Friday, 11 April 2014

..ሰበር ዜና፣ የሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ

April 11, 2014
ሰሞኑን አንድነት ፓርቲ በአዲስ አበባ የሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ህወሃት/ኢህአዴግን በደብዳቤ ሲያስፈቅድና ፍቃድ ሲከለከል፣ ከዚያም ድግሞ ለሌላ ጊዜ ሲያስተላልፍ የተላለፈውን ቀንም መልሶ ሲሰርዝ በመጨረሻም ቀኑን ወደፊት እንደሚያስታውቅ ገልጾ ነበር ጉዳዩን በእንጥልጥል የተወው።
ይህ በዚህ እንዳለ የሰማያዊ ፓርቲ በፌስ-ቡክ ገጹ ላይ የሚከተለውን ጥሪ አስተላልፏል፣
———————————–

የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልሳለን!!!

የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልሳለን በሚል መሪ ቃል ሰማያዊ ፓርቲ ሚያዚያ 19 እሁድ ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ከጠዋቱ 4 ሰአት እስከ 8 ሰኣት ድረስ በጃንሜዳ ያደርጋል፡፡

Semayawi (Blue party) called rally in Addis Ababa

በኢትዮጵያ የመብቶች ትግሎች ሁሉ ህወሓትን ከሥልጣን ወደ ማስወገድ አቅጣጫ ያመራሉ! (ግንቦት 7)

April 11, 2014
Ginbot 7 weekly editorialየሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ መሪዎች የክስ ሂደት በበርካታ አሳዛኝ ጉዳዮች የታጀቡ ቢሆኑም የሚሰጡት ትምህርት ግን ከፍተኛ ነው። እነዚህ ወገኖቻችን “ችሎት” በተሰኘው የአገዛዙ የድራማ መድረግ በመገኘት ፍትህን ለመግደል ካባ ለብሰው “ዳኞች” ተብለው ለተኮፈሱ የአገዛዙ ተላላኪ ካድሬዎች እና ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረጓቸው ጠንከር ያሉ ንግግሮች ካድሬ “ዳኞችን” አሳፍረዋል፤ ኢትዮጵያዊያንን ግን አኩርተዋል። እኚህ ወገኖቻችን ከወያኔ ችሎት ፍትህ ይገኛል የሚል ብዥታ ባይኖራቸውም መድረኩን መልዕክት ለማስተላለፊያነት ተጠቅመውበታል። በዚሁ መድረክ በአገዛዙ እጅ ከወደቁበት ጊዜ ጀምሮ እየደረባቸው ስላለው ሰቆቃ ሲናገሩ አድማጮች ሊቆጣጥሩት የማይችሉት ሐዘንና እልህ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።
ወያኔ እንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ የሚፈጽመው በሙስሊም መሪዎች ላይ ብቻ አይደለም። የህግ እውቅና የተሰጣቸው መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው በጠየቁ ወገኖቻችን ሁሉ ተመሳሳይ ሰቆቃ ሲፈጸም ኖሯል፤ አሁን እየተፈጸመ ነው። “ኑሮ ከበደን” ያሉ ወጣቶች ተደብድበዋል። “የእርሻ መሬት አጣን” ያሉ ገበሬዎች ከያዙት ቁራሽ መሬት ተፈናቅለዋል፣ ተግዘዋል፣ ከነልጆቻቸው ለጎዳና ኑሮ ተዳርገዋል። በሀረር እና በአዲስ አበባ ከተሞች እንደታየው “ነግደን እንኑር” ባሉ ነጋዴዎች ላይ ከአቅም በላይ ከሆነ ግብር ጀምሮ በንብረታቸው ላይ እሳት እስከመልቀቅ የደረሰ አረመኔዓዊ ድርጊት ተፈጽሟል።
በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 18 መሠረት እያንዳንዱ ሰው በግሉም ሆነ በጋራ የፈለገውን ሃይማኖት የመከተልና የማስተማር፤ ያልፈለገውን ደግሞ የመተው መብት አለው። ስለሆነም የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ተግባራት በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ እውቅና ለተሰጣቸው መብቶቻቸው መከበር ያደረጉት ትግል ነው። ለወጉ ያህል “ሕገ መንግሥት” ተብሎ በሚጠራው ኢትዮጵያዊያንን ለመክሰሻነት ብቻ በሥራ ላይ በሚወለው ሰነድ ውስጥ የተካተቱ ቢሆንም ዓለምዓቀፍ እውቅና ያገኙ መብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ተረግጠዋል። ለእነዚህ መብቶች መከበር በጽናት የቆሙ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች ከተራ የመንደር ካድሬና ጆሮ ጠቢ እስከ እስከ ከፍተኛው እርከን ባለ ባለሥልጣኖች ተዋክበዋል፤ ሰቆቃ ተፈጽሞባቸዋል።
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለእምነት መብቶቹ መከበር እስካሁን ያደረገው ተጋድሎ የሚደነቅ ነው። የተቀናጁ እንቅስቃሴዎቹ፣ ተምሳሌታዊ የተቃውሞ ምልክቶች አጠቃቀሙ የሚያበረታታ ነው። ክርስቲያኑ ከዚህ የሚማራቸው በርካታ ቁም ነገሮች አሉ።
