ለአምባ ገነኖች ችግር የሚመጣው የሰዎች አእምሮ ሲያስብ ነው፤ ያሰበውንም መናገርና መጻፍ ሲጀምር ነው፤ ‹‹መጥፎ ሀሰብ››፣ ማለትም ለጨቋኞቹ የማይበጅ ጥሩ ሀሳብ በንግግር፣ በጽሑፍ፣ በራድዮና በቴሌቪዥን ቢተላላፍና ብዙ ሰዎች ቢሰሙት አገር ይረበሻል፤ ሰው ሁሉ ሽብርተኛ ይሆናል፤ አገዛዙ ሕዝቡን ለመሰንከል ብዙ ዘዴዎች አሉት፤ በስም ማጥፋት እንዳልከሰስ ዘዴዎቹን አልናገርም፤ ነገር ግነ ክፉ እንቅልፍ ይዞት የሄደ ካልሆነ በቀር የማያውቃቸው የለም፤ የማያውቅ ካለ በየቤቱ እየመጡ ይተዋወቁታል፡፡
ወያኔ የትግራይን ሕዝብ አንድ ለአሥር ጠርንፎ ከሃያ ዓመታት በኋላ ውሉ ጠፋበትና ጥርነፋው ላላ! የቂል ነገር ለትግራይ ያልተሳካውን ጥርነፋ በቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይም ለመዘርጋት አቅዷል ይባላል፤ የወያኔ መሪዎች በአዲስ አበባ ቤቶችን አፍርሰው መንገድ ከሠሩ በኋላ ባቡር ትዝ ሲላቸው መንገዱን አፍርሰው ሀዲድ ለመሥራት ይሞክራሉ፤ ጥርነፋ በትግራይ እንዳልሠራ እያዩ በቀሩት ክልሎች ያሉትን ሰዎች ለመጠርነፍ ይፈልጋሉ፤ ጭንቅላተቸው ውስጥ ያለው ምንድን ነው ያሰኛል፤ እንኳን እንዲህ መክሸፉ በተግባር እየታየ ይቅርና ማሰብ ለሚችል በሀሳብም ደረጃ የከሸፈ ነገር ነው፤ እንስሳትን መሰንከል ቀላል ነው፤ ጉልበትን በበለጠ ጉልበት ማሸነፍ ነው፤ መናገርን መሰንከል ግን አይቻልም፤ ምላሱ ቢቆረጥበትም ሰው ሌላ መንገድ ይፈልጋል፤ በደርግ ዘመን ከኤንሪኮ በር ላይ የማይጠፋ ወፍራም ድሪቶ የሚለብስ ዲዳ ሰው ነበር፤ አንዳንድ ቀን ያየውን ‹‹ሲያወራ›› አንዳንዶች ያስይዘናል በማለት ይሸሹት ነበር፤ ያያቸው ወታደሮች መሆናቸውን በራሱ ላይ መለዮ በእጁ ያሳይና ሹመታቸውን ደግሞ በትከሻው ወይም በክንዱ ላይ እያመለከተ ሰዎችን ጨረሷቸው ለማለት በእጁ አፉን ጥርግ ያደርጋል፤ እኛ እንደሰማነው ወታደሮቹም እየገባቸው በየጊዜው ይደበድቡት ነበር፡፡
