Friday, 11 April 2014

የህወሓት ስትራተጂ: –

ማስፈራራት – በጥቅም መደለል- ማግለል- ማስቀናት- ከጥቅም ማገድ- ስም ማጥፋት- በመጨረሻ መፍራትና መሸነፍ!
==================
የህወሓት ዓላማ ስልጣን ነው። ስትራተጂውም ከዓላማው ይመነጫል። ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚከተለው ስትራተጂ ሌሎች አማራጭ ፓርቲዎች በሐሳብና በተግባር በማሸነፍ (በልጦ በመገኘት) ሳይሆን አማራጭ ሐሳብ ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማዳከም ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለማዳከም የሚጠቀመው የመጀመርያ ስትራተጂ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ማስፈራራት ነው። የፓርቲ አባላትን በማስፈራራት አባልነታቸውን (ተቃውሞአቸውን) እንዲያቆሙ ተፅዕኖ ይደረጋል።
የማስፈራራት ስትራተጂ ካልሰራ (የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በህወሓት ፕሮፓጋንዳ ካልፈሩ) በጥቅም የመደለል ስትራተጂ ይከተላል። የተቃውሞ ፓርቲ አባልነታቸው አቁመው ለህወሓት ከሰሩ (ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እየሰለሉ ህወሓትን ካገለገሉ) ቁሳዊ ጥቅም እንደሚሰጣቸው ይነገራቸዋል። በመረጡት ቦታ መሬት ይሰጣቸዋል፤ የፈለጉትን ዓይነት አገልግሎት ያገኛሉ።
ይህንን በጥቅም የመደለል ስትራተጂ ካልሰራ (ድለላው ተቀባይነት ካላገኘ) የማግለል ስትራተጂ ይከተላል። ጓደኞችህን በማስፈራራት ካንተ (ፓርቲ አባል) እንዲርቁ ይደረጋል፤ ከማህበራዊ ህይወትህ ትገለላለህ። ብቸኝነት ተሰምቶህ ዓቋምህ ትቀይር እንደሆነ ለማየት ነው። መጀመርያ የደህንነት ሰዎች እየመጡ ጓደኞችህን ያስፈራራሉ። ከፈሩና ከተለዩህ ህወሓቶች ተሳካላቸው ማለት ነው። ካልፈሩ ደግሞ ቁሳዊ ጥቅም ይቀርብላቸውና አንተን በጥቅም የማስቀናት መንገድ ይከተላሉ። (ብዙ ጓደኞቼ ስለፈሩ ወደ ቁሳዊ ጥቅም የማግኘት ደረጃ ያልደረሱ አሉ፤ የተወሰኑ ግን በጣም ሃብታም ነጋዴዎች ሁነዋል፤ እንኳን ተጠቃሚ ሆኑ፤ ህሊና በቁስ ነገር መሸጥ መጨረሻው ፀፀት ቢሆንም)። በመጨረሻ አንተን ከሁሉ ዜግነታዊ ጥቅምና ሕጋዊ መንግስታዊ አገልግሎት ያግዱሃል። በዚህ ሁሉ ተፅዕኖ ካልተምበረከክ የደህንነት ሰዎች አሰማርተው ስምህ እንዲጠፋ የፈጠራ ወሬዎች ይነዛሉ። አሁን ካልተሸነፍክ ግን በቃ እነሱ ይፈሩሃል፤ ያከብሩሃል። በመጨረሻም እጃቸው ይሰጣሉ፤ ይምበረከካሉ። መሸነፋቸውን በገዛ አንደበታቸው ይመሰክራሉ።
ስለዚህ በግለሰብ ደረጃ ህወሓቶች ስትራተጂ: ማስፈራራት፣ በጥቅም መደለል፣ ማግለል፣ ማስቀናት፣ ከጥቅም ማገድ፣ ስም ማጥፋት ነው። በመጨረሻ መፍራትና መሸነፍ፤ ድል ያንተ ነው።
በፓርቲ ደረጃ: ተቃዋሚ ፓርቲዎች አማራጭ ሐሳባቸውን ለህዝብ እንዳያቀርቡ ይደረጋል። ስለነሱ መጥፎ ነገር ለህዝብ ይነገራል። ህዝብ ፖለቲካ እንዳያውቅ ይደረጋል፤ ምክንያቱም ህዝብ ፖለቲካ ካወቀ መብቱ ያውቃል። መብቱ ካወቀ ነፃነቱ ያውቃል። ነፃነቱ ካወቀ ዓፈና ይቃወማል። ዓፈና ከተቃወመ ዓፋኝ ስርዓትን ከስልጣን ያባርራል። ዓፋኝ ስርዓት ከስልጣን ከተባበረ ህወሓት ስልጣን ይለቃል። ምክንያቱም ህወሓት ዓፋኝ ስርዓት መሆኑ ይደረስበታል። ስለዚህ የህወሓት ጥረት ህዝብ እንዳያውቅ ማፈን ነው።
ለዚህም ነው የህወሓት ዋነኛ ስትራተጂ ህዝብን ማፈን የሆነው። ህዝብ ሲታፈን ዓፈናውን መጋለጥ አለበት። የህዝብ ዓፈና የሚያጋልጡ የግል ጋዜጠኞች ናቸው። ጋዜጠኞች በህዝቦች ላይ የሚደርስ ዓፈና በማጋለጥ የጋዜጠኝነት ግዴታቸውን ይወጣሉ። ህወሓት ዓፋኝ ስርዓት መሆኑ ስለሚያውቅ ህወሓት በህዝቦች ላይ የሚያደርሰውን ዓፈና ሊያጋልጡ የሚችሉ የግል ጋዜጠኞች በጥቅም ማማለልና መደለል ጀምሯል። በዚሁ መሰረት ብዙ የግል ጋዜጠኞች በመረጡት ከተማና ቦታ መሬት ይሰጣቸዋል። ለጋዜጠኞች መሬት የመስጠት ድርድር (ቅሌት) ተጀምሯል። በድርድሩ የተስማሙ ጋዜጠኞች መሬት ይሰጣቸዋል። እንደዉጤቱም በህዝቦች ላይ የሚደርስ ዓፈና ሳያጋልጡ ያፍናሉ። የዓፈና መረጃ ያፍናሉ ማለት ነው። ሙያቸው ይክዳሉ ማለት ነው። እስካሁን መሬት የተሰጣቸው ጋዜጠኞች አውቃለሁ። የተሟላ ስም ዝርዝር ከተወሰነ ግዜ በኋላ ይቀርባል።

በዚህ መንገድ ህወሓት በስልጣን የመቆየት ህልሙ ለማሳካት ጥረት እያደረገ ይገኛል። ህዝብን በማፈን ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይቻል ከደርግ ስርዓት መማር አለመቻሉ ያሳዝናል። በስልጣን ለመቆየት የሚረዳ የህዝብ ይሁንታ ነው። የህዝብ ይሁንታ የሚለካው በምርጫ ነው። ምርጫ የሚኖረው ደግሞ የህዝብ ነፃነት ሲኖር ነው። ህወሓት በደህንነት ሰዎቹ ላይ የተንጠለጠለ ህዝባዊ መሰረት የሌለው ዓፋኝ ስርዓት ሆነዋል። ከስር መሰረቱ እንደሚነቀል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

No comments:

Post a Comment