ከሙስሊም እንቅስቃሴና ወያኔ ይህንን እንቅስቃሴ ለማፈን እየሰዳቸው ካሉ እርምጃዎች የምንረዳው አንድ ትልቅ ሐቅ የቱን ያህል ጨዋና የሰለጠነ ቢሆን ወያኔ የሕዝብ ድምጽ ለማዳመጥ ፍላጎት የሌለው መሆኑን ነው። ሙስሊም ወገኖቻችን ጥያቄዎቻቸውን በሚያስገርም ቁጥብ ሥነሥርዓት (ዲሲፕሊን) ቢያቀርቡም ከወያኔ የተሰጠው ምላሽ ግን አፈና፣ ረገጣ፣ ቶርቸር እና ከእስከዛሬዎቹ ይበልጥ አፋኝ የሆኑ ደንቦችና ድንጋጌዎችን ነው። ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ያደረጓቸው ትግሎችም እንደዚሁ ወደ ባሱ የመብት ጥሰቶች እያመሩ ነው። ከዚህ የምንማረው ነገር ትግሉ ውጤታማ እንዲሆን ስትራቴጂዎችን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ነው።
እንደሚታወቀው፤ ሰብዓዊ መብቶች እርስ በርሳቸው የተቆራኙ፤ እርስ በርሳቸውም የሚደጋገፉ ናቸው። አንዱ የመብት ዓይነት ሲጓደል፤ ሌላውም አብሮ ይጓደላል። ለምላሴ የመናገር መብት ተገፎ እያለ የማምለክ መብት ሊፋፋ አይችልም፤ ወይም ደግሞ ፍትሃዊ ዳኝነት የማግኘት መብት ተጥሶ እያለ የማምለክ መብትን የሚያስከብር ተቋም ሊኖር አይችልም።
ለመብቶች መከበር የሚደረጉ ትግሎች፤ በተለይም ደግሞ የሙስሊም ወገኖቻችን ትግል የደረሰበት ደረጃ በአንክሮ ሲጤን ስትራቴጂን በተመለከተ በጥልቀት ልናስብባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን እንገነዘባለን። ለጊዜው ሁለት ነገሮች ላይ አጽንዖት ሰጥተን እናልፋለን።
  1. ከላይ እንደተገለፀው የመብት ትግሎች ሁሉ መደጋገፍ ይኖርባቸዋል። ቀደም ሲል በባህርዳር፣ በኋላም በአዲስ አበባ በሴቶች ዓለም ዓቀፍ ቀን አሁን ደግሞ በደሴ ውስጥ እንደታየው የመብት ጥያቄዎች ሁሉ ተደጋግፈው መነሳት ይኖርባቸዋል። ይህ የመደጋገፍ ልምድ የሁለቱ ትላልቅ ሃይማኖቶች ተከታዮች ለየእምነቶቻቸው ነፃነት በሚያደርጉት ትግል ውስጥ መኖር ይኖርበታል። የሙስሊሞች የመብት ጥያቄዎች የክርስቲያኖችም፤ የክርስቲያኖች ደግሞ የሙስሊሞችም መሆን ይኖርበታል።
  2. በሥልጣን ላይ ያለው የህወሓት አገዛዝ አንዱንም የመብት ጥያቄ መመለስ የማይችል መሆኑ ግልጽ መሆን ይኖርበታል። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የመብት ጥያቄዎች ግብ ወያኔን ከሥልጣን ከማባረር ያነሰ መሆን አይችሉም። ስለሆነም የመብት ማስከበር ትግል ስናካሂድ ይህን አልመን እና ለዚህም ተዘጋጅተን መሆን ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የስነልቦና፣ የድርጅትና የስልት ዝግጅት ይጠይቃል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ህወሓት ከሥልጣን መወገድ ይኖርበታል ብሎ ያምናል። ወያኔ በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ መገለል፣ መረገጥ፣ መጋዝ፣ መሰደድ፣ መደብደብ፣ የማይቀርልን በመሆኑ ሥቃያችንን ለመቀነስ ወያኔን ማስወገድ ይኖርብናል ብሎ ግንቦት 7 በጽኑ ያምናል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ መንገዶችና ምክንያቶች የምናደርጋቸው ትግሎች ወደ አንድ አቅጣጫ ያመራሉ ብሎ ያምናል። ትግሎቻችን ዞሮ ዞሮ ህወሓትን ከሥልጣን ወደ ማስወገድ ማምራታቸው ግልጽ ስለሆነ ለዚህ የሚያስፈልገውን ስነልቦናዊና ቁሳዊ ዝግጅቾችን እናድርግ ይላል።

የህወሓት ስትራተጂ: –

ማስፈራራት – በጥቅም መደለል- ማግለል- ማስቀናት- ከጥቅም ማገድ- ስም ማጥፋት- በመጨረሻ መፍራትና መሸነፍ!
==================
የህወሓት ዓላማ ስልጣን ነው። ስትራተጂውም ከዓላማው ይመነጫል። ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚከተለው ስትራተጂ ሌሎች አማራጭ ፓርቲዎች በሐሳብና በተግባር በማሸነፍ (በልጦ በመገኘት) ሳይሆን አማራጭ ሐሳብ ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማዳከም ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለማዳከም የሚጠቀመው የመጀመርያ ስትራተጂ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ማስፈራራት ነው። የፓርቲ አባላትን በማስፈራራት አባልነታቸውን (ተቃውሞአቸውን) እንዲያቆሙ ተፅዕኖ ይደረጋል።
የማስፈራራት ስትራተጂ ካልሰራ (የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በህወሓት ፕሮፓጋንዳ ካልፈሩ) በጥቅም የመደለል ስትራተጂ ይከተላል። የተቃውሞ ፓርቲ አባልነታቸው አቁመው ለህወሓት ከሰሩ (ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እየሰለሉ ህወሓትን ካገለገሉ) ቁሳዊ ጥቅም እንደሚሰጣቸው ይነገራቸዋል። በመረጡት ቦታ መሬት ይሰጣቸዋል፤ የፈለጉትን ዓይነት አገልግሎት ያገኛሉ።