ማሰብን መሰንከል ደግሞ ከመናገርን ወይም መጻፍን ከመሰንከል የበለጠ አስቸጋሪ ነው፤ ለኢጣልያ የገበረው ባንዳ ሁሉንም አየነው፤ አማኑኤል ደግ ነው፤ እያለ የኢጣልያኑን ቄሣር አሞገሰና በጊዜው በላበት፤ በኋላ የአጼ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ሲመለስና ሲቋቋም ባንዳው ተገልብጦ ኢየሱስ ክርስቶስን ማለቴ ነው አለ! ሰምና ወርቅ የሚባለው የተፈጠረው ሀሳብን የመግለጽ መሰንከልን ለማክሸፍ ነው፤ ማሰብን መሰንከል እስካልተቻለ ድረስ ሀሳብን መግለጽን መሰንከል አይቻልም፡፡
የሰንካዮችን ጭንቅላት አልፎ ሊሄድ የማይችል አንድ ታሪክ ደጋግሞ ያረጋገጠው ነገር አለ፤ ልፋ ያለው ዳውላ ይሸከማል፤ እንደሚባለው ጨቋኞችና አፋኞች እንደእንስሳ ለሆዳቸው ብቻ የሚገዙ ታማኝ አገልጋዮችን እየመለመሉ ዙሪያቸውን ያጥራሉ፤ ነገር ግን የሆዳሞቹ አገልጋዮች በሀሳብ ወረርሺኝ ሲመታና ሲነቃ አፋኞች ማሰብን ለመሰንከል ባለመቻላቸው የራሳቸው ታማኝ አገልጋዮች ይገለብጧቸዋል፤ ይህ የታሪክ እውነት ቢገባቸው ማሰብን መሰንከል መሞከሩ ቀርቶ ሀሳብን መግለጽንም ለመሰንከል አይሞክሩም ነበር፤ ምክንያቱም ማሰብ በሚቻልበትና ሀሳብን በነጻነት መግለጽ በሚቻልበት አገር ሀሳብ አይፈነዳም፤ ሀሳብ እንደሚፈነዳ፣ ከፈነዳም በኋላ እንደወረርሺኝ መንደር ሳይመርጥ፣ ጎሣ ሳይመርጥ፣ የቋንቋና የሃይማኖት ልዩነት ሳያግደው፣ ሀሳብ ብቻ ሊያግደው የሚፈልገውን ኃይል ሁሉ በዘዴ እያሽመደመደ ይንቀለቀላል፤ ይስፋፋል፡፡
አብርሃም ሊንከን አለ እንደሚባለው ‹ጥቂት ሰዎችን ሁልጊዜ ማታለል ይቻላል፤ ሁሉንም ሰው ለጥቂት ጊዜ ማታለል ያቻላል፤ ነገር ግን ሁሉንም ሰው ሁልጊዜ ማታለል አይቻልም፤› ለጥቂት ጊዜ የታለሉት ማታለልን ይማሩና ያታልላሉ! የተኙ መስለው ያሸልባሉ፤ የሚያለብሱ መስለው ያራቁታሉ፤ የሚያከብሩ መስለው ያዋርዳሉ፡፡
በመጨረሻም ተጠርናፊዎች ጠርናፊዎች ይሆኑና መክሸፍ ይቀጥላል! ጠርናፊም እስኪጠረነፍ ሌላ ነገር አላስተማረም፤ ተጠርናፊም ራሱን ከጥርነፋ እስኪያወጣ የተማረው ሌላ ነገር የለም፤ ማስረጃ ከተፈለገ ተቃዋሚ በሚባሉት ቡድኖች ውስጥ ሞልቶአል!!
