Thursday, 10 April 2014
“ንብረት የማፍራት መብት መገለፅ ያለበት በብሔረሰብ ደረጃ ሳይሆን በግለሰብ ነው” – አቶ ተክሌ በቀለ (የአንድነት ፓርቲ ም/ፕሬዝዳንት) – በዘሪሁን ሙሉጌታ
April 10th, 2014
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ሁለተኛውን የሕዝብ ንቅናቄ መጀመሩ የሚታወስ ነው። ፓርቲው ከዚህ ቀደመ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል መሪ ቃል የሕዝባዊ ንቅናቄ መድረኮች አዘጋጅቷል። አሁን ደግሞ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነት” በሚል መሪ ቃል ፕሮግራሙን ይፋ አድርጓል። ባለፈው እሁድ መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም በደሴ ከተማ ፕሮግራሙን በሰላማዊ ሰልፍ አከናውኗል።
በደሴ ስለተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍና “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነት” በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፓርቲውን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክሌ በቀለ፣ የፓርቲው የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ እና የፖርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ሰልፉን መርተውታል። ከመሬት ባለቤትነትና ከሰልፉ ጋር በተያያዘ የፓርቲውን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክሌ በቀለን አነጋግረናቸዋል።
ሰንደቅ፡- በደሴ ያካሄዳችሁት ሰላማዊ ሰልፍ ምን ያህል የተሳካ ነበር?
አቶ ተክሌ፡- መጀመሪያ ፕሮግራሙን ያሰብነው በሐዋሳ፣ በአዲስ አበባና በደሴ ከተሞች ነበር። እንደአጋጣሚ ሆኖ የደሴው በመሳካቱ ቅስቀሳ ስናደርግ ቆይተን ሰልፉን ለማካሄድ በቅተናል። የአዲስ አበባውና የሐዋሳው ለሌላ ጊዜ ተዛውሯል። የሐዋሳውን በራሳችን ምክንያት ያራዘምነው ሲሆን፤ የአዲስ አበባው ግን በአስተዳደሩ ችግር ምክንያት ነው።
የደሴው ሰላማዊ ሰልፍ እንደጠበቅነው በከፍተኛ ሞቅታ ነው ፕሮግራሙ የተጀመረው። በርካታ ሕዝብ ተገኝቶልናል። የሰልፉ አካል ሆኖ በመሐል መንገድ ላይ መፈክር እያሰማ ሲሄድ የነበረው የሕዝብ ብዛት ከ50 እስከ 60 ሺህ ገምተነዋል። ከሰልፉ ጎን ለጎን ዳርና ዳር የሚሄደው ሕዝብ በግምት መቶሺህ ይሆናል። በእኛ እምነት ሕዝቡ በመሬት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመሬት ጉዳይ የሚያስከፍላቸውን ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመገንዘብ ከፍተኛ የሆነ መነሳሳት አሳይቷል። በተደረገው የሁለት ቀን ቅስቀሳ ያን ያክል ሕዝብ መውጣቱ የሕዝቡም ስሜት ከፍተኛ እንደነበር ያሳያል። በዚህ ወቅት እኔን ያስታወሰኝ በ2002ቱ መርጫ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “ደሴም ሳይቀር አሸንፈናል” ብለው ነበር። አሁን ሳየው ግን የኢህአዴግ የምርጫ ኮንትራት ሳያበቃ ይሄን ያክል ሕዝብ ወጥቶ “በቃኝ” የማለቱ ሁኔታ ሲታየ ምርጫውን እንዴት ነበር ያሸነፉት ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል።
ሰንደቅ፡- መሬት የፖሊሲ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ከሰላማዊ ሰልፍ ይልቅ በሕዝባዊ ውይይት ማካሄዱ ይሻላል፤ አለበለዚያ በትንሹም በትልቁም ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት የፓርቲውን ደጋፊዎች ያሰለቻል የሚል ነገር እየተነሳ ነው። ለዚህ ኀሳብ ያለዎት ምላሽ ምንድነው?
አቶ ተክሌ፡-ፕሮግራሙ ሲጀመር የመረጥናቸው ከተሞች ነበሩ። አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ የሀገሪቱ ምሁራን የሚገኙበት የአዳራሽ ውስጥ ስብሰባ አቅደን ነበር። ወደ አደባባይ እየገፋን ያለው ኢህአዴግ ነው። መሬትና ከመሬት ጋር ተያይዞ ለሚፈጠሩ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና የፍትህ ችግሮች በተመለከተ በሰላማዊ ሰልፍና በሕዝባዊ የአዳራሽ ስብሰባ ለይተን ነበር። ነገር ግን ገና ከመጀመሪያው አዲስ አበባ ላይ አዳራሽ ማግኘት ተቸግረናል። የመንግስት አዳራሾች ብቻም ሳይሆን በገንዘባችን ከፍለን የሆቴሎችን አዳራሽ ማግኘት አልቻልንም። ወደ ጎዳና እየገፋን ያለው ገዢው መደብ ነው።
ሰንደቅ፡- የመሬት ችግር በከተማና በገጠርም የተለያየ ነው። በሀገሪቱም የችግሩ አይነትና መጠንም የተለያየ ነው። በቀላሉ የሕዝብ ድጋፍ አላችሁ ተብሎ በሚገመተው ደሴ ከተማ ከማካሄድ ይልቅ በደቡብና ኦሮምያ ክልሎች ለምን እንቅስቃሴውን አልጀመራችሁም?
