የኢትዮጵያ ሽግግር ምክር ቤቱ ኢፕሪል 13 ስብሰባን በተመለከተ

April 7th, 2014
የአንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ንቅናቄ በሚል የጀመረው እንቅስቃሴ፣ በዉጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ድጋፍ እያገኘ መጥቷል። ኢትዮጵያዉያን በአካባቢያቸው ካሉ የአንድነት ድጋፍ ማህበራት ጋር በመሆን ከሚደግፉት በተጨማሪ፣ የተለያዩ ሲቪክ ማህበራት፣ በዉጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ደርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች ሳይቀር፣ ጉዳዩ የአንድ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ጉዳይ ነው፣ በሚል ከሚሊዮኖች አንዱ ነን እያሉ ነው።

ENTC-flyer
ከነዚህ፣ አገር ቤት እየተደረገ ያለዉን እንቅስቃሴ ከሚደግፉ ድርጅቶች መካከል፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት አንዱ ነው። ምክር ቤቱ የራሱ አላማና ግብ ይዞ እየተንቀሳቀስ ያለ ደርጅት ነው።
በኢትዮጵያ የሚደረገዉን ሰላማዊና ሕጋዊ እንቅስቃሴ ምክር ቤቱ እንደሚደግፍ ብዙ ግዜ አሳዉቋል። አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል የምክር ቤቱ መሪዎችና አባላት ያሳነሱበት፣ ያንቋሸሹበት፣ «አይሰራም፣ ጊዜ ማጥፋት ነው» በሚል በተዘዋዋሪ መንግስት ሕዝቡ ድጋፍ እንዳይሰጥ የሞከሩበት ጊዜ የለም። ይልቅስ ፣ የሽግግር ምክር ቤቱ፣ በዳያስፖራ ያለው የሚሊዮኖች ንቅናቄ ግብረ ኃይል ተወካዮችን ልኮ አብሮ የሚሰራ ከመሆኑም ባሻገር፣ በተለያዩ መግለጫዎቹ አገር ቤት ለሚደረገው ትግል ያለውን ሶሊዳሪቲ በገሃድ ያሳየ ድርጅት ነው።
ለምሳሌ ኦክቶብር ፣ 2013 የሽግግር ምክር ቤቱ «በኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደረገዉን ትግል እንደግፋለን» በሚል ርእስ ያወጣዉን መግለጫ ማንበብ እንችላለን። መግለጫዉ «የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት ለነዚህ ቆራጥ የፖለቲካ ድርጅቶች በተለይም ለሰማያዊ ፓርቲና የአንድነት ድርጅት አመራርና አባላቶች፤ እንዲሁም በየእስር ቤት ተወርውረው ለሚገኙት የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ደራሽ ጀግኖች የድርጅት መሪዎችና ጋዜጠኞች፤ ያለንን ከፍተኛ አድናቆት ከመግለጽ ባሻገር፤ ይህንን ግፈኛ ስርአት በህዝባዊ አመጽ መታገልና ማስወገድ የድርጅታችን መርህ ከመሆኑ አኳያ ሙሉ ድጋፋችንን የምንሰጥ መሆኑን እናረጋግጣለን» ሲል ነው፣ አገር ቤት ላሉት ታጋዮች ምክር ቤቱ አጋርነቱን የገለጸው።
ምክር ቤቱ የአንድነት ፓርቲም ሆነ ሌሎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ታግለው፣ በምርጫ አሸንፈዉ፣ በሕጉ መሰረት ሕገ መንግስቱን አሻሽለው፣ ለሁሉም ዜጎች እኩል የሆነች፣ አንዲት፣ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ብትመጣ ፣ እንደ ማንኛዉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የሚመኙትና የሚናፍቁት ነው። ለዚህም ነው ድጋፋቸዉን እየሰጡ ያሉት።
