Friday, 16 May 2014

የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ክለላ ዛሬ በድብቅ ሊፈረም ነው!

May 16th, 2014       
የኢትዮ ሱዳን ዳር ድንበር በግልፅ የተከለለ እንዳልሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያ አርሶአደሮች የሚጠቀሙት መሬት የኢትዮጵያ እንደሆነ ሲወሰድ ሱዳናውያን የሚገለገሉበትም የሱዳን ነው ተብሎ ይታሰባል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የኢህአዴግ መንግስት ኢትዮጵያውያን አርሶአደሮችን ከቀያቸው እያፈናቀለ ለሱዳን ማስረከቡ ይታወቃል። ብዙ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች ተፈናቅለዋል፣ የተወሰኑ ተለዋጭ መሬት ሲሰጣቸው ምንም ያላገኙም አሉ።
ድንበሩ ብዙ ዉዝግብና ተቃውሞ ያለው ሲሆን የኢህአዴግ መንግስት ከሱዳኖች ጋር በመተባበር በድብቅ ለመከለል ተስማምቷል። እንዲህ ነው የተደረገው፥ በድንበሩ አከባቢ የሚገኙ ኗሪዎች (የኢትዮጵያና የሱዳን) ድንበራቸውን አይተው ክለላውን ይፈፅማሉ፣ ይፈራረማሉ። ለሱዳን የተሰጠው መሬት ታውቋል። ሁሉም ነገር በኢህአዴግና የሱዳን መንግስት አልቋል። አሁን “የሀገር ሽማግሌዎች” እንዲፈርሙ እየተደረገ ነው። የሀገር ሽማግሌዎች እንዲፈርሙ የተፈለገበት ምክንያት የድንበር ክለላ የተከናወነው በኗሪዎች ነው እንዲባል ነው። ለሌላ ግዜም ምስክር ሁነው እንዲቀርቡ ነው።
በዚህ መሰረት በድንበሩ አከባቢ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ከተሞች ማይካድራና በረከት የተወሰኑ ሰዎች በካድሬዎች ተመርጠው “ኮሚቴ” ተሰኝተው ዛሬ ግንቦት 8, 2006 ዓም እንዲፈርሙ ወደ ሱዳን ድንበር ተጉዘዋል። እነዚህ ኮሚቴ ተብለው የተመረጡ ሰዎች ስለ ድንበሩ ይሁን አከባቢው እውቀት የሌላቸው፣ የአከባቢው ኗሪዎች ሳይሆኑ በቅርብ ግዜ ባከባቢው መሬት የተሰጣቸው ሰፈርተኞች ናቸው። ዕድሜየቸውም ከአርባ በታች ነው፣ ትምህርት የላቸውም፣ የድንበሩ ታሪክ አያውቁም፣ መሬት ስለተሰጣቸውና በካድሬዎች ስለታዘዙ ብቻ ሊፈርሙ የሚችሉ ናቸው። ስለዚህ የሀገር ሽማግሌዎች ሊባሉ አይችሉም። ምክንያቱም ሰፈርተኞች እንጂ ኗሪዎች አይደሉም፣ ወጣቶች ናቸው (ድንበሩ ላያውቁት ይችላሉ)፣ ትምህርት የላቸውም (የድንበር ጉዳይ ምን ያህል ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እንደሆነ ላይረዱ ይችላሉ) ወዘተ። ዛሬ እንዲፈርሙ የተወሰዱት በድብቅ መሆኑ ነው።
የድንበር ጉዳይና ሌሎች የሑመራ አከባቢ ኗሪዎች በማየሉ ተቃውሞ እየተቀሰቀሰ በመሆኑ ባከባቢው ተገኝቶ መረጃ ማሰባሰብ አስቸጋሪ እየሆነ ነው። የመንግስት አካላት ኗሪዎች ለሌሎች አካላት መረጃ እንዳይሰጡ እያስፈራሩ ነው። መረጃ መሰብሰብም አይፈቀድም። በዚሁ አጋጣሚ ግርማይ ወልደግዮርግስ የተባለ የድምፂ ወያነ ሬድዮ ጋዜጠኛ ባስተዳዳሪዎች ከቀረቡለት አራት ካድሬዎች ዉጭ ሌሎች ኗሪዎችን በማነጋገሩ ምክንያት ባለስልጣናት ፖሊስ ጠርተው አስረውታል። የድምፂ ወያነ ሬድዮ ጋዜጠኛ ህዝብን ሳንፈቅድልህ አገጋግረሃል ተብሎ ነው የታሰረው።
በሑመራ አከባቢ ብዙ ተደራራቢ ችግሮች አሉ። ሕገወጥ የመሬት ሽንሸና እየተደረገ ነው። ኗሪዎችን ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ስርዓቱ ያገለግላሉ ለተባሉ ሰዎች መሬት እየተሰጠ ይገኛል። ለምሳሌ አቶ ካሕሳይ ገብረሚካኤል የተባሉ ያከባቢው ኗሪ መሬታቸው ተወስዶ ለሌላ የህወሓት ካድሬ ዉሽማ ተሰጥቷል። ፍትሐዊ ያልሆነ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል።