አቶ ተክሌ፡- በአጠቃላይ በመሬት ላይ ያለን እይታ ሦስት አይነት ነው። መሬት በግል፣ በወል ወይም በመንግስት ስር መሆን አለበት የሚል የመሬት ስሪት አቋም አለን። ኢህአዴግ ደግሞ መሬትን በተመለከተ የሚያስቀምጠው ከእኛ ፍፁም የተለየ ነው። በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 40 ንዑስ ቁጥር ስድስት ላይ መሬት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንደሆነ አድርጎ ነው የሚያስቀምጠው። ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ ወዘተ እንጂ ንብረት በማፍራት መብታቸው ሊገለፅ አይችልም። ንብረት የማፍራት መሠረታዊ መብት መገለፅ ያለበት በብሔረሰብ ደረጃ ሳይሆን በግለሰብ ነው። ኢህአዴግ ብሔር ብሔረሰቦች የሚያቋቁሙት መንግስት ነው ብሎ ስለሚያምን በተዘዋዋሪ መሬት የመንግስት እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ይህ ማለት ደግሞ በብሔር ብሔረሰቦች ስም መሬትን ወይም የሕዝብን ንብረት ጠቅልሎ ኢህአዴግ ወስዶታል ማለት እንችላለን። በሌላ አነጋገር ግለሰቦች ከመሬት ባለቤትነት ውጪ ሆነዋል ማለት ነው። በእኛ እምነት የከተማ መሬት የግለሰቦች መሆን አለበት ብለን እናምናለን። የገጠሩ ደግሞ አስቀድሜ እንደነገርኩህ በግል፣ በወል ወይም በጋራ እና በመንግስት መያዝ አለበት።
ወደ ጥያቄህ ስመጣ አጠቃላይ የኢህአዴግ የመሬት ፖሊሲ በብሔር ብሔረሰቦች ሽፋን ከመውሰዱ አንፃር ችግሩ የመላ ሀገሪቱ ነው። ስለዚህ በደሴም ጀመርከው በደቡብ ችግሩ አንድና ተመሳሳይ ነው። በእርግጥ በደሴ የጀመርነው የተሻለ ተቀባይነት አለን በሚል መነሻ ብቻ አይደለም። አንድነት አጠቃላይ ሕዝቡ ከተቃዋሚው ጎራ ጋር እንደወገነ እንረዳለን። ኢህአዴግ የሚዘጋብን ሕዝቡ እንደሚደግፈን ስለሚያውቅ ነው። በእርግጥ አንድነት ያልደረሰባቸው፣ ሌሎች ተቃዋሚዎች ጠንካራ ስራ የሚሰሩባቸው ቦታዎች ይኖራሉ። ያም ሆኖ ስንጀምረው አዲስ አበባና ሐዋሳ ነበር። ደሴ አልነበረም።
ሰንደቅ፡- ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎች በመሬትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የጠራ ፖሊሲ የላቸውም እያለ ነው። በእናንተ እምነት በአሁኑ ወቅት የጠራ ፖሊሲ አለን ብላችሁ ታስባላችሁ?
