Friday, 23 May 2014

የአረና አመራሮች በአዳራሽ ውስጥ ታግተዋል – ፍኖተ ነጻነት

May 23rd, 2014
አረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ በዛሬው ዕለት በሀውዜን ከተማ ከ3፡00 ሰዓት ጀምሮ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንዳለ ከመቀሌ የመጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ደርሰው እኛ ሰላማዊ ሰልፍ ስለምናደርግ ስብሰባ የሚባል ነገር የለም በማለት ወደ አዳራሹ የሚመጣውን ሰው ድንጋይ በመወርወር ስብሰባው እንዳይካሄድ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ስብሰባውን እንዲታደም ሲቀሰቅሱ የነበሩ አንድ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና ሁለት አባላት ታርጋ በሌላቸው ሞተር ሳይክሎች በመግጨት አደጋ አድርሰውባቸዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት አዳራሹ ውስጥ ተዘግቶብን ዙሪያውን ተከበናል ፖሊስ መቆጣጠር ስላልቻለ ተጨማሪ ኃይል ጠይቋል ሲሉ የአረና አመራር ለፍኖተ ነፃነት ገልጸዋል፡፡ ከአሁን ቀደም በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የትውልድ ስፍራ ወላይታ ከተማ በተደራጁ ሰዎች ዝርፊያና ታርጋ በሌላቸው ሞተር ሳይክሎች አደጋ ለማድረስ መሞከራቸውን ፍኖተ ነፃነት መዘገቧ የሚታወስ ነው፡፡arena-structure

የአዳማው የአንድነት ሰልፍ ለሰኔ አንድ ተላለፈ

May 23rd, 2014
ኑና አብረን ድምጻችንን እናሰማ!!
የአንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የመሀል ቀጠና ፅ/ቤት ለግንቦት 10 ጠይቆትየነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በገዢው ፓርቲ የተለያዩ ሰበቦችና ምክንያቶች ሲድበሰበስ ከርሞ ለሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም መተላለፉን የመሀል ቀጠና ጽ/ቤቱ በጠራው የአስቸኳይ ስብሰባ መወሰኑንናይህንኑ ውሳኔውንም በቀን መወሰኛ ደብዳቤው ላይ ገልጾ ለአዳማ መስተዳድር ከንቲባ አቶ አብረሐም ማስረከቡን በመረጃ አያይዞ ገልጧል፡፡በመሆኑም ሰኔ አንድ የአንድነት ደጋፊዎችና አባላት እንዲሁም የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች የሆናችሁ ነጋዴዎች፣ተማሪዎችና ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በሰልፋችን ላይ በመገኘት በገዢው ፓርቲ ላይ የተባበረ የተቃውሞ ድምጻችንን በሰላማዊ የትግል ስልት መንፈስ እንድናሰማ ጋብዘናችኋል፡፡ ሰኔ አንድ አይቀርም!
መነሻችን 4፡00ሰዓት ፣አዳማ ራስ ሆቴል (የቀድሞው መነን ሆቴል) ሆኖ፣ በፍራንኮ ሆቴል አርገን ወደ ምንጃር ጎዳና እንወጣና፤ ከሳር ተራ በአዲሱ ግንብ ገበያ ወደ መብራት ሐይል አቅንተን፤ ቁልቁል በአንደኛ መንገድ (ግርማሜ ነዋይ ጎዳና) ከደራርቱ አደባባይ ፊት ለፊት ካለው የፖስታ ቤት ሜዳ ላይ ማሳረጊያ እናደርጋለን፡፡ በጳጉሜ ሶስት የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት የሁለተኛ ዙር ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ የሚሊየኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነት በሚል መሪ ቃል ላይ ተመስርተን በሀገሪቱ ስላለው ኢፍሀዊ የመሬት ስሪት እንጮሀለን! በመልካም አስተዳደር ዕጦት ስለሚደረጉ የሙስና ወንጀሎች የተቃውሞ ድምጽ እናሰማለን!-ኑ ኑና አብረን ድምጻችንን እናሰማ!!10305607_726441860747899_1605322284415562929_n

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ባለቤት ናት?