ይህንን በጥቅም የመደለል ስትራተጂ ካልሰራ (ድለላው ተቀባይነት ካላገኘ) የማግለል ስትራተጂ ይከተላል። ጓደኞችህን በማስፈራራት ካንተ (ፓርቲ አባል) እንዲርቁ ይደረጋል፤ ከማህበራዊ ህይወትህ ትገለላለህ። ብቸኝነት ተሰምቶህ ዓቋምህ ትቀይር እንደሆነ ለማየት ነው። መጀመርያ የደህንነት ሰዎች እየመጡ ጓደኞችህን ያስፈራራሉ። ከፈሩና ከተለዩህ ህወሓቶች ተሳካላቸው ማለት ነው። ካልፈሩ ደግሞ ቁሳዊ ጥቅም ይቀርብላቸውና አንተን በጥቅም የማስቀናት መንገድ ይከተላሉ። (ብዙ ጓደኞቼ ስለፈሩ ወደ ቁሳዊ ጥቅም የማግኘት ደረጃ ያልደረሱ አሉ፤ የተወሰኑ ግን በጣም ሃብታም ነጋዴዎች ሁነዋል፤ እንኳን ተጠቃሚ ሆኑ፤ ህሊና በቁስ ነገር መሸጥ መጨረሻው ፀፀት ቢሆንም)። በመጨረሻ አንተን ከሁሉ ዜግነታዊ ጥቅምና ሕጋዊ መንግስታዊ አገልግሎት ያግዱሃል። በዚህ ሁሉ ተፅዕኖ ካልተምበረከክ የደህንነት ሰዎች አሰማርተው ስምህ እንዲጠፋ የፈጠራ ወሬዎች ይነዛሉ። አሁን ካልተሸነፍክ ግን በቃ እነሱ ይፈሩሃል፤ ያከብሩሃል። በመጨረሻም እጃቸው ይሰጣሉ፤ ይምበረከካሉ። መሸነፋቸውን በገዛ አንደበታቸው ይመሰክራሉ።
ስለዚህ በግለሰብ ደረጃ ህወሓቶች ስትራተጂ: ማስፈራራት፣ በጥቅም መደለል፣ ማግለል፣ ማስቀናት፣ ከጥቅም ማገድ፣ ስም ማጥፋት ነው። በመጨረሻ መፍራትና መሸነፍ፤ ድል ያንተ ነው።
በፓርቲ ደረጃ: ተቃዋሚ ፓርቲዎች አማራጭ ሐሳባቸውን ለህዝብ እንዳያቀርቡ ይደረጋል። ስለነሱ መጥፎ ነገር ለህዝብ ይነገራል። ህዝብ ፖለቲካ እንዳያውቅ ይደረጋል፤ ምክንያቱም ህዝብ ፖለቲካ ካወቀ መብቱ ያውቃል። መብቱ ካወቀ ነፃነቱ ያውቃል። ነፃነቱ ካወቀ ዓፈና ይቃወማል። ዓፈና ከተቃወመ ዓፋኝ ስርዓትን ከስልጣን ያባርራል። ዓፋኝ ስርዓት ከስልጣን ከተባበረ ህወሓት ስልጣን ይለቃል። ምክንያቱም ህወሓት ዓፋኝ ስርዓት መሆኑ ይደረስበታል። ስለዚህ የህወሓት ጥረት ህዝብ እንዳያውቅ ማፈን ነው።
ለዚህም ነው የህወሓት ዋነኛ ስትራተጂ ህዝብን ማፈን የሆነው። ህዝብ ሲታፈን ዓፈናውን መጋለጥ አለበት። የህዝብ ዓፈና የሚያጋልጡ የግል ጋዜጠኞች ናቸው። ጋዜጠኞች በህዝቦች ላይ የሚደርስ ዓፈና በማጋለጥ የጋዜጠኝነት ግዴታቸውን ይወጣሉ። ህወሓት ዓፋኝ ስርዓት መሆኑ ስለሚያውቅ ህወሓት በህዝቦች ላይ የሚያደርሰውን ዓፈና ሊያጋልጡ የሚችሉ የግል ጋዜጠኞች በጥቅም ማማለልና መደለል ጀምሯል። በዚሁ መሰረት ብዙ የግል ጋዜጠኞች በመረጡት ከተማና ቦታ መሬት ይሰጣቸዋል። ለጋዜጠኞች መሬት የመስጠት ድርድር (ቅሌት) ተጀምሯል። በድርድሩ የተስማሙ ጋዜጠኞች መሬት ይሰጣቸዋል። እንደዉጤቱም በህዝቦች ላይ የሚደርስ ዓፈና ሳያጋልጡ ያፍናሉ። የዓፈና መረጃ ያፍናሉ ማለት ነው። ሙያቸው ይክዳሉ ማለት ነው። እስካሁን መሬት የተሰጣቸው ጋዜጠኞች አውቃለሁ። የተሟላ ስም ዝርዝር ከተወሰነ ግዜ በኋላ ይቀርባል።

በዚህ መንገድ ህወሓት በስልጣን የመቆየት ህልሙ ለማሳካት ጥረት እያደረገ ይገኛል። ህዝብን በማፈን ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይቻል ከደርግ ስርዓት መማር አለመቻሉ ያሳዝናል። በስልጣን ለመቆየት የሚረዳ የህዝብ ይሁንታ ነው። የህዝብ ይሁንታ የሚለካው በምርጫ ነው። ምርጫ የሚኖረው ደግሞ የህዝብ ነፃነት ሲኖር ነው። ህወሓት በደህንነት ሰዎቹ ላይ የተንጠለጠለ ህዝባዊ መሰረት የሌለው ዓፋኝ ስርዓት ሆነዋል። ከስር መሰረቱ እንደሚነቀል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ዜና ዕረፍት: የአሞራ አባት በድንገት አረፉ! – አብረሃ ደስታ በፌስ ቡክ እንደዘገበው

የጀግናው “አሞራ” አባት አቶ ነጋሽ ገብረሩፋኤል መጋቢት 20, 2006 ዓም በ80 ዓመታቸው በድንገት ማረፋቸው ታውቋል። አቶ ነጋሽ ወንድ ልጆቻቸው ለህዝብ ነፃነትና ደህንነት ሲሉ የህይወት መስዋእትነት በመክፈላቸው ምክንያት የሚረዳ አጥተው ባላቸው ዓቅም ሰርተው ለመብላት ዕንጨት ሲቆርጡ ድንገት ወድቀው ተጎድተው ለሕክምና የሚደርስላቸው ወገን በማጣታቸው ምክንያት ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል። አቶ ነጋሽ በትግራይ ማእከላዊ ዞን ቆላ ተምቤን ወረዳ ኗሪ ነበሩ። የአሞራ የትውልድ ቦታ ቆላ ተምቤን በህወሓቶች ከተበደሉ ወረዳዎች አንዷ ነች። ያከባቢው ኗሪዎች “ዓረና” እየተባሉ የመንግስት አገልግሎትና መሰረተ ልማት ተነፍገዋል። ፍትሕ አጥተዋል።
የኢቲቪ ጋዜጠኞች በወረዳው አስተዳዳሪዎች ታጅበው ከአቶ ነጋሽ ጋር (ለፖለቲካ ጥቅም) ቃለመጠይቅ ለማካሄድ ወደ ቆላ ተምቤን ተጉዘው ጉሮሮ በምትባል ትንሽ የገጠር ከተማ ሲደርሱ የአቶ ነጋሽን ሕልፈት ሲሰሙ በስርዓተ ቀብሩ ሳይገኙ ተመልሷል። ህወሓት አቶ ነጋሽን የሚፈልጋቸው ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ነበር ማለት ነው። የአቶ ነጋሽ ሞት በኢቲቪ አልተነገረም።