አቶ ተክሌ፡- በመሬት ላይ ብቻ አይደለም። በአጠቃላይ ከመሬት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች በርካታ ናቸው። የሀገሪቱ አንጡራ ሀብት መሬት እንደሆነ አንረዳለን። ዋነኛ ትኩረታችንም የመሬት ምርታማነት፣ ባለቤትነትና ልማት ነው። ከገዢው ፓርቲ ጋር ካሉን የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የአከባበር ልዩነቶች ባሻገርም አንዱና ዋነኛው መሬት ነው። ከሀገሪቱ የችግር ምንጮች ውስጥ አንዱ የመሬት ባለቤትነት ነው። ስለዚህ በዚህ ዙርያ ያሉ ችግሮችን ተረድተናል። ችግሮቹን በመረዳታችንም የጠራ ፖሊሲ ቀርፀናል። ከመሬት ባሻገርም በፋይናንስም በለው፣ በግብርናም ሆነ በውጪ ጉዳይ በማኅበራዊ ጉዳዮች ሀገሪቷዋን ከድህነትና ኋላቀርነት ያወጣል ብለን እናምናለን። ችግራችን የቀረፅናቸውን አማራጭ ፖሊሲዎች ለሕዝብ ማድረስ የምንችልበት የሚዲያ እና ወደ ሕዝቡ የምንቀርብበት መድረክ መዘጋቱ ነው። እና ኢህአዴግ “ተቃዋሚዎች አማራጭ የላቸውም” የሚለው አባባል ድሮ የቀረ ተረት ተረት ነው።
ሰንደቅ፡- በተቃዋሚዎች በኩል ወጥ የሆነ የመሬት ፖሊሲ አይስተዋልም። በተለይ በኦሮሞ ብሔር የተደራጁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሬት የመንግስት ይሁን የሚል ዝንባሌ አላቸው። ሌሎቻችሁ ደግሞ “መሬት ይሸጥ ይለወጥ” እስከማለት ትደርሳላችሁ ይህ ደግሞ በምርጫ ወቅት አያስቸግርም?
አቶ ተክሌ፡- ተመሳሳይ ፕሮግራም ያላቸው ፓርቲዎች ውህደት ፈጥረው በአንድ ላይ ቢንቀሳቀሱ ችግሩ ሊፈታ ይችላል። የግል ስልጣንና የቡድናዊ ጥቅምን አስወግደው ወደ ውህደት ቢመጡ መልካም ነው። አሁን ፓርቲዎች ሚዛን በማይደፉ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ቢሆንም፤ ያነገቡት ፕሮግራም የተለያየ አይደለም፤ በመሆኑም ሕዝቡ የተለያዩ ፓርቲዎችን ቢመርጥም የሚመረጠው ፕሮግራም ግን ተቀራራቢና በአመዛኙ አንድ አይነት ነው ለማለት ያስደፍራል። በእርግጥ ከመድረክ ጋር በተያያዘ አንዱ ልዩነት የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን በመለስተኛ ፕሮግራማችን ላይ መሬትና ያልተፈቱ ሌሎች ጥያቄዎችን ሕዝቡ እንዲፈታቸው ተስማምተናል። ነገር ግን ሕዝቡ ደግሞ ደሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶቹን ሙሉ በሙሉ አልተጎናፀፈም። መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ያልተጎናፀፈ፣ ሕዝብ ዋነኛ በሆኑ የሕዝብ ችግሮች ላይ መፍትሄ ለማምጣት መጀመሪያ የተነፈገውን መብት ማግኘት አለበት የሚል መረዳት አለ። በመሠረቱ የተጠቀሱት የኦሮሞ ድርጅቶችም መሬት የመንግስት ይሁን ሳይሆን፤ ሕዝቡ ይወስን እያሉ ነው። አረናን ብትወስደው መሬት የግል ቢሆንም፤ መሸጥ መለወጥ የለበትም ይል እና ጉዳዩ የሕገ-መንግስት ማሻሻያን የሚጠይቅ እንደመሆኑ ሕዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። በድምሩ ስታየው መሬትን በተመለከተ በተቃዋሚዎች ካምፕ ያለው መረዳት የሚያራራቅ ሳይሆን ሊታረቅ የሚችል ጉዳይ ነው።
ሰንደቅ፡- ፓርቲያችሁ በአሁኑ ወቅት የመሬትን ጉዳይ ያነሳው ለምንድን ነው?
አቶ ተክሌ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የስልጣን መባለግን ጨምሮ ከፍተኛ የሙስና ምንጭ የሆነው መሬት ነው። የመሬት ጉዳይ የፍትህ እጦትና የመልካም አስተዳደር ችግር መገለጫዎች አንዱና ዋነኛው ነው። ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አዝጋሚነትና ለማኅበራዊ ችግሮች ምንጩ የመሬት ባለቤትነትና የይዞታ አስተዳደር ችግር ነው። ይህንን እኛ ብቻ ሳንሆን እራሱ ገዢው ፓርቲ የሚያምንበት ጉዳይ ነው። በዚህ ወቅትም ጉዳዩን ልናነሳው የቻልነው ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች ላይ ግንዛቤ ለመጨበጥ፣ ባለን ፖሊሲም ላይ እንደ ግብአት የሚያስፈልግ ነገር ካለም ለማካተት ነው። በዋናነት ግን የሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች መገለጫ መሆኑን፣ የኢህአዴግ የመሬት ፖሊሲ የተሳሳተና ያስከተለውንም በሙስና የመጨማለቅ ሁኔታን ለማሳየት ነው።
በአሁኑ ወቅት መሬት በኢንቨስትመንት ስም የሙስና መንጭ ሆኗል። ግለሰብ በግለሰብነቱ ከመሬት ባለቤትነት ከራቀ በፖለቲካ ዓይን ስታየው የካድሬዎች መጫወቻ ይሆናል። ይህንን ማረጋገጥ የሚቻለው በተለያዩ ጊዜአት መንግስት የሚያስራቸው ባለስልጣናቱን እያየን ነው።
ሰንደቅ፡- በቀጣይ የምታካሂዱት እንቅስቃሴስ ምን ይመስላል?
አቶ ተክሌ፡- በትላልቅ ከተሞች በተለይም ምሁራንን በቀላሉ በምናገኝበት ቦታ የአዳራሽ ስብሰባዎች እያደረግን፣ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ይደረጋል። በገጠር ደግሞ በወረዳ ደረጃ የሚሰሩ ስራዎች አሉ። ሰላማዊ ሰልፎቹም በተመረጡ ከተሞች ይቀጥላሉ። እንደነገርኩህ መሬትን በተመለከተ ሕዝቡ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ዋነኛ ዓላማችን ነው። በገጠሩም በከተማም ሰፊ እንቅስቃሴ እናደርጋለን ብለን አቅደናል።
ሰንደቅ፡- ይህ መሬትን ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ በቀጥታ ከ2007ቱ ምርጫ ጋር የሚያያይዘው ነገር አለ?
የአዲስ አበባ መስተዳድር የእውቅና ደብዳቤ ጻፈ ፓርቲው አልተስማማም::
April 10th, 2014
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ለመጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም ሊያደርገው ለነበረው ሰላማዊ ሰልፍ የመስተዳድሩ የሰላማዊ ሰልፍና ማሳወቂያ ክፍል ዘግይቶ በጻፈው ደብዳቤ የሰልፉ ቀን በሌላ ፕሮግራም መያዙን በመጥቀስ የቀን ለውጥ እንዲደረግ መጠየቁ አይዘነጋም፡፡
ፓርቲው የቀረበውን አስተያየት በመቀበል ሰልፉ ለሚያዚያ 5 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲደረግ መወሰኑን በመግለጽ ለመስተዳድሩ አሳውቋል፡፡ሆኖም መስተዳድሩ ዕለቱ በታላቁ ሩጫ መያዙን በመጥቀስ ለፖሊስ ጥበቃ ለመስጠት የሚያስቸግረው በመሆኑ ሰልፉ ለሚያዚያ 4 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲደረግ የእውቅና ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ፓርቲው በመስተዳድሩ የተሰጠውን እውቅና አለመቀበሉን ለማሳወቅ ከፍተኛ አመራሮቹን ወደ ከንቲባው ጽ/ቤት ልኮ የአንድነት አመራሮቹና የመስተዳድሩ ሰዎች በጉዳዩ ዙሪያ የተነጋገሩ ሲሆን ዝርዝሩን እንደደረስን አንገልጻልን፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ለመጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም ሊያደርገው ለነበረው ሰላማዊ ሰልፍ የመስተዳድሩ የሰላማዊ ሰልፍና ማሳወቂያ ክፍል ዘግይቶ በጻፈው ደብዳቤ የሰልፉ ቀን በሌላ ፕሮግራም መያዙን በመጥቀስ የቀን ለውጥ እንዲደረግ መጠየቁ አይዘነጋም፡፡
ፓርቲው የቀረበውን አስተያየት በመቀበል ሰልፉ ለሚያዚያ 5 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲደረግ መወሰኑን በመግለጽ ለመስተዳድሩ አሳውቋል፡፡ሆኖም መስተዳድሩ ዕለቱ በታላቁ ሩጫ መያዙን በመጥቀስ ለፖሊስ ጥበቃ ለመስጠት የሚያስቸግረው በመሆኑ ሰልፉ ለሚያዚያ 4 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲደረግ የእውቅና ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ፓርቲው በመስተዳድሩ የተሰጠውን እውቅና አለመቀበሉን ለማሳወቅ ከፍተኛ አመራሮቹን ወደ ከንቲባው ጽ/ቤት ልኮ የአንድነት አመራሮቹና የመስተዳድሩ ሰዎች በጉዳዩ ዙሪያ የተነጋገሩ ሲሆን ዝርዝሩን እንደደረስን አንገልጻልን፡፡

የቶሮንቶና የነቀምት ግንባር፣ የአንድነት የሶስት ወር ዘመቻ
April 10, 2014
የማርቆስ ብዙነህ ደብዳቤ፤
1- “በርካታ ትምህርት ቤቶች፤ ዩኒቨርስቲና የመንግስት ተቋማት በሚገኙበት አካባቢ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የማይቻል በመሆኑ፤ የተጠየቀው የሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ጥያቄ ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን እንገልጻለን” ይላል፤ በአዲስ አበባ መስተዳድር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቅ ክፍል ሀላፊ፤ በአቶ ማርቆስ ብዙነህ ማንደፍሮ፤ መጋቢት 23 ቀን 2006/2014 የተፈረመው ደብዳቤ፡፡ አንድነት፤ ሰልፉን ለማድረግ ያቀረባቸው መስመሮች 3 ሲሆኑ፤ ሶስቱም መስመሮች ከቀበናው የአንድነት ጽ/ቤት ይነሳሉ፡፡ አንደኛው መስመር በአራት ኪሎና በፒያሳ አድርጎ፤ ወደ አዲስ አበባ መስተዳድር ጽ/ቤት ያመራል፡፡ ሁለተኛው አማራጭ በአራት ኪሎ ተጉዞ፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን አልፎ መስቀል አደባባይ ያበቃል፡፡ ሶስተኛው አማራጭ፤ በአራት ኪሎ ፒያሳ፤ ቸርችልን ይዞ ድል ሀውልት ጋር ያበቃል ነበር የሚለው፡፡ ከላይ እንደተመለከታችሁት፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር፤ ሶስቱም አማራጮች አልተመቹትም፡፡ የተመረጡት መስመሮች በርካታ ትምህርት ቤቶች የትምህርትና የመንግስት ተቋማት ስለሚገኙበት፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ግንባታ ያለባቸው መንገዶች ስለሆኑ፤ እንዲሁም በእለቱ የህዳሴው ግድብ ግንባታን የተመለከቱ ዝግጅቶች ስላሉ፤ መስተዳድሩ ሰልፉን ሳይፈቀድ ቀረ፡፡
2- አንድነት ክልከላው ሕገወጥ ነው፤ ሰልፋችንን እንቀጥልበታለን ብሎ አቋሙን ሲያሳውቅ፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ዘግይቶም ቢሆን፤ ተለዋጭ ቀንና መንገድ እንደሚቀበል ጠቆመ፡፡ ወትሮም ቢሆን የአዲስ አበባ መስተዳድር የተከተለው ስልት የማዳከም፤ የማበሳጨት፤ የማሰናከልና ተስፋ የማስቆረጥ እንጂ ጨርሶ የመከልከል አይመስልም፡፡ ስለዚህም ድርጅቱ በተዘጋጀበትና በመረጠው ቀን ባይሆንም፤ በሌላ ቀን እንዲሆን ለመለወጥ አስገደደ፡፡ በርግጥ የአዲስ አበባ መስተዳድር የመጀመሪያውን ሰልፍ ያሰናከለበት ምክንት አግባብ ባይሆንም፤ የአንድነት ልሳን ፍኖተ-ነጻነት፤ የአዲስ አበባ መስተዳርን የዘገየ እሺታ አስጩሆ የዘገበበት መንገድ ብልሀት ይጎድለዋል፡፡ ፍኖት ነጻነት፤ “በመጨረሻ የአዲስ አበባ መስተዳድር እጅ ሰጠ” ነው ያለው፡፡ ይሄ አይነቱ ረታናችሁ፤ አሸነፍናችሁ አካሄድ መንግስት የሚያሸሽ ስለሆነ፤ ፍኖተ ነጻነት ከዚህ አይነቱ አናዳጅ ርእሰ-ዜና መራቅ አለበት፡፡ ኢሳትም ይሄን አይነት ሰራንላችሁ፤ የታባታችሁ የሚል አዋራጅ አዘጋገብ አልፎ አልፎ ይተገብራል፡፡ ፈጣሪ ጊዜና ጉልበት ከሰጠኝ፤ ይሄ አይነቱ ጠላትን የማዋረድና የጽንፈኝነት አካሄድ ለምን እንደሚጎዳ እጽፋለሁ፡፡ ለጊዜው የፍኖተ ነጻነት ርእስ እንዳልተመቸኝ ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡
ስለሕገመንግስት፤ መብት ተረጋግጧል ወይስ ተረግጧል
3- የሆነ ሆኖ፤ ወደሰልፉ ጉዳይ ስንመለስ፤ አሁን በስራ ላይ ባለው የኢትዮጵያ ሕገመንግስት መሰረት፤ ዜጎች በመሰላቸው ርእስ፤ በጣማቸው ምክንያት፤ በታያቸው ሕልም፤ በተሰማቸው ደስታ፤ ባሳዘናቸው ሰበብ፤ መንግስትን ደግፈውም ይሁን ተቃውመው፤ ሀሳባቸውን በተቃውሞ ወይም በድጋፍ የመግለጽና የመሰብሰብ መብታቸው ተረጋግጧል፡፡ ሕገ-መንግስቱ ራሱን በራሱ ያስፈጽም ይመስል፤ ሕወሀት/ኢህአዴግ ብዙውን ግዜ እንዲህ ያለው መብት በሕገ መንግስቱ ተከብሯል፤ በሕገመንግስቱ ተረጋግጧል እያለ የሚያጭበረብረው ነገር ስላለ፤ ይሄንን የተቃውሞ ሰልፍ በህገመንግስቱ ተከብሯል የሚል አረፍተነገር የተመለከተ ሰው፤ ጥንቃቄ ካላደረገ በስተቀር በሀይለኛው ይሳሳታል፡፡ በሕገ መንግስቱ መሰረት፤ ተረጋግጧል የሚለው ቃል፤ ተከብሯል በሚለው መተርጎም ቢኖርበትም፤ በኢትዮጵያ በተግባር እንደምናየው ግን፤ ተከብሯል በሚለው ሳይሆን፤ በሕገመንግስት ተረግጧል በሚለው ቢተረጎም ይቀላል፡፡ መብቱ በሰበብ አስባቡ ተሸራርፏል፡፡ በአንድነትና በሰማያዊ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ላይ የሚደርሰውን ለተመለከተ ይሄንን መረዳት አያዳግተውም፡፡
4- ለምሳሌ ሕገመንግስቱ ሰልፍ ከማድረግ በፊት ለሚመለከታቸው አካላት ስለማሳወቅ ብቻ ሲናገር (የአቶ ማርቆስ ብዙነህ ማህተም የሰልፍና ስብሰባ ማሳወቅ ኦፊሰር ነው ይላል)፤ ህግ አውጪዎቹና አስፈጻሚዎቹ ደግሞ፤ የለም ሰልፍ አሳውቅ ሳይሆን አስፈቅድ ነው ብለው ተረጎሙት፡፡ መተርጎም ብቻ ሳይሆን፤ ሕገ መንግስቱ ያረጋገጠውን መብት፤ ሰልፍን የተመለከቱ አዋጆችና ደንቦች አውጥተው ረጋገጡት፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ መስተዳድር የስብሰባና ሰልፍ አሰራር ስነ-ስርአት አንቀጽ 5.1 ከላይ በተጠቀሱት የመንግስትና የትምህርት ተቋማት አካባቢ ሰልፍ ማድረግ አይቻልም ይላል፡፡ በካናዳ ቢሆን፤ እነዚህን ሕገመንግስታዊ መብት የሚሸራርፉ አዋጆችና ደንቦች፤ ፍርድቤቶች ዋጋ የለሽ ህጎች ብለው ይወስኑባቸው ወይም ያመክኗቸው ነበር፡፡ እኛ አልታደልንምና፤ እስካሁን እንዳየነው፤ የኢትዮጵያ ፍርድቤቶች እንዲህ ያለውን ሕግ የመሻር ወይም፤ ሕገመንግስቱን ይጥሳል ብለው የመወሰን ስልጣንም ወኔውም አልተመለከትንባቸውም፡፡ ከተመለከትንም፤ ወይ ፍርዱ ወይ ዳኛው አይጸናም፡፡ መንግስት እንዲህ ነው ካለ፤ የኢትዮጵያ ፍርድቤቶችም አብረው እንዲያ ነው ይላሉ፡፡ ከመንግስት ጋር ይስማማሉ፡፡
የት ሄደን እንሰለፍ፤ ነው ወይስ እንሰየፍ
5- ሰልፍ 48 ሰዓት ቀደም ብለህ አሳውቅ የሚለው ድንጋገጌ ሰልፍ አስፈቅድ በሚለው አዋጅ ተሸርፎ ብቻ አላቆመም፡፡ ከአንድነትና መኢአድ እንዲሁም ሰማያዊ ፓርቲ ስኬታማ ሰልፎች በኋላ ደግሞ ሰሞኑን የምንመለከተው፤ ጭራሽኑ ሰልፍ መሰለፊያ ስፍራ የሚያሳጣ ሁኔታ እንዳለ ነው፡፡ ቀደም ሲል ሰልፍ የተከለከለባቸው ስፍራዎች የጦር ሰራዊት ካምፖች፤ ሆስፒታሎችና መሰል ስፍራዎች ነበሩ፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ በትምህርትቤቶች ወይም ዩኒቨርስቲዎች አካባቢም ሰልፍ ማድረግ አይቻልም የሚል ደንብ ወጣ፡፡ ቀጥሎ በእምነት ተቋማት ማለትም በመስጊድና በአብያተክርስቲያናት አካባቢ አይቻልም የሚል አዋጅ/ደንብ ይመጣል፡፡ በአዲስ አበባ በሁሉም ማእዘን ቢኬድ፤ ትምህርትቤት ባይኖር፤ ሆስፒታል አለ፤ ሆስፒታል ባይኖር፤ የጦር ካምፕ አለ፤ የጦር ካምፕ ባይኖር፤ ቤተ-እምነት አለ፤ ቤተ-እምነት ባይኖር፤ ዩኒቨርስቲ አለ፤ ዩኒቨርስቲ ባይኖር መዋእለ-ሕጻናት አለ፤ ያም ባይኖር የሆነ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ሰለፍ ሊደረግ የሚችልባቸው ስፍራዎች ውሱን በጣም ውሱን ሊሆኑ ነው፡፡ ደግሞስ የተቃውሞ ሰልፍ አንድም መንግስት እንዲሰማው ለማድረግ ሆኖ ሳለ፤ በመንግስት ተቋም አጠገብ መሰልፍ አይቻልም የሚሉት ደንብ እንዴት ያለ ደንብ ነው፡፡ ተቃጠልን እኮ ጎበዝ፡፡
የአንድነት የሶስት ወር ዘመቻ
6- እንግዲህ በዚህ ሁሉ ሕገመንግስቱን የሚሸራርፉ የተጻፉ ደንቦችና አዋጆች፤ ያልተጻፉ አፋናዎችና ትንኮሳዎች ውስጥ ተሸሎክሉከው ነው፤ አንድነቶችና ሰማያዊዎች የተቃውሞ ሰልፎችን የሚያደርጉት፡፡ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ፤ (ከዚህ በኋላ አንድነት እያልኩ ነው የምጠራው)፤ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ ከአዲስ አበባ ተጀምሮ አዲስ አበባ የሚያበቃ፤ በ15-17 ከተሞች የሚደረግ፤ የኑሮ ውድነትን፤ የሰብአዊ መብት ጥሰትና አፈናና፤ የመሬት ባለቤትንትን፤ የሚመለከቱ የተቃውሞ ሰልፎችን አሰናድቷል፡፡ አንድነት በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የሚደርጋቸውን ሰልፎች በገንዘብ ለመርዳት በውጭ አገር የሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ኢትዮጵያዊያን ቃል እየገቡ ነው፡፡ መቼም ሲያትል ጎንደሬ ይበዛል፤ ጎንደርን ወስዷል፡፡ አትላንታ አንድ ከተማ ወስዷል፡፡ ላስ ቬጋስም እንደዚያው፡፡ እስካለፈው ወር መጨረሻ ድረስ የቀሩት ከተሞች አምስት ብቻ ናቸው፡፡ የቶሮንቶ አንድነት የድጋፍ ሰጪ ማህበርም የነቀምት ከተማን ሰለፍ ለመርዳት ቃል ገብቷል፡፡ ቀደም ሲል እሁድ ማርች 23 ቀን የአንዱዓለም አራጌን መጽሀፍ ለማከፋፈልና እስረኞችን ለማሰብ በተጠራ ዝግጅት ላይ የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ ታምራት ይገዙ ቶሮንቶ መቀሌንም ስፖንሰር እንደሚያደርግ አስታወቋል፡፡ ስለዚህ፤ ቶሮንቶ ሁለት ከተሞችን ስፖንሰር ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ይሄ በረከት ሲያንሰን ነው፡፡
እነሆ ቅስቀሳ፤ አጋርነት ለነቀምት፤
7- አንድነት ቶሮንቶ፤ ለነቀምቱ ሰልፍ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ቅዳሜ ኤፕሪል 26 ቀን፤ ከሰዓት በኋላ፤ ከ3pm ሰኣት ጀምሮ፤ 2050 ዳንፎርዝ ጎዳና ላይ በሚገኘው ሂሩት ካፌ፤ የአብረን እንዋል መርሀግብር አዘጋጅቷል፡፡ ይሄ ጽሁፍ በከፊል የዚያ ዝግጅት ቅስቀሳ አካል ነው፡፡ ልቀስቅሳችሁ ተዘጋጁ፡፡ ቅስቀሳው እንዲህ የሚል ነው፤ አገር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፤ ከላይ የጠቀስናቸውን መሰናክሎች አልፈው የተቃውሞ ሰልፍ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ሲሉ፤ ሰልፋቸው በኢህአዴግ ሰራዊት ወይም ፖሊስ ወይም ደህንነቶች እንጂ፤ በገንዘብ እጦት ምክንያት እንዳይሰናከል የማድረግ ግዴታ አለብን የሚል ነው፡፡ በቶሮንቶ አካባቢ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን፤ በዚህ መደበኛ ባልሆነ፤ የአብረን እንዋል ዝግጅት ላይ በመገኘት፤ የበኩላችንን የገንዘብ ልገሳ እንድናደርግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ፤ ቅዳሜ ኤፕሪል 26 ቀን፤ 2014 ዓ.ም፤ ከሰኣት በኋላ፤ ሂሩት እንገናኝ፡፡
8- በነገራችን ላይ፤ ቶሮንቶ በቆየሁባቸው ያለፉት 13 ወራት፤ ከገንዘብ ማሰባሰብ ጋር በተያያዘ ቶሮንቶ የሚንቀሳቀሰው ከአቅም በታች ነው ማለት ይቻላል፡፡ ትንሽ ቋጣሪ መስሎብኛል፡፡ በርግጥም በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሚደረጉ ፖለቲካ ነክ ዝግጅቶች ላይ የሚታደሙትንና ያላቸውን የሚወረውሩት ቸሮች፤ ተመሳሳይና የተወሰኑ ሰዎች በመሆናቸው፤ የዚህ ከአቅም በታች የመንቀሳቀስ ተጠያቂዎች እነማን እንደሆኑ እንጃ፡፡ ላለፈው ስርየት ሆኖ፤ ስለሚመጣው ሳስብ ግን፤ እኔ እንዲህ ያለውን አገራዊ ዝግጅት የማየው እንደበረከት ነው፡፡ ይሄ በረከት ለሁላችሁም መድረስ አለበት፡፡ ስለዚህ የመጪው ኤፕሪል 26፤ የአንድነት በረከት እንዳያመልጣችሁ፤ ሂሩት ካፌ እንገናኝ፡፡ በእለቱ በተለያየ ምክንያት መገኘት ያልቻለም፤ የገንዘብ ልገሳውን በሰው መላክ እንደሚችል ወይንም በአንድነት ባንክ ሂሳብ Unity for Human Rights and Democracy: TD Trust; የባንክ ሂሳብ ቁጥር፡ 12682 0041 0883 5209213፡ መክተት እንደአማራጭ እንደተቀመጠ፤ አንድነት ቶሮንቶ ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡
ከደሴ ወደአዲስ፤ … ወደነቀምት፤ በዚህ 22 አመት እንደነቀምት የተጎዳ ማን አለ፤
9- በርግጥ የአንድነት የአዲስ አበባ ሰልፍ በተያዘለት ቀን መጋቢት 28 አልቀጠለም፡፡ ይሄ ጽሁፍ ወደህትመት ሲላክ፤ የአዲስ አበባው ሰልፍ ሚያዚያ 5 እንደሚደረግ ቢገመትም፤ አሁን ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ሰልፉ ቅዳሜ፤ የሰልፉም አቅጣጫ ወደጃንሜዳ ካልሆነ እያለ ነው፡፡ ማደናበር፤ ማናደድ፤ ማዘናጋት ይሉታል ይሄንን ስልት፡፡ እኔ፤ ብልጥ ልጅ የሰጡትን ይዞ ያለቅሳል ነው የምለው፡፡ ፖለቲካና ሕይወት ,ባልመረጥነው መንገድ ውስጥ የመረጥነውን ለማግኘት የምናደርገው ሩጫ ነውና፡፡ መጋቢት 28 ቀን በደሴ የተደረገው ሰልፍ ደማቅና የሚያበረታታ፤ በርግጥም ለሌሎች ከተሞችም መነሳሳትን የሚያመጣ እንደሆነ አስተውያለሁ፡፡ ስለዚህ፤ ነቀምትን ከደሴ የተሻለ ለመቀስቀስና ለማሰለፍ፤ ሁላችንም መረባረብ እንዳለብን ቀስቃሽ አያስፈልገንም፡፡ ደግሞስ በዚህ 22 አመት በኦነግ ስም እንደነቀምት የተጎዳ ማን አለ፡፡ ስለዚህ ነቀምት ተሰልፎ እሪይ ይል ዘንድ ግድ ነው፡፡ ደሴ ነቅሎ ወጥቷል፡፡ ነቀምትም ነቅሎ ይወጣል፡፡ ነቀምት ነቅሎ እንዲወጣም እኛም ከዚህ ከቶሮንቶ ነቅለን እንወጣለን፡፡ ቅዳሜ፤ ሚያዚያ 26 ቀን፤ ከሰዓት በኋላ፤ ከ3 እስከ 6 ሰዓት ሂሩት እንገናኝ፡፡
10- ለተጨማሪ የአንድነት ዝርዝር አገልግሎቶችና መረጃዎች በአካል በአንድነት በጽህፈት ቤታት፤ ወይም ከታች በተጠቀሱት የመገናኛ መንገዶች ያግኙን፡፡ አንድነትን ለማግኘት፤ ኢሜል፤ unityforhumanrights@gmail.com ፤ ድረገጽ፤ http://andnettoronto.blogspot.ca/. የጽህፈት ቤት አድራሻ፡ B2- 2017 Danforth Avenue, Toronto, ዳንፎርዝ ላይ፤ ከዉድባይን ባቡር ጣቢያ በስተምስራቅ 50 ሜትር ራቅ ብሎ፤ ከዘመን እንጀራ መደብር በተቃራኒ፤ ከትብብር መረዳጃ እድር ጎን፡፡