May 23, 2014
ኪዳኔ ዓለማየሁ
መግቢያ፤
በጥንቱ ዘመን፤ የአባይ ወንዝ ዋናዋ ምንጭ ኢትዮጵያ መሆኗና ባለቤትነቱዋ ታውቆ፤ የግብጽ መሪዎች በየዓመቱ ለሚጎርፍላቸው ውሀ ይከፍሉ ነበር። ባሁኑ ጊዜ ግን፤ በተለይ ግብጽ የአባይን ወንዝ እንደ ግል ንብረቷ በመቁጠር ኢትዮጵያ በገዛ ወንዟ ለመጠቀም የምታከናውነውን ጥረት መቃወም ብቻ ሳይሆን ማስፈራራትም ይቃጣታል።
እንደሚታወቀው፤ ሰሞኑን በየድህረ-ገጹ በስፋት ከሚቀርቡት ሐተታዎች፤ ትችቶችና አስተያየቶች ውስጥ ሰፊ ስፍራ ይዞ የሚገኘው በኢትዮጵያ በመገንባት ስላለው ታላቅ የአባይ ግድብ ነው። ስለ ግድቡ የተንጸባረቁት የተለያዩ አስተያየቶች እንዳሉ ሆነው፤ የአባይ ወንዝ ባለቤትነት የማን እንደ ሆነ፤ ውሱን በሆነ መንገድ ተነካ እንጂ በጥልቀት በተከናወነ ምርመራና በዓለም-አቀፍ ሕግ ላይ በተመሠረተ አስተማማኝ ማስረጃ የተደገፈ ጽሑፍ አልቀረበም። የዚች ጦማር ዓላማም ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር በምታከናውናቸው ውሎች ያሁኑንና የመጪውን ትውልድ ሁሉ መብት በሚጠብቅ ሥልት መጠቀሟን እንድታረጋግጥ ተገቢውን ቅድመ-ዝግጅትና ጥንቃቄ እንድታደርግ ለማሳሰብ ነው። በዚህ አጋጣሚም፤ ተሞክሮው ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ስለሚመስለኝ፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት፤ የለሶቶ (Lesotho) መንግሥት የሥራ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በነበርኩበት ጊዜ ስለዛች ሐገር ወንዝ፤ በዓለም ባንክ ድጋፍ፤ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጋር እኔ ራሴ በመራሁት የልዑካን ቡድን ስለ ተከናወነው ድርድርና ስለ ተገኘው ውጤትም ባጭሩ እገልጻለሁ። Rile river facts and information in Amharic
የአባይ ወንዝ በረከት፤
አባይ፤ ኢትዮጵያ ካሏት እጅግ ታላቅና አኩሪ የተፈጥሮ ሐብቶች አንዱ ነው። ክልዩ ልዩ ወንዞች የተጠራቀመው ወደ 80 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር (cubic metre) ውሀ በአባይ አማካኝነት እየተዥጎደጎደ ሱዳንንና ግብጽን እያለማ አቋርጦ ከሚተነው ውሀ የተረፈው ሚዲቴሬኒያን ባሕር ይገባል። አባይ ከኢትዮጵያ ሰንቆ የሚጓዘው ውሀ ብቻ ሳይሆን ለም አፈር ጭምር ነው። ስለዚህ ግብጽና ሱዳን የሚታየው ለም መሬት፤ አብዛኛው በአባይ ወንዝ አማካኝነት ከኢትዮጵያ በሚጎርፍለት ውሀና ለም አፈር ችሮታ ነው። በተጨማሪም፤ እስካሁን ሳንጠቀምበት የቆየነው፤ ምናልባት በመሠራት ላይ ያለው ግድብ ለውጤት ከበቃ፤ ለኢትዮጵያና ለአካባቢዋ ከፍ ያለ የኃይል ማመንጪያ ሐብት ሊያስገኝ የሚችለው ሌላው የአባይ ወንዝ በረከት ሊሆን ይችላል።
በአባይ ወንዝ በረከት የተጠቀመው ማን ነው?