መጨረሻም በኢጣልያ የአገዛዝ ዘመን አምስት ለአንድ ጥርነፋ ማለት አንድ ኢጣልያዊ ለአምስት አበሻ ማለት ይሆንና አንድ ጠርናፊና አምስት ተጠርናፊዎች በቋንቋና በባህል የማይግባቡ፣ በታሪክም ሆነ በማኅበረሰብ ኑሮ ዝምድና የሌላቸው፣ የወደፊቱም ሕይወታቸው በተረጋገጠ የበላይነትና የበታችነት ደረጃ የተወሰነ ስለሚሆን ጥርነፋው ትርጉም ያለው ሊመስል ይችላል፤ አምስት አበሻ ለአንድ አበሻ መጠርነፍ ግን በጠርናፊም ሆነ በተጠርናፊ በኩል ብርቱ የማሰብ ችግር (ከመንግሥተ ሰማያትም ቢሆን አመጣሃለሁ! ያለው ሰውዬ ዓይነት) ከሌለ በቀር ከንቱ ነው፤ በቀላሉ አንድ ለአምስት በማድረግ ዓላማውን መገልበጥ ይቻላል! አንድና አምስት ስድስት ነው፤ እንዲሁም አምስትና አንድ ስድስት ነው፤ ሁለትና አራት ስድስት ነው፤ ሦስትና ሦስትም ስድስት ነው፤ በነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ሰው የምንለው ማንን ነው? ከብት የምንለው ማንን ነው? ሁሉም ሰዎች ከሆኑ ጠርናፊና ተጠርናፊ አይኖርም፡፡

በጎንደር የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እና የቅስቀሳ ቡድን አባላት በፖሊስ ታሰሩ

January 30, 2014
ጥር 22/2006 (BlueParty Ethiopia)
እስካሁን 14 የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በጎንደር የታሰሩ ሲሆን ከታሰሩት ውስጥ አራት ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች ይገኙበታል፣
1. ጌታነሀ ባልቻ (የድርጅት ጉዳዮች ሃላፊ)
2. ብርሃኑ ተ/ያሬድ (የሀዝብ ግንኙነት)
3. ዮናታል ተስፋዬ (የወጣቶች ጉዳይ ሃላፊ)
4. ይድነቃቸው ከበደ (የህግ አማካሪ)
A protest call in Gonder, Ethiopia


ሁለት ሹፌሮች እና አንድ ፊልም አንሺም (Cameraman) ከታሳሪዎቹ ውስጥ ናቸው፣ በአሁኑ ስዓት ታሳሪዎቹ በወረዳ ሁለት ፖሊስ ጣብያ ሲገኙ ጌታነሀ ባልቻ (የድርጅት ጉዳዮች ሃላፊ) እና አግባው ሰጠኝ ወደ ጎንደር ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ተወስደዋል።
ጥር 25 2006 ዓ.ም. የኢትዮ ሱዳን ድንበር ማካለልን ህገወጥነት በተመለከተ በጎንደር መስቀል አደባባይ የሚደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ ከአዲስ አበባ የተጓዘው የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ ሉኡካን ቡድን በዛሬው እለት በጎንደር ከተማ በቅስቀሳ ላይ እንዳሉ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው ሲሆን ጎንደር የገባው ቡድን በጠቅላላ በእስር ላይ ይገኛል፡፡ የቅስቀሳው አባላት በጎንደር ከተማ እና በተለያዩ ቦታዎች ቅስቀሳውን እንደጀመሩ የፓሊስ አባላት ፈቃድ ስለሌላችሁ መቀስቀስ አትችሉም ያሏቸው ሲሆን አባላቱም በህጉ መሰረት ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ የሚጠበቅብን ስላልሆነ ለሚመለከተው አካል ያሳወቅን በመሆናችን ህጋዊዎች ነን በማለታቸው ፓሊስ በማዋከብና በመደብደብ ጎንደር ከተማ በሚገኘው ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ መጉላላትና እንግልት እያደረሱባቸው ይገኛል፡፡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችም ፖሊሶቹን ምን አደረጓችሁ በማለት እና ይህ ጉዳይ የኛም ጉዳይ ነው በማለት አባላቱን ከፖሊስ ለማስለቀቅ የተቻላቸውን ያደረጉ ሲሆን ፖሊስም ሐይል በመጨመር ህዝቡን በዱላ በማባረር የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እና የቅስቀሳ ቡድኑን እንዲሁም የጎንደር የፓርቲው መዋቅር አባላትን ጨምሮ አስረዋቸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎንደር ነዋሪ ህዝብ የፖሊስ ጣቢያውን በመክበብ የታሰሩት እንዲፈቱ እየጠየቀ ሲሆን ሰልፉ በተያዘለት ቀን እንዲደረግ ለማድረግ ሌላኛው የሉኡካን ቡድን ከአዲስ አበባ በዛሬው እለት መንቀሳቀሱ ታውቆአል፡፡