ህወሓቶች የልጃቸው አሞራን ታሪክና ጀግንነት ለፖለቲካ ፍጆታ ከማዋል ያለፈ ዕርዳታ አድርገውላቸው እንደማያውቁ ያከባቢው ኗሪዎች ገልፀዋል። የተሰው ልጆቻቸው መሬት በህወሓቶች ተነጥቀዋል። “አሞራ ፊልም” ሲሰራ አቶ ነጋሽ ቃለ መጠየቅና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ቃል ተገብቶላቸው ሲያበቃ ለህወሓት መሪዎች ጥቅም ሲባል ቃለ መጠይቁ ሲካሄድ ለአቶ ነጋሽ የተደረገ ድጋፍ ግን አልነበረም። ይልቁንስ የልጆቻቸው መሬት ተነጥቆ ለሌሎች ካድሬዎች ተሰጥቷል።
ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ሲባል ስለ አሞራ ታሪክ ይተረካል። አሞራ ያን መስዋእት ከፍሎ በሆነ ተአምር በህይወት ተርፎ አሁን “ለዴሞክራሲና ነፃነት ነበር የታገልኩትና የፈለኩትን ፓርቲ እደግፋለሁ፣ ያልፈለኩትን ፓርቲ ደግሞ እቃወማለሁ” ብሎ ዓረናን ቢደግፍ ኑሮ ከሃዲ ተብሎ በህፃናት በድንጋይ ይወገር ነበር። አሞራ እንኳን ጓዶች ህን እነ ስየና አስገደ አላየኋቸውም። በቃ በል በሰላም ተኛ።
የአቶ ነጋሽን ነፍስ በገነት ያኑርልን። ለቤተሰቦቻቸውን ፅናቱ ይስጥልን። R.I.P

ስለፍትሕ ሲባል፤ ሥርዓቱ ይፍረስ! (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )

April 11, 2014
ባለፉት አራት አስርታት ሀገሪቱ አያሌ ተግዳሮቶችን መጋፈጧ ባይዘነጋም፤ በተለያየ ጊዜ ሚሊዮኖችን ካረገፈው አሰቃቂው ረሃብ በማይተናነስ መልኩ ሕዝቦቿን ዋጋ ያስከፈለ ጉዳይ ቢኖር የፍትሕ አለመከበር ያስከተለው ሁለንተናዊ ምስቅልቅሎሽ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍሩ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ የየካቲቱን አብዮት ጠልፎ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊው ደርግ፣ የፍርድ ቤት ደጆችን በጓጉንቸር ቆልፎ ሲያበቃ፣ የራሱ አባላት እጃቸውን እያወጡ ድምፅ በመስጠት በአፄው ባለስልጣናትንም ሆነ ግብረ-አበሮቹ በነበሩ መኮንኖች ላይ የሞት ቅጣትን ያህል የመጨረሻ ከባድ ውሳኔ የማሳለፍን አስደንጋጭ ክስተት ጨምሮ፤ ከከተማ እስከ ገጠር ያደራጃቸው የአብዮት ጠባቂዎችና የገበሬ ማሕበራት ከየቤቱ አንቀው እያወጡ “ነፃ እርምጃ” እንዲወስዱ፣ ከየእስር ቤቱ እየለቃቀሙ በጅምላ እንዲረሽኑ በአዋጅ የፈቀደበት ጊዜ የፍትሕ ምኩራቡ ፈርሶ በግላጭ የተቀበረበት ዕለት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በርግጥ ይህ የማን-አለብኝነት አረመኔያዊ አገዛዝ የታቃውሞውን ጎራ በማጠናከር ታሪካዊ ውድቀቱ እንዲፋጠን ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ እንደነበር ለመረዳት 17 ዓመታትን መውሰዱ አይዘነጋም፡፡Temesgen Desalegn "Fact" Ethiopian Amharic newspaper editor
“ፍትሕ አልባው አምባ-ገነናዊ የደርግ ስርዓት አማርሮ በርሃ ያስወጣንና ብሶት የወለደን የለውጥ ሃዋርያት ነን፤ በመቃብሩም ላይ ፍትሕ-ርትዕ የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት አገር እንመሰርታለ” በማለት ከበሮ ይደስቁ የነበሩት የያኔው “ነፃ አውጪዎች”ም፣ ደርግ አፍርሶ የቀበረውን የፍትሕ ምኩራብ አመዱን አራግፈው ቢያነሱትም፤ ባነበሩት አስመሳይ ሥርዓት በኩል በዘውግ ማንነት፣ በሙስናና በሙያ አልባ ዜጎች በክለው ክብር የለሽ ሲያደርጉት በጣት የሚቆጠሩ ወራት እንኳ አልፈጀባቸውም፡፡ ‹‹አዲስ ንጉስ አንጂ ለውጥ መቼ መጣ!›› እንዲል ከያኒው፤ ካስወገዱት የደርግ መንግስት ጋር ልዩነታቸው-ደርጉ ያልቻለበትን የተቃውሞ ድምፆች በአዋጅ እንዲንቀሳቀሱ በአንድ በኩል ፈቅደው፣ በሌላ በኩል መልሶ ለመጨፍለቅ የፍርድ ቤቶችን ባረኮት የመጠቀም ባለ ሁለት ገፅ ብልጠታቸው ብቻ ነው፡፡