ነገር ግን ነገሮች እንደተጠበቁ ላይሄዱ ይችላሉ። «በአገራችን ኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ቀዉስ የበለጠ እየከረረ፣ ኢሕአዴግ እርሱ ባወጣዉ ሕግ አልገዛም ብሎ፣ ሕገ ወጥና አምባገነናዊ እርምጃዎች በመዉሰድ ፣ ወደ አላስፈላጊ ደረጃ ከተኬደ፣ በኢትዮጵያ አናርኪ እንዳይፈጠር፣ ከወዲሁ አማራጭ መፍትሄ ማዘጋጀት ያስፈልጋል» ብለው በሽግግር ምክር ቤቱ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ያምናሉ። አሁን በስልጣን ላይ ያሉት አምባገነኖች ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል የሚል እምነት በመኖሩም፣ ከወዲሁ በተለይም በዉጭ ያለውን ኃይል በማሰባሰብና ወደ አንድ በማምጣት፣ ተጠባባቂ PLAN B ለማዘጋጃት እየሰሩ ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት የሚል ስያሜም ለራሳቸው የሰጡት በዚህ ምክንያት ነው። ስልጣን ለመጨበጥ ሳይሆን፣ ነገሮችን በፈራረሱበት ወቅት፣ የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ አገራችን እንደ አገር የምትቀጥልበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ።
አገር ቤት ያለዉ ትግል ተጨባጭ ዉጤት አምጥቶ፣ በኢሕአዴግ እና በተቃዋሚዎች መካከል መግባባት ተፈጥሮ፣ አሁን ያለው ሕገ መንግስት ተሻሽሎ፣ ነገሮች ሁላችንም እንደምንፈልገው ቢሄዱና የሽግግር መንግስት ምክር አላስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ቢከስም፣ ሁላችንም የምንመኘው ነው። ነገር ግን ያ እስኪሆን፣ «ምናልባት» በሚል መጠንቀቁ አስተዋይነት ነው። ለዚህም ነዉ ጥረታቸው ሊደገፍና ሊበረታታ የሚገባው።
የሽግግር ምክር ቤቱ፣ የፊታችን ሚያዚያ 5 ቀን በዋሺንግተን ዲሲ ስብሰባ ያደርጋል። ስብሰባዉን ላይቭ በፓልቶክ፣ ወይንም፣ ቴሌኮንፈራንስ የሚተላለፍ ከሆነ ለመከታተል እሞክራለሁ። በዲሲ አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያዉያን በአካል ስብሰባዉን እንዲካፈሉ፣ ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ፣ ሃሳባቸውን እንዲገልጹም አበረታታለሁ። በአገር ጉዳይ ላይ መመካከርና መወያየት ምንጊዜም ጠቃሚ ነውና።
ስብሰባው፣ ብዙ ጊዜ በዳያስፖራ ከተለመደውና አሰልቺ ከሆነው፣ አገዛዙን ከማዉግዝና ከመስደብ ፖለቲካ ያለፈ፣ የተጨበጡና ሥራ ላይ ያተኮሩ፣ ኢትዮጵያዊያን ማሰባብስ የሚችሉ፣ በሰለጠነ መንፈስ የሚቀርቡ፣ አንኳር ቁም ነገሮችን ጉዳዮችን አንስቶ እንደሚወያይ ተስፋ አደርጋለሁ።

በዓረና ከፍተኛ አመራሮቸ፣አባሎችና ዓረና በጠራው ህዝባዊ ስብሰባ ተሳታፊዎች የተፈፀመው ኢ ሰብአዊ እንግልት – ብርሃኑ በርሄ (የዓረና ፕሬዘዳንት)

April 7th, 2014
ዛሬ እሁድ መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ/ም ዓረና ትገራይ ህዝባዊ ፖለቲካዊ ስብሰባ በምስራቃዊ ዞን አፅቢ ወንበርታ ወረዳ ጠርቶ ያካሄደ ሲሆን ከትናትና ጀምሮ ህዝቡን ወደ ስብሰባው እንዲመጣ የሚቀሰቅሱ አባሎችና አመራሮች ከድንጋይ ውርወራና የቡድን ረብሻ ባለፈ ከተከራዩት አልጋ አስወጥቶ ሌሌት የትም ተጥለው እንዲወድቁ ለማድረግ እጅግ ኢ-ሰብአዊ ተግባር መፈፀሙን ተገልፆ ነበር ፡፡ የአፅቢ ፖሊስ አባላቶቻችን ከተከራየትና ገንዘቡን ከፍለው የክፍሉ ቁልፍ ተረክበው በእጃቸው ከሚገኝ ቤት ካለወጣሁ በማለት ትናንት መጋቢት 27 ቀን 2006 ዓ/ም አቶ አምዶም ገ/ሰላሴ ፣ አቶ ስልጣኑ ሕሸ ፣ መም/የማነ ንጉሰ እስከምሽቱ 2፡30 በአፅቢ ፖሊስ በእስር ነበሩ ፡፡ በዚሁ ቀን የወረዳ አስተዳዳዎች የሚመሩት ለህዝብ የሚታደል በራሪ ፅሑፍ መቅደድና በአራና አባላት ላይ ድንጋይ በመወርበር ሲያውኩ ዛሬ ጥዋት ደግሞ ቦዘኔ ህፃናትና ምልምል ካድሬዎች ገብረ ማርያም የተባለው የታጠቁ ምልሻ ጭምር በዓራና አባላት ላይ መጠነ ሰፊ የማወክ ተግባር እንደጀመሩና ስብሰባው እንዳይካሄድ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ተገልፆ ነበር ፡፡
ዛሬ ከሰኣት በሁዋላ የህዝብ ስብሰባው እንደተጠናቀቀ ደገሞ የአረና ከፍተኛ አመራሮችና አባሎች እንዲሁም በስብሰባው የተገኙ ወደ 61 የሚሆኑ ገበሬወች በአፅቢ ከተማ ፖሊስ ጣብያ ታስረዋል ፡፡ የእስሩ መነሻ ምክንያት ተደባዳቢ የወንጀለኞች ቡድን የአረና አባላትን ሲደበድቡና ስብሳባው እንዳይጀመር ሲያውኩ የሚያሳይ መረጃ በሞባይል ቀርፃችሁዋል የሚል ሆኖ ተቀረፀ የተባለው ፊልም ከተገኘበት የሞባይል ስልክ አውጥቶ ለመንጠቅና ለማጥፋት ያለመ ነው፡፡
የአቶ አብርሃ ደስታ ሞባይል ተወስዶ እየተፈተሸ ሲሆን የሌሎቹ የአረና ከፍተኛ የአመራር አባላትና አባላት ሞባይል ስልኮችም እንዲሁም በስብሰባው የነበሩ ገበሬዎች ሞባይል በፖሊስ ተነጥቆ በአፅቢ ፖሊስ ጣብያ እስር ቤት እየተፈተሸ እንደሆነ ቦታው ያሉ የአረና አባላት ሪፖርት አድርገውልኛል ፡፡
ሁኔታው ለትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘአማኑኤል ለገሠ በሞባይል ስልካቸው 0914 300868 ልክ ዛሬ እሁድ ከሰአቱ 9፡30 ደውየላቸው ስልኩን እንዳነሱ የምደውልላቸው ያለሁኝ ብርሃኑ በርሀ መሆኔን ገልጨ ልክ በኩሓ አፀያፊ እስርና መንግላታት በዓረና አባለት እየተፈፀመ እንዳለ ሪፖርት ሳደርግላቸው እኔን መሆኔን እንዳወቁ ወዲያው ስልካቸውን የዘጉብኝ እንዳይሆን ብየ ስልኩን እንዳይዘጉብይ በፍጥነት በአፅቢ ስብሰባ የሚያካሂዱ አባላቶቻችን መታሰራቸው ስነግራቸው ንግግሬን ሳልጨርስ ስልኩን ዘጉት ፡፡
ፖሊስ ወንጀል ስለመሰራቱ ማስረጃ የያዘለት ይሸልማል እንጂ ወንጀል መሰራቱን የሚያረጋግጥ መረጃ ለማጥፋት ፖሊስ የሚሰራ ከሆነ ይህ ዓይነቱ ፖሊስ የሰላም አባት ወይስ የወንጀል አባት እንበለው ?
አሁን በፖሊስ ምርመራ በአፅቢ ፖሊስ ጣብያ የሚገኙት 1- አቶ ስልጣኑ ሕሸ የዓረና የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና የፅሕፈት ቤት ሃላፊ 2- አቶ ዓምዶም ገብረ ስላሴ የዓረና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ 3- አቶ አብርሃ ደሰታ የዓረና የህዝብ ግንኙነት ኮሚቴ አባልና ስራ አስፈፃሚ