በድንበሩ ጉዳይ በድብቅ እየተፈረመ ያለው ነገር ተቀባይነት የለውም። ለሱዳን የሚሰጥ መሬት መኖር የለበትም። ተግባሩ ሕገወጥ ነው። ኢህአዴግም ለተግባሩ ይጠየቃል።SUDAN

ዝክር ለግንቦት 7 1997 እና ለግንቦት 7 ቀን 2000 ዓ.ም

May 16, 2014
ዘንድሮ፣ የታሪካዊው ግንቦት 7 ቀን 1997 አገር ዓቀፍ ምርጫ ዘጠነኛ ዓመት እና ንቅናቄዓችን የተመሠረተበት ስድስተኛ ዓመት የምንዘክረው ከመችውም በላይ አገራችን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ሁና ነው። ወያኔ የማይገዛትን አገር እንዳትኖር ለማድረግ እማትወጣው አረንቋ ውስጥ ከመክተት የማይመለስ ኃይል መሆኑን ዛሬ በአምቦ፣ በጉደር፣ በጊምቢ እና መሰል ቦታዎች በተግባር እያስመሰከረ ነው።Ginbot 7 logo
የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ፍላጎቱን የመግለጽ አንፃራዊ ነፃነት አግኝቶ የነበረበት የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. ምርጫን ስናስብ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ መመዘናችን አይቀርም። ያኔ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ እጁ መዳፍ ቀርባ ትታየው የነበረችው ድል እስከዛሬ አልጨበጣትም። ትግሉ ግን ቀጥሏል። የዛሬው ትግላችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከያኔው በበለጠ ከታሪክና ከራስዋ ጋር የታረቀች አገር የመመሥረትን ርዕይ አስፈላጊነት ላይ ትኩረት መስጠትን የሚጠይቅ ሆኗል።
ወያኔ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ለአለፉት አርባ ዓመታት ሲያብላላው የቆየው፤ በመንግሥት ሥልጣን በቆየባቸው ሃያ ሶስት ዓመታት ውስጥ ደግሞ በፓሊሲ ደረጃ ሲያስፈጽመው የቆየውን የዘር ፓለቲካ አስከፊ ውጤት አሁን እየታየ ነው። ይህ የዘር ፓለቲካ ራሱ ወያኔን ያጠፋዋል። ችግሩ ግን የዘር ፓለቲካ ወያኔን ነጥሎ አያጠፋም፤ ከወያኔ ጋር አገራችንንም ሊያጠፋ ይችላል። ከሁሉም በላይ አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ የዘር ፓለቲካ የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። በጎረቤት አገራት ውስጥ ያየነውን ዓይነት የእርስ በርስ እልቂት ወደ አገራችን ለማምጣት ህወሓትና ኦህዴድ ተግተው እየሠሩ ነው። ሌሎች የወያኔ ተቀጥላ ድርጅቶችም የዚህ ትልቅ የጥፋት ፕሮጀክት አካል ናቸው።
የግንቦት 7 1997ቱ ብሩህ ተስፋ በፋሺስቱ ወያኔ የግፍ አፈና ሲጨልም፤ ያ ተስፋ እንዲያንሠራራ በግንቦት 7 2000 ዓ.ም. የተቋቋመው ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዛሬ የኢትዮጵያን ተስፋ ለማጨለም ከተነሱ ኃይሎች በተፃራሪ በመቆም የሕዝብና የአገር አለኝታነቱ ማረጋገጥ ይኖርበታል።
በዚህም ምክንያት፣ በዚህ ወሳኝ ወቅት የግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች የሆንን ሁሉ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ ይኖርብናል። በግራም ይሁን በቀኝ ያለ ጽንፈኝነት አገራችን አይጠቅምም፤ የምንመኛትን ኢትዮጵያ አያመጣልንም። ሕዝባችንና አገራችንን ከዚህ አረንቋ ማውጣት የሚቻለው የአንድነትና የእኩልነት ፓለቲካን አሸናፊ ማድረግ ስንችል ነው።
በአሁኑ የኢትዮጵያ ፓለቲካ ለሀገራችን የሚጠቅማትና ትክክለኛ ነው ብለን የምናምነው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚታገል፤ የተለያዩ የኅብረሰተሰብ ክፍሎች በመሰላቸው መንገድ ለመደራጀት መብታቸው እውቅና የሚሰጥ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ማኅበረሰቦች በሙሉ በእኩልነት የሚስተናገዱበት ሥርዓትን የሚያልም፤ መሰማማት፣ መቻቻል እና ከዚያም አልፎ መተጋገዝ ያለበት የኢኮኖሚና የፓለቲካ ሥርዓት እንዲኖር የሚታገል፤ የእምነቶች እኩልነትን የሚያከብር፤ በታሪክ ውስጥ የተፈፀሙ በደሎችን መርምሮ ማኅበራዊ እርቅ ለመፍጠር ፍላጎት ያለው ፓለቲካ ነው።
ይህ ዓይነቱ የአንድነትና የእኩልነት ፓለቲካ በአሸናፊነት እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል ብሎ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ያምናል። ይህ ለሁላችንም የሚበጀው ፓለቲካ አሸናፊ ለማድረግ የሚከተሉትን መፈፀም ይጠበቅብናል።
በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ የሚደርስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በፍጹም የማንታገስ መሆኑን ማመንና በተግባሮቻችንም ይህንኑ መግለጽ፤
ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር መውጫው መንገድ ወያኔን ማስወገድና በምትኩ የዜጎችን እኩልነት የሚያረጋግጥ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያስታርቅና የሚያስተሳስር መንግሥት መመሥረት መሆኑን ማመንና በተግባሮቻችን ማሳየት፤
የኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላቶች ወያኔ እና ተቀጥላዎቹ፣ በተለይም ህወሓት፣ ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ደህዴድ መሆናቸውን በማመን ትኩረታችንን ነቀሎ ወደሌላ ከሚወስዱ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች መቆጠብ፤
በብሔር ከተደራጁ ኃይሎች ጋር በሚለያዩን ነገሮች ላይ ሳይሆን በሚያስተባብሩን ጉዳዮች ላይ በማተኮር የወያኔን የከፋፍለህ ግዛ አጀንዳ ማክሸፍ፤
በስሜትከተሞሉ የአጭር ጊዜ እይታዎች ለእርስ በርስ ግጭቶች ከሚዳርጉ አስተሳሰቦችና ተግባራት መቆጠብ፤ እና
አርቆ አስተዋይነትና ታጋሽነት በተላበሰ መንገድ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ደህንነት፣ለፍትህና ለነፃነት በግንባር ቀደምትነት መቆም፤
የግንቦት 7 ንቅናቄ አባላትና ደጋፊዎች ከላይ የተዘረዘሩትን ለመፈጸም የሚቻለንን ሁሉ ለማድረግ ያለንን ዝግጁነት እየገለጽን፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔና ግብር አበሮቹ ከፊቱ የደቀኑበትን ከፍተኛ አደጋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተባብሮ እንዲያስወግድ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪውን ያቀርባል።
አስቸጋሪ ወቅት ላይ የምንገኝ ቢሆንም እንኳን በርትተን ከታገልን የተረጋጋች፣ ዲሞክራሲያዊ ሉዓላዊ አገር – ኢትዮጵያ – ይኖረናል። ለዚህ ውጤት በርትተን እንታገል።
ክብር የግንቦት 7 1997 ሀገራዊ ተስፋን እውን ለማድረግ ለወደቁ ሰማዕታት!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!