በእንግሊዝኛ Blue Nile (በአማርኛ፡ አባይ) ከተሰኘው፤ በዓለምና በታሪክ ታዋቂ ከሆነው ወንዝ ዋናዎቹ ተጠቃሚዎች ሱዳንና ግብጽ ናቸው። ከሌሎች ሐገሮች ጭምር ወደ ሱዳንና ግብጽ የሚፈሰው ውሀ ሲታሰብ ከኢትዮጵያ የሚዘልቀው የአባይ ወንዝ አስተዋጽኦ ከጠቅላላው የውሀ መጠን 86% እንደ ሆነ ይታወቃል። የሚያሳዝነው ከባድ ጉዳይ ግን፤ የአባይ ወንዝ ዋናዋ ምንጭ የሆነችው፤ ኢትዮጵያ፤ ለብዙ ዘመናት ተጠቃሚ ሳትሆን መቅረቷ ነው። ይህን ሁኔታ ከባድ የሚያደርገው፤ ባንድ በኩል አባይን የመሰለ አኩሪ የውሀ ሐብት እያላት፤ ኢትዮጵያ በድርቀት ምክንያት በመደጋገም ረሀብና እልቂት የተፈራረቀባት ሐገር መሆኗ ነው።
በዚህ አጋጣሚ፤ አንድ የማልረሳው ነገር፤ በተባበሩት የዓረብ ኤሚሬትስ እሠራ በነበረበት ጊዜ፤ በዚያ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP) ባዘጋጀልን አንድ ስብሰባ አንድ ግብጻዊ የውሀ መሐንዲስ ጎኔ ተቀምጦ ስለ ነበር፤ በውይይታችን መሀል የአባይ ወንዝ ጉዳይ ተነሳና አብዛኛው ከኢትዮጵያ የሚመነጭ መሆኑን ሳስታውሰው፤ ወዲያውኑ የሚያስቆጭ መልስ ሰጠኝ፤ “አዎን፤ እኛ (ግብጽ) እንጠቀምበታለን።” “እኛም (ኢትዮጵያም)” የምልበት ጊዜ በሕይወት እያለሁ ይደርስ ይሆን?!
ለመሆኑ፤ የአባይ ወንዝ ባለቤት ማን ነው?
ዶር. ሚንጋ ነጋሽ፤ ዶር. ሰይድ ሀሰንና ዶር. ማሞ ሙጬ በቅርቡ ባበረከቱት “Misplaced Opposition to the Grand Ethiopian Renaissance Dam” በተሰኘው ጽሑፋቸው፤ ክታዋቂው ከሪቻርድ ፓንከርስት (Richard Pnakhurst) በመጥቀስ፤ በጥንቱ፤ ቱርኮች ግብጽን በሚገዙበት ዘመን፤ የአባይ ወንዝ የኢትዮጵያ መሆኗ ታውቆ፤ 50000 (ሃምሳ ሺ) የወርቅ መሀለቅ (gold coins) ለሐገራችን በየዓመቱ ይከፍሉ እንደ ነበር ታውቋል።
ከላይ እንደ ተጠቀሰው፤ ምንም እንኳ ወደ ሱዳንና ግብጽ የሚነጉደው የአባይ ወንዝ ምንጭ ኢትዮጵያ ብትሆንም፤ በቅርብ ዘመናት የታየው፤ ለጊዜው ተጠቃሚ የሆኑት ሐገሮች እያንጸባረቁት የቆየው ተጨባጭ ክስተት ባለቤትነቱ የነሱ እንደ ሆነ ዓይነት መሆኑ ነው። ከላይ የተጠቀሱት ምሑራን እንደ ገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችባቸው ውሎች፤ (ሀ) እ.አ.አ በ1929 በእንግሊዝና በግብጽ መሀል በተፈጸመው ውል 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር ውሀ ለግብጽ፤ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር ውሀ ለሱዳን እንዲመደብ፤ በኋላ ደግሞ (ለ) በ1959 በግብጽና በሱዳን መሀል በተከናወነው ውል 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር ለግብጽ፤ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር ውሀ ለሱዳን ተመድቧል። የሚያስገርመው፤ ዋናዋ የውሀው ምንጭ የሆነችው የኢትዮጵያ መብት ምንም ዋጋ አልተሰጠውም።
ባሁኑም ጊዜ ተከስቶ ያለው ሁኔታ፤ ግብጽ “የአባይ ስጦታ” (“Gift of the Nile”) መሆኗን ስለምታውቅ በተለይ በቅርቡ ዘመን የለመደችውን ልቅ የሆነ በአባይ ወንዝ የመጠቀም ችሮታ ያለገደብ እንድትቀጥል መብቷ እንደ ሆነ እያስመሰለች ኢትዮጵያ በመብቷ ከተጠቀመች እርምጃ የሚያስከትል መሆኑን በመጠቆም የማስፈራራት ሥልት እያናፈሰች፤ በሌላ በኩል የዚህ ዓይነት አጉል ዘዴ የማያዋጣ መሆኑን ግንዛቤ ያለው በሚመስል ሥልት ለመደራደር ፈቃደኛነት ትጠቁማለች። ኢትዮጵያውያን መብታቸውን ለማስከበር በቁርጠኛነት ከወሰኑ፤ ማንም ሊገድባቸው እንደማይችል ግብጽም ብትገነዘብ መልካም ነው። በታሪክ እንደምናውቀው፤ ግብጽ፤ የሕልውናዋ ምንጭ የሆነውን አባይን በቁጥጥሯ ስር ለማድረግ፤ ከአሥር ጊዜ በላይ ኢትዮጵያን ወርራ፤ ሐረርን እስከ መያዝ ደርሳ፤ በመጨረሻው ግን ሳይሳካላት ቀርቷል። በተቃራኒው፤ ከታሪክ የምንማረው፤ ኢትዮጵያ ከኃያሎቹ ሐገሮች አንዷ በነበረችበት ዘመን፤ ግብጽንም ተቆጣጥራ እንደ ነበር ነው። ለዚህ ማስረጃ ካስፈለገ፤ የጥንት ግብጻዊ ነገሥታትን ታሪክ መመልከት ይበቃል። ስለዚህ፤ ግብጽ ስለ አባይ ወንዝ ባለቤትነት የምትከተለው ሥልት የትም ስለማያደርሳት፤ ይልቁንስ ሚዛናዊ በሆነ፤ የሁሉንም የወንዙን አካባቢ ሐገሮች መብት በትክክል ማስተናገድ የተሻለ ዘዴ ነው። መብቷን የማስከበሩ ዋናው ኃላፊነት ግን የኢትዮጵያ ነው።
ሱዳንን በተመለከተ፤ ምንም እንኳ፤ ከመገናኛ ብዙኃን መገንዘብ እንደሚቻለው፤ በመገንባት ላይ ስላለው ግድብ ደጋፊ መሆኗ ቢገለጽም፤ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ስላላት መብት አቋሟ ምን እንደ ሆነ በይፋ አልተገለጸም።
ስለ አባይ ወንዝ ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ፤ ከሚነጉደው ውሀ 86% የምታበረክተው፤ 100 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት የኢትዮጵያ ድርሻ በትክክል እንዲታይ ያስፈልጋል። የውሀ ሐብቷ እያለ፤ ኢትዮጵያ በድርቅና በረሀብ መሰቃየቷ መቀጠል የለበትም። ኢትዮጵያም፤ የወንዝ ምንጮች እንደሆኑ እንደ ሌሎች ሐገሮች፤ በአባይ ወንዝ በረከቷ፤ በውሀዋ፤ በኃይል ማመንጫዋና በአፈሯ በስፋት እየተጠቀመች ልማቷን ማጣደፍና ማሳደግ መብቷ ነው። ይህም ሲባል ግን፤ የሌሎቹ ሐገሮች፤ ማለት የሱዳንና የግብጽ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት አይኑር ማለት አይደለም። የዓለም-አቀፍ ሕግ መመሪያዎችን መሠረት ባደረገ ሚዛናዊ በሆነ የጋርዮሽ አጠቃቀም ሥልት ይከናወን ማለት ነው። ይህንንም ለማስገኘት በጥሞናና በመከባበር ለዘለቄታው ተቀባይነት በሚያስገኝ ዘዴ መደራደርና መዋዋል ያስፈልጋል ማለት ነው።
የለሶቶ (Lesotho) በወንዟ ሐብት የመጠቀም ተሞክሮ፤
በመግቢያው እንደ ገለጽኩት፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት ለሶቶ (Lesotho) አገልግዬ ነበር። እዚያች ሐገር የሠራሁትም እ.አ.አ በ1972-78 ሲሆን፤ ለአራት አመቶች በፖስታ፤ ቴሌኮሙኒኬሽንና ሲቪል አቭዬሽን ዋና ዲሬክተርነት ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመቶች ደግሞ የሥራ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በመሆን ነበር። የሥራ ሚኒስቴሩም የሚያጠቃልላቸው አገልግሎቶች፤ የመንግሥት ሕንጻዎችና መንገዶች ግንባታዎችና ጥገናዎች፤ የውሀ ልማትና አቅርቦት፤ የመብራት ኃይል አገልግሎትና፤ የትራንስፖርት አገልግሎት ነበሩ። በነገራችን ላይ፤ ስለዚህ ሥራዬና ስለ ሌሎችም አገልግሎቶቼና ተያያዥ ጉዳዮች በቅርቡ በሚወጣ መጽሐፌ በሰፊው ለመግለጽ እየተዘጋጀሁ ነው።
ለሶቶ፤ ደቡብ አፍሪካ መሀል የምትገኝ አንድ ትንሽ ሐገር ናት። ትንሽ ብትሆንም፤ እንደ ኢትዮጵያ የውሀ ሐብት በረከት ያላት ሐገር ናት። እኔ ለሶቶ በነበርኩበት ጊዜ የለሶቶ ወንዝ የሚፈሰው ደቡብ አፍሪካ ለልማትና ሌላም ጥቅም ወደምትፈልገው አቅጣጫ ስላልነበረ፤ አስፈላጊው የማስተካከል ተግባር ተከናውኖ ሙሉ ተጠቃሚ እንድትሆን በለሶቶና በደቡብ አፍሪካ ድርድር ተጀምሮ ነበር። በዚህም ምክንያት በቋሚ ተጠሪነት ተግባሬ በድርድሩ ተካፍዬ ነበር። ከዚሁ በተለይ የማስታውሰው፤ እ.አ.አ. በ1977 በኔ መሪነት ኬፕ ታውን (Cape Town) በመጓዝ የለሶቶ ባለሥልጣኖችና ከየዓለም ባንክም ተወካይ የተገኘበት ልዑካን ከደቡብ አፍሪካ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣኖች ጋር ተደራድረን ነበር። የድርድሩ ጭብጥም ለሶቶ በውሀ ሐብቷ (ለኃይል ማመንጪያ ጭምር) የመጠቀም መብቷ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚፈሰው ውሀ ለሶቶ ተገቢውን ክፍያ እንድታገኝ ለማድረግ ነበር።
ያ ሁሉ ድርድር ውጤቱ አምሮ፤ የለሶቶን ተራራ በመሸንቆርና የወንዙን ፍሰት አቅጣጫ በማስለወጥ ለደቡብ አፍሪካ የሚያስፈልገው ውሀ በሚገባ እንዲቀርብ ለማድረግ ከቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሆነበት ሥራ ተጠናቆ፤ ባሁኑ ጊዜ ለሶቶ በያመቱ፤ በአማካኝ፤ $50 ሚሊዮን በደቡብ አፍሪካ እየተከፈላት ነው።
ለሶቶ ብሔራዊ መብቷንና ጥቅሟን ከላይ እንደ ተገለጸው ማስከበር ከቻለች፤ በታሪኳም ነጻነቷንና ክብሯን በማስከበር የምትታወቀው ኢትዮጵያ ከዚያ ያነሰ ይጠበቅባታል?
ማጠቃለያ፤
የአባይ ወንዝ የኢትዮጵያ ታላቅ የተፈጥሮ ሐብት ነው። ኢትዮጵያ የሱዳንንና የግብጽን ተገቢ መብት እያከበረች የራሷንም ጥቅም መጠበቅና ማስከበር ይኖርባታል። ለዚህም፤ በወንዝ ውሀ አጠቃቀም መርሆ፤ ሥልትና እቅድ ባለሞያዎች በመታገዝ ዝርዝር ጥናቶች በማከናወን ከጎረቤት ሐገሮች ጋር የሚደረገው ድርድር የኢትዮጵያን የዘለቄታ ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን ማረጋገጥና ሒደቱም ግልጽነትና ቁጥጥር የሰፈነበት እንዲሆን፤ የአባይ ወንዝ ዋናው ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖረውና ሙሉ መብቱ እንዲጠበቅ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

የወያኔ ጥላቻ ፍሬ (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም )

May 23, 2014
ወያኔ ለትግራይ ሕዝብ ሀብትንና ብልጽግናን አመጣ ብለው የሚያምኑ ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ወያኔ የሥልጣን ወንበሩ ላይ በመውጣቱ ትግሬዎች ሁሉ አልፎላቸዋል ተብሎ ይታመናል፤ በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ላይ የጠነከረ እምነት አላቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙ ውይይትም ይሁን ንትርክ ይደረጋል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የተፈራ ርእስ ነው፤ ውስጥ-ውስጡን እንጂ አደባባይ አይወጣም፤ ይህንን ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ አደባባይ ለማውጣት ጊዜው የደረሰ ይመስለኛል፤ አረጋዊ በርሄ፣ ገብረ መድኅን አርአያ፣ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ አብርሃ ደስታ (አሥር ቢሞሉልኝ ደስ ይለኝ ነበር!) እየደጋገሙ ቢያነሡትም ሌሎች በቁም-ነገር የተቀበሉት አይመስልም፤ ሕዝቡ ግን በራሱ መንገድ እየተናገረና ምስክርነቱን እየሰጠ ነው፤ በመቀሌ የተሠራውን የመኳንንት መንደር ሕዝቡ አፓርቴይድ ብሎ ሲሰይመው፣ በአዲስ አበባ የተሠራውን መንደር መቀሌ ብሎ ሲሰይመው እየመሰከረ ነው፤ ‹‹የለሁበትም!›› እያለ ነው።
Prof. Mesfin Woldemariam
Prof. Mesfin Woldemariam

የትግራይ ሕዝብ መደህየቱ አልበቃ ብሎት ሲለምንም እየተሳቀቀ ነው፤ የሚለምነው ትግሬ ለብዙ ሰዎች ትግሬና ወያኔ አንድ መስሎ እንደሚታየው ያውቃል፤ አብዛኛው ሰው በወያኔ ላይ ያለውን ስሜት ያውቃል፤ ስለዚህም ሲለምን ሰዎች በወያኔ ላይ ያላቸውን ስሜት ስለሚያራግፉበት እየተሸማቀቀ ነው፤ አንድ የትግራይ ቄስ ከአርሲ ነኝ አሉኝና ለምን እውነቱን አይናገሩም ስላቸው እውነቱን ስናገር የማገኘው ስድብ ብቻ ነው አሉኝ፤ እኒህ ሰው ምን በወጣቸው የወያኔን ኃጢአት ተሸካሚ ይሆናሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በትግሬነቱ የተጠቀመ አለ፤ እኔ የማውቀው የደርግ ወታደር የነበረ ትግሬ ቆስሎ ከውትድርና ወጣና በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የጥበቃ ሥራ ላይ ነበር፤ በጣም ይቸግረው ነበር፤ ሚስቱ ሕመምተኛ ነበረች፤ የቤት ኪራይ መክፈል ይቸገር ነበር፤ ዛሬ ግን የሚለብሰው ልብስ ሌላ ነው፤ ከኑሮውም ተርፎ ለሲጃራና ለጫት እያወጣ ነው፤ ወይም ሌሎች እያወጡለት ነው፤ ትግሬነታቸው ብቻ እንዲህ የደላቸው በጣም፣ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህም በወያኔ አገዛዝ ትግሬ ሁሉ ተጠቅሞአል ማለት ከጉልሁ እውነት ጋር የሚጋጭ ስሕተት ነው፤ አብርሃ ሰዎች ትግሬ ሁሉ ተጠቃሚ ሆኗል ሲሉ ‹‹ያመኛል›› ማለቱ ይገባኛል።
ወያኔ ትግሬ በመሆኑ ብቻ ትግሬ ሁሉ ዕዳ አለበት ማለት እንደወያኔ ማሰብ ነው፤ ወንጀል በዘር አይተላለፍም፤ እያንዳንዱ ሰው ለሠራው ሥራ ሁሉ ኃላፊነትን ይወስዳል፤ ጊዜው ሲደርስ ውጤቱንም ለመቀበል ይገደዳል፤ ይህ የሚሆነው ሰው ሁሉ በመንፈሳዊ ኃይል በጎ መንፈስ አድሮበት፣ አእምሮው በትምህርት ተገርቶ በትክክል ማሰብ ሲችል ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን በአለበት ሁኔታ በጎ መንፈስ የራቀው ይመስላል፤ አእምሮም ጭራሹኑ በእኩይ መንፈስና በጥላቻ እየዛገ ነው፤ ስለዚህ ያስፈራል፤ በደቡብ ሱዳን ሁለት መቶ ሰዎች በዘር ተለይተው ታረዱ ሲባል ያስፈራል፤ በናይጂርያ፣ በኮንጎ የሚካሄደውን የዘርና የሃይማኖት እልቂት ስንሰማ ያስፈራል፤ በ1997 ዓ.ም. መለስ ዜናዊና አዲሱ ለገሰ እንዳስታወሱን የሩዋንዳ የጎሣ እልቂት በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ አለ፤ የቅርብ ተኳሽ የሆነው የአግዓዚ ጦርም አድፍጦ መጠበቅ ያስፈራል፤ ሌላውም ይህንን አውቆ አድፍጦ መጠበቁ ያስፈራል፤ ሰማይ ጠቀስ የሠሩት፣ የሥልጣን ኃላፊነትን ችላ ብለው በሥልጣን የሚነግዱና የሚከብሩት፣ የማይኖሩበትን ሕንጻ የሚክቡት፣ ከሕዝብ ጋር ያላቸው የአይጥና የድመት ኑሮ ያስፈራል፤ አቶ አስገደ ወያኔ መደንገጡን ይነግረናል፤ መደንገጥ የማይቆጣጠሩት ፍርሃት ነውና አደጋ ያመጣል፤ አደጋው አደጋን ይጠራል፤ ይህም ያስፈራል።
በትግራይ ዙሪያ ያለው ምንድን ነው? የትግራይ ሕዝብ በየትኛው አቅጣጫ ነው አንደልቡ እየተዘዋወረ ለመሥራትና ለመኖር የሚችለው? ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ከሰሜን ከወገኑ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ደም አቃብቶታል፤ በደቡብ-ምሥራቅ ከወሎ መሬት ቆርሶ የወሎን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ በደቡብ-ምዕራብ ከጎንደር መሬት ቆርሶ የጎንደርን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ የራስን ወገኖች አስቀይሞ ሱዳንን በመሬት ለመደለል የሚደረገው ጥረት ሁሉ ፋይዳ የለውም፤ ሱዳን ለራሱም ያልበጀ አገር መሆኑ እየታየ ነው፤ ወደፊት ደግሞ ይበልጥ ይታያል፤ በትግራይ ውስጥ ደግሞ ወያኔ የፈጠረው አፓርቴይድ የወያኔን የኑሮ ደረጃ ወደሰማይ ሲያስጠጋው፣ የቀረውን ወደአንጦርጦስ የደሀነት ገደል ውስጥ ከቶታል፤ በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ከነልጆቻቸው እየተዘዋወሩ የሚለምኑ ሞልተዋል፤ ይህ ልመናም ለወያኔ ለመገበር ነው፤ ብዙዎቹ እንደሚናገሩት የሚለምኑት የማዳበሪያ ዕዳቸውን ለወያኔ ለመክፈል ነው።
ወያኔ ከሀያ ዓመታት በላይ አፍንጫ እየያዘ ያስከፈለውን የሚመልስበት ጊዜ እየተቃረበ ነው፤ ጥያቄው ወያኔ እንዲመልስ የሚገደደው እንዴት ነው? የሚል ነው፤ጥላቻ ወደንዴት፣ ንዴት ወደቁጣ ተለውጦ ሲገነፍል ምጽዓት ደረሰ ማለት ነው፤ ሁሉም ሰው ራቁቱን ይሆናል፤ አንደአውሬ ከጥፍሩና ከጥርሱ በቀር ሌላ መሣሪያ አይኖረውም፤ ሰው ሁሉ በክፋት ወደአውሬነት ይለወጣል፤ ጠመንጃና ቦምብ አያገለግሉም፤ ሕንጻው ምሽግ አይሆንም፤ መኪናው፣ ባቡሩ፣ ታንኩ ከቆመበት አይነቃነቅም፤ የትም አያደርስም፤ ጭፍራ ሁሉ በየራሱ ፍዳ ታንቆ እንኳን ለሌላ ሊተርፍ ለራሱም የማይበቃ ይሆናል፤ ለነገሩ ጌታና ሎሌም የለም፤ ሁሉም በአውሬ እኩልነት የተፋጠጠ ነው፤ ርኅራኄ ተሟጦ፣ መግል ያዘለ ልብ ፈርጦ፣ ውይይትና ክርክር አብቅቶ፣ ጥርሱን ያገጠጠና ጥፍሩን የሳለ መንጋ በደም የሚራጭበት ሁኔታ ነው።
ሌላ አገር እንዲህ አልሆነም፤ እዚያ አገር እንዲህ አልሆነም፤ የሚባል ነገር የለም፤ እኛ ዘንድ ሌላ ነው፤ የኢትዮጵያ ደሀዎች እንባ የእግዚአብሔርን ሰማይ አጨቀየው!