ይህ አይነቱ አገዛዝም ሥልጣን በያዘ ማግስት ሀገሪቱን እንዳሻው ለመርገጥ ሲቪል ቢሮክራሲውን ብቻ ሳይሆን የፍትሕ ስርዓቱንም በአምሳሉ አፍርሶ መስራት ነበረበት፡፡ ይሁንና ተቋሙን በዚህ መልኩ ለማዋቀር ጊዜ እንደሚያስፈልግ በመረዳቱ አሁን ድረስ በቂ መከራከሪያ ሊቀርብላቸው የማይችሉ ጉዳዮችን ከፍትሕ ሥርዓቱ ነጥቆ ሕገ-መንግስቱ ውስጥ በመዶል ለሌሎች ሰጥቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ማሳያ የሚሆነው፤ ሕገ-መንግስታዊነትን አስመልክቶ የሚነሱ የማጣራት ኃላፊነቶችን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መስጠቱ ነው፡፡ በርግጥ አንዳንድ የወቅቱ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ሕገ-መንግስቱ በተረቀቀበት ሰሞን፣ ከሕገ-መንግስቱ የሚጣረሱ አዋጆች፣ ክሶች አሊያም ኩነቶች ሲፈጠሩ፣ የማጣራቱ ኃላፊነት የፍርድ ቤት መሆን አለበት ሲሉ የተከራከሩ ድምፆች ነበሩ፡፡ ዳሩ ውሎ-አድሮ ምን እንደሚሰሩ አስቀደመው የሚያውቁት ታጋዮች፣ በዛ ካድሬ-ዳኞች ባላፈሩበት ወቅት እንዳሻቸው ሕገ-መንግስቱን እየናዱ ቢያስሩ፣ አዋጅ ቢያወጡና ቢያስፈርዱ ድጋፉን የሚሰጣቸው ተቋም፣ በኢሠፓውያን እንደተሞላ የሚጠረጥሩት ፍርድ ቤት ሳይሆን፣ እንደ ልብ ሊቆጣጠሩት የሚችሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን በመረዳታቸው፣ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ትመራለች በተባለች ሀገር ብዙም ባልተለመደ አኳኋን ሕገ-መንግስታዊ ትርጉም የሚሻቸውን ጉዳዮች የማጣራት ስራን ለዚሁ ምክር ቤት ሰጡት፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በጥቂት ዓመታት ውስጥ የፍትሕ ተቋሙን በፓርቲ ፖለቲካ የተተበተበ፣ ለጉልበተኛ የሚገብር፣ ገንዘብ ሊገዛው የሚችል፣ ተቀናቃኝ ድምፆችን የማፈኛ መሳሪያ… አድርጎ የመቅረፅ ዓላማቸውን ማሳካት ችለዋል፡፡ በውጤቱም ተቋሙ የህግ የበላይነት የተደፈጠጠበት አድሎአዊና በየጊዜው ደካሞችን የሚያጠቃ ከሆነ እነሆ ከሁለት አስርት በላይ አስቆጥሯል፡፡
የሆነው ሆኖ የሥርዓቱን ፍትሕ ረጋጭነት በተጨባጭ ፍፃሜዎች አስደግፎ ለማቅረብ ሁለት አብነቶችን እጠቅሳለሁ፡፡ ቀዳሚው የበርካታ ግፉአንን እሪታ ሲወክል፤ ተከታዩ ደግሞ የገዥዎቹን የሙስና እና የጓዳ ፖለቲካ ትስስሮች ይጠቁመናል ብዬ አምናለሁ፡፡
የሞገስ ወልዱ-ጩኸት
ሰማይ ከመፍገጓ በፊት፣ ሁሌ ንጋት ላይ ኮተቤ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ተነስቶ፣ በእግሩ ሰከም ሰከም እያለ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ግድም ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይደርስና ዋናው በር ፊት ለፊት ቆሞ ከአንድ ሰዓት ላላነሰ ጊዜ ‹‹ሌባ ዳኛ!›› እያለ ይጮኻል፡፡ ያፏጫል፡፡ ‹‹እናንተ ገላችሁኛል፤ ቀብራችሁኛል፤ አምላክ ፍርዱን ይሰጣል!›› በማለትም ተስፋው በሰማያዊው መንግስት ላይ ብቻ እንደሆነ ያውጃል፡፡ …ይህ ሰው እንደምን ያለ ከባድ በደል ቢደርስበት ይሆን ምሬቱ እንዲህ ጣራ የነካው?
አሳዛኙ የሞገስ ታሪክ እንዲህ ይጀምራል፡- በ1997 ዓ.ም የወላጅ እናቱን ወ/ሮ አስካለ ቢፋ ህልፈት ተከትሎ፣ ወንድሙ ኃይሉ ወልደአማኑኤል የወራሽነት ድርሻውን እንዲያካፍለው ክስ መስርቶ ሲያበቃ፤ ሶስት ጥያቄዎችን ለፍርድ ቤቱ ያቀርባል፡-‹‹ንብረትነቱ የእናታችን የሆነ ቀበሌ 14/15 ውስጥ የሚገኝ 250 ካሬ ሜ. ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት፣ ሁለት ማሳ የእርሻ መሬት እና በንግድ ባንክ አራት ኪሎ ስላሴና መገናኛ ቅርንጫፍ የተቀመጠ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብን ያካፍለኝ፡፡››
የከሳሽ ወንድም የሆነው ኃይሉም ፍርድ ቤት ቀርቦ ‹‹ቤትም ሆነ የእርሻ መሬት የሚባል ነገር የለም፤ በባንክ አለ ስለሚባለው ገንዘብም አላውቅም፤ እናታችን በሞተችበት ወቅት ስሟን ለማስጠራት ስል የእርሷ የነበረውን መሬት በ30 ሺህ ብር ሸጬ፤ ለአርባ፣ ለመንፈቅ፣ ለተስካር 10 ሺህ ብር ያወጣሁ ሲሆን፤ ቀሪውን 20 ሺህ ደግሞ ለወንድሜ ማረፊያ የሚሆን ቤት ሰርቼበታለሁ›› ሲል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ችሎቱም ‹ቤቱንና የእርሻ መሬቱን በተመለከተ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩን› ገልፆ ‹የ30 ሺህው ጉዳይ ግን ያለይግባኝ ባይ ፍቃድ ወጪ የተደረገ ስለሆነ፤ የገንዘቡ ግማሽ 15 ሺህ ብር ድርሻው ስለሆነ እንዲሰጠው› በማለት ወስኖ መዝገቡን ይዘጋል፡፡ በውሳኔው እጅግ በጣም የተበሳጨው ሞገስ፣ ጉዳዩን በይግባኝ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይወስደዋል፤ ይግባኝ ሰሚውም ‹‹ቤቱ ይገኝበታል›› የተባለው ቀበሌ የእናታቸውን ማህደር እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ግና፣ ሀገሪቷ ኢትዮጵያ ናትና፤ ቀበሌው ማህደሩ መጥፋቱን፣ ሟችም በተከሳሽ ቤት ይኖሩ እንደነበረ በደብዳቤ ያሳውቃል፡፡ ሆኖም ቀበሌው ይህንን ምላሽ ከሰጠ ከ14 ቀን በኋላ ‹የቀድሞውን አስተዳደር ጠይቄ ያገኘሁት መረጃ ነው› በማለት ለፍርድ ቤቱ እንዲህ የሚል ሌላ ደብዳቤ ይልካል፡- ‹ወ/ሮ አስካለ የግል መኖሪያ ቤት የነበራቸው ሲሆን፣ ቤቱ ያረፈበት መሬት ለ‹‹ሪል እስቴት›› በመሰጠቱ፤ ምትክ ቦታና ስድስት ሺህ ብር ወስደዋል›፡፡
የሰው ምስክሮችም ቀርበው ሟች እናት ቤት ሰርተው እንደነበረ ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም ሆኖ የወ/ሮ አስካለ ማህደር ከቀበሌው ‹‹ጠፍቷል›› በመባሉ ምንም አይነት ማስረጃ ስላልቀረበ የቀድሞው ውሳኔ በይግባኝ ሰሚው ችሎትም ሊለወጥ አልቻለም፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛው ፍርድ ቤት በር ላይ ቆሞ መጮኽን ስራዬ ብሎ ይዞታል፡፡ በርግጥ ከቀን ቀን አካላዊ መዳከም እየበረታበት መሄዱ በግልፅ ቢታይም የ40 ዓመቱ ጎልማሳ ሞገስ ወልዱ ዛሬም ከፍርድ ቤት ደጅ ቆሞ መጮኹና ማፏጨቱ የበርካታ ግፉአንን ድምፅ የሚወክል ይመስለኛል፡፡
ይህ ጉዳይ የሚያሳየው፣ የመንግስት ደመወዝ እየተከፈላቸው በዜጎች ሕይወት ላይ ሊወስን የሚችል እንዲህ አይነቱን ማስረጃ ያለአንዳች ጭንቀት ‹‹ጠፋ›› ብሎ ለመናገር የሚደፍሩ፣ ስለሕዝብ ብሶትና ችግር ምንም ግድ የሌላቸው ካድሬዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም እንደ ሞገስ ያሉ የፍትሕ እጦት ረመጥ ሆኖ ያንገበገባቸው ምስኪኖች በአደባባይ ሲጮኹ ውለው፤ ሲጮኹ ቢያድሩ ‹‹ምን ይሆን ችግራቸው?›› ብሎ ለማድመጥ የሚሞክር አንድ እንኳን ባለሥልጣን መታጣቱንም ጭምር ነው፡፡
‹‹ሳይሰሙ ቀርተው ይሆናል!›› ማለቱን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ፣ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ የሚተላለፉ መንገደኞችም ሆኑ ወደ ተቋሙ የሚመጡ ባለጉዳዮች ክስተቱን የማወቃቸው እውነታ ነው፡፡ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሰዎችን የችሎት ውሎ ለመሰለል ከተከሳሾች ቀድመው የሚደርሱ የደህንነት ሰራተኞችም ሞገስን ለማወቃቸው እኔው ራሴ ምስክር ነኝ፡፡
በአናቱም ከዚህ ቀደም በሸገር ራዲዮ ‹‹ኧረ በሕግ›› የሚል ፕሮግራም ያዘጋጅ የነበረውና በአሁኑ ወቅት በ97.1 ኤፍ.ኤም ‹‹የእኔ መንገድ›› የተሰኘ በተመሳሳይ ጭብጥ ዙሪያ የሚያተኩር ፕሮግራም የሚያዘጋጀው በሳሉ የሕግ ባለሙያ ሰለሞን ጓንጉል፣ ይህንን ታሪክ ከአንዴም ሁለቴ ለአድማጭ አድርሶታል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነው ከቀበሌ አንስቶ ላይ ድረስ ያሉ መንግስታዊ መዋቅሮችን የዘረጋውና የሚቆጣጠረው የኢህአዴግ አመራር አባላት፣ የሞገስን ጩኸት ‹‹አልሰሙም›› ማለቱን ከባድ ያደረገው (በነገራችን ላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ግቢ ለአስር አመት ያህል በየቀኑ እየተመላለሱ የሚቆሙ አንዲት አዛውንት እና በፍትሕ ሚኒስቴር በር ላይ ቆማ መዋል ከጀመረች ስድስት ዓመት ያለፋት ራሄል የተባለች አቤት ባይ እንስት… መኖራቸውን አልዘነጋሁም)
ሙስና እና የጓዳ ፖለቲካ ትስስሮሽ
አገሪቷ በዚህ ሁሉ መፍትሔ እጦትና በፍትሕ መዛባት እየተመሰቃቀለችና በሕዝቦቿም ዋይታ እየተናወፀች ቢሆንም፤ መጽሐፉ ‹‹ዓይን አላቸው አያዩም፤ ጆሮ አላቸው አይሰሙም›› እንዲል፤ ገዥዎቻችን ይህን መሰሉን የድሆችና የአቅመ ደካሞች ብሶት መስማትን ፍፁም አይሹም፡፡ እነርሱ የታጋሉትም ሆነ የሚሰሙት አለቆቻቸውንና ባለፀጋዎችን ብቻ እንደሆነ ከሚያሳዩን በርካታ ማስረጃዎች መሃል ለአብነት አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡-
ጉዳዩ በሙስና ተጠርጥሮ በእስር ላይ ከሚገኘው የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ዳይሬክተር መላኩ ፈንቴ ጋር ይያያዛል፡፡ ከዚህ ሰው ሃያ አንድ ገፅ ከፈጀ የእምነት ክህደት ቃል ውስጥ ኮነ ምህረቱ የተባለ ግለሰብ በአራጣ ማበደር ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ ‹‹እነአየለ ደበላ ለዳኛ ጉቦ ሰጥተው በዋስ ከእስር ተፈትተው፣ ከሀገር ለመውጣት ያስባሉ›› የሚል ‹‹መረጃ›› በመስጠት መተባበሩን ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ እንደነገረው ገልፆ፣ ከእስር እንዲለቀቅ መደረጉን እናገኛለን፡፡ መቼም በሙስና ወንጀል ከተጠያቂነት የሚድን ተከሳሽ የሚሰጠው መረጃ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ለመጠየቅ የሚጠቅም ሲሆን እንጂ፤ እንዲህ ባለ ከዋናው ክስ ጋር በማይዛመድ ተራና የአሉ-ባልታ ወሬ አለመሆኑን እነገብረዋህድና እነመላኩ ቀርቶ ማንኛውም መንገደኛ እንኳ ሊጠፋው አይችልም፡፡ አውቆ የተኛ… እንደሚባለው ካልሆነ በቀር፡፡
የሆነው ሆኖ ከመላኩ ፈንቴ የእምነት-ክህደት ቃል ትኩረት የሚስበው፣ ግለሰቡ በዚህ መልኩ ከሱ ተነስቶለት ከእስር ከተፈታ በኋላ ንብረቱና የባንክ ሒሳቡ መታገዱን አስመልክቶ የተፈጠረው ኩነት ነው፡፡ አቶ መላኩ ጉዳዩን ለመርማሪዎቹ ሲያብራራ ቃል-በቃል እንዲህ ነበር ያለው፡-
‹‹አቶ አባይ ፀሀዬ እና አቶ ደመቀ መኮንን ደውለው ‹ግለሰቡ አቤቱታ እያቀረበ ነው፡፡ ለምን አታዳምጡትም? ሲሉኝ፤ እኔም ከዚህ በኋላ ነው ግለሰቡን እቢሮዬ አግኝቼ ከላይ በገለፅኩት ሁኔታ እንዲስተናገድ ያደረኩት፡፡
እነዚህ ሰዎች ‹‹ነፃ አወጣነው›› የሚሉትን ሕዝብ ለስቃይ ዳርገው፣ ጥቂት ባለፀጎችን ብቻ ለማገልገል የቆሙ መሆናቸውን ለማስረገጥ ከዚሁ የእምነት-ክህደት ቃል አንድ ማሳያ ልጨምር፡- ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የተባለ የአዲስ ልብ ህክምና ክሊኒክ ባለቤት ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የሕክምና መሳሪያዎች (የልብ ፒስ ሜከር ተብሎ ተጠቅሷል) በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያስገባ በቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ ሠራተኞች እጅ ከፍንጅ ከተያዘ በኋላ መለቀቁን በተመለከተ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባል የሆነው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድህኖም ስልክ ደውሎ ‹‹ክሱን ብታነሱላቸውና በአስተዳደራዊ መፍትሔ ብትሰጧቸው›› ብሎ ከመንገሩም በላይ የግለሰቡ ክስ እንዲቋረጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ እንደፃፈላቸው መላኩ ፈንቴ ለመርማሪዎቹ መናገሩ በመዝገቡ ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህንን ሁናቴም ከወቅቱ የፖለቲካ አሰላለፍ አኳያ ስንተነትነው አቶ መላኩ ‹ዶ/ር ቴዎድሮስን መስማት፤ ህወሓትን እንደመታዘዝ ነው› የሚል እምነት አድሮበት የተባለውን ፈፀመ ብለን ብንደመድም ተምኔታውያን አያሰኘንም፡፡
እነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያውም ሀገር በሚጎዳ ወንጀል የተከሰሰ ተጠርጣሪን በተመለከተ ከሥልጣን ገደባቸው አልፈው ‹‹አድምጥ!›› እያሉ የማዘዛቸው ምስጢር ሥርዓቱ ለፍትሕ ያለውን ግድየለሽነት እና በዚህ ሥርዓት የሕግ የበላይነት ብሎ ነገር እንጦሮጦስ መውረዱን ፍንትው አድርጎ ያሳያል ብዬ አምናለሁ፡፡ በርግጥ ይህንን ጉዳይ ለጥጠን ከተመለከትነው ‹‹…ለምን አታዳምጡትም?›› የምትለዋን ቃል ሰምና ወርቅ የለበሰች ቅኔ አድርገን በመውሰድ ልንፈታት እንችላለን፤ በተለይም መላኩ ፈንቴ ከዚህች ጥያቄ መሰል ትዕዛዝ በኋላ ግለሰቡን ቢሮ ጠርቶ ማስተናገዱን ስናስተውል፡፡
ምንም እንኳን አባይ ፀሀዬ በጊዜው በጉዳዩ ላይ መላኩን ሊያዝበት የሚያስችል መንግስታዊ ሥልጣን /የዕዝ ተዋረድ/ ባይኖረውም፤ አንጋፋ የህወሓት አመራር አባልና የበለጠ የፖለቲካ ጉልበት ያለው መሆኑ፤ ደመቀ መኮንን ደግሞ በብአዴን በኩል የአለቃነቱ ነገር ሲታሰብ፣ አሁንም መላኩ ፈንቴ የተጠየቀውን ‹‹ጥያቄ›› ከማስተናገድ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖረውም ወደሚል ጠርዝ ይገፋናል፡፡ በርግጥ እውነታው ይህ ቢሆንም፣ መላኩ ዛሬም እስር ቤት ውስጥ ሆኖ የቀድሞ አለቆቹንም ሆነ ራሱን ተጠያቂ ለማድረግ አልደፈረም፡፡ በግልባጩ ለቀረቡበት ክሶች በሙሉ ተጠያቂው ገብረዋህድ እንደሆነ ከመናገሩም በላይ እንዲህ በማለት ወንጅሎታል፡-
‹‹የአያት ባለቤት በግብር ማጭበርበር ተከሶ በነበረበት ወቅት የተከሳሹ ቤተሰብ የሆነ ሰው እቢሮዬ መጥቶ ‹ገብረዋህድ ምንም ጥፋት ሳያጠፋ ነው የአያት አክሲዮን ማሕበር ባለቤትን ያሳሰረው፤ አሁንም አንድ ሚሊዮን ብር ካመጣችሁ ከእስር ይፈታል ብሎናል› የሚል ጥቆማ አመጣልኝ፡፡ …ገብረዋህድ እና ነጋ ገ/እግዚአብሔር (የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት ነው) ጓደኛሞች ናቸው፡፡ ነጋ ዕቃ ሲያስመጣ አያስፈትሽም፤ የነጋም ጓደኞች እነ አልሳም፣ ጌት አስ የመሳሰሉት ድርጅቶች ዕቃ በቀላል ቀረጥና ታክስ እንዲሁም አልፎ አልፎ ሳይፈተሹ ያልፋሉ፤ …ባለቤቱ ሃይማኖትም፣ በነጋ ድርጅት ውስጥ ትሰራለች…››
መላኩ ፈንቴ ይህንን ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መናገሩንና ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ፀጋዬ በርሄን ‹‹ተከታተል›› ብሎት እንደነበረ ከአስረዳ በኋላ እንደሚከተለው ይቀጥላል፡-
‹‹ገብረዋህድ በኋላ እንደነገረኝ ባለቤቱን ከነጋ ድርጅት አስወጥቶ በአዜብ ትዕዛዝ መሰረት ኤፈርት ውስጥ ያስቀጠራት መሆኑን ገልፆልኝ ‹አንተም ላይ የሚወራው ስለምትታገል ነው ብላኛለች አዜብ› ሲለኝ እኔም ተከታትዬ ፀጋዬ በርሄ ከምን እንዳደረሱት አልጠየኩም፡፡ መጠየቅ ነበረብኝ፤ ጥፋት ነው፡፡ በአጠቃላይ ገብረዋህድ ላይ ብዙ ነገር ይባል ነበር፡፡››
መቼም ይህ ምላሽ በ1981 ዓ.ም ከአስመራ ዩንቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ዲግሪውን፣ ከአውስትራሊያ በገቢ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪውን፤ ከለንደንም በቢዝነስ አስተዳደር በተመሳሳይ መልኩ ትምህርቱን ካጠናቀቀና የረዥም ዓመታት የስራና የፖለቲካ ተሞክሮ ካለው ሰው የተሰጠ መሆኑን ስናስተውል፤ ሀገሪቱ የአምባገነን ባለሥልጣናት መቀለጃ ብቻ ሳትሆን፤ የሰዎቹንም የአቅም ማነስ ያመላክታል፡፡ እንዲሁም እነሞገስ ሰሚ ያላገኙበትን ምክንያትም ሆነ በዚህች ሀገር ገንዘብ ያለው የፈቀደውን መፈፀም የመቻሉን ምስጢር ይገለፅልናል፡፡
ኢህአዴጋዊ ዕድሜ ማራዘሚያ…
ገዥው ስብስብ የፍትሕ ስርዓቱን ተቋማዊነት ሳይነካ፣ ለጨቋኝነቱ መጠቀሚያ የሚያደርግበት አንዱ መንገድ ከጠቅላይ እስከ ታች በተዋረድ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ድረስ ያሉ ዳኞችን የሚመድብበት አካሄድ ነው፡፡ በርግጥ እንዲህ አይነቱ ሀገርና ሕዝብ አልያም ሞራላዊ ልዕልና እና የሕግ-የበላይነት የማያስጨንቀው አገዛዝ፣ የፍትሕ ስርዓቱ ቅጥ የለሽ ተባባሪነት ሳይታከልበት የሥልጣን ዕድሜውን ማራዘም እንደማይችል መረዳት አይሳነውም፡፡ ይህን ለማድረግም ያለው ብቸኛ ምርጫ ዳኞቹን ከስሩ መሰብሰብ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ መሩ-መንግስት ሁለት አካሄዶችን ለመተግበሩ ያሳለፋቸው ሁለት አስርታት በሚገባ ያሳያሉ፡፡
የመጀመሪያው የሚሾሙት ዳኞች፣ የግንባሩ ከፍተኛ የካድሬ ማሰልጠኛ እንደሆነ ከሚነገርለት ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ተማሪዎች መካከል ማድረጉ ነው፡፡ ከዚህ ‹‹የትምህርት›› ተቋም ውስጥ የሚወጡ የሕግ ምሩቃን ደግሞ ስለጥልቅ ዘመናዊ የሕግ ፅንሰ-ሃሳብ ለማወቅ ከመትጋት ይልቅ፤ የኢህአዴግ ፖሊሲዎች እና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሕግን እንዴት ‹‹ለመደብ ጠላት›› መጠቀም እንደሚያስችሉ በሚሰብኩ መምህራን ስር እንዲያልፉ ይገደዳሉ (ስለመምህሮቹ ምሁራዊ ልሽቀት ለመረዳት የሕዝብ ሙስሊሙን ጥያቄ በሽብር ተግባር ለመፈረጅ እና ማሕበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት ለመወንጀል በ‹‹ጥናታዊ ጽሑፍ›› ስም የተጓዙበትን ርቀት ማየቱ ብቻ በቂ ይመስለኛል)፡፡ ተማሪዎቹም በዚህን መሰሉ የካድሬ ተቋም ስልጠና ስር ሰንብተው ሲወጡ፤ በፍፅምና ሊታመኑላቸው ይገቡ የነበሩትን ፍትሓዊ ዳኝነትና ህሊና የሚባሉ ጉዳዮችን ጨፍልቀው፣ በተለይም ፖለቲካዊ ነክ በሆኑ አይረቤ ክሶች ፊታቸው በሚቆሙ ንፁሀን ዜጎች ላይ መከራን የሚያዘንቡ አሽከሮች ይሆናሉ፡፡ ይህንን አስነዋሪነት ካለመታከት የሚፈፅሙትም፣ ሥልጣንን እና ተያያዥ ጥቅማ-ጥቅሞችን እያጋበሱ ወደ ከፍታ ሲወጡ ተመልክተናል፡፡
ሁለተኛው የግንባሩ አካሄድ ከካድሬ ማሰልጠኛውም ሆነ የተሻለ ነው ከሚባለው የአ.አ.ዩ. የሕግ ፋካሊቲ የሚመረቁትን፣ በተከታታይ ርዕዮተ-ዓለማዊ ጠመቃ የሥርዓቱ ጋሻ-ጃግሬ ማድረግ ላይ ያተኮረው ነው፡፡ በሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ሲያገለግሉ ቆይተው ስደትን የመረጡ ዳኞችና ዐቃቢ-ህግያት በተለያየ ጊዜ እንደ መሰከሩትም አሰልቺ የርዕዮተ-ዓለም ጠመቃ የፍትሕ ሥርዓቱን ነፃነት ጽልመት ካላበሱት ሂደቶች በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በአንድ ወቅትም ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ የሀገሪቱን ዳኞች ሰብስቦ ስለሕገ-መንግስት እና ሕገ አተረጓጎም መርህ ሲያስተምር ለማየት የተገደድነው የዚሁ የጠመቃው አንድ አካል በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ዳሩስ፣ ይህማ ባይሆን ኖሮ እስክንድር ነጋ ላይ 18 ዓመት መፍረድ ሕሊና እንዴት ይፈቅድ ነበር? ኦልባና ሌሊሳንስ ለ11 ዓመታት ወህኒ ያስወረወረው ጥፋት ምን ተብሎ በአሳማኝ መልኩ ሊጠቀስ ይችል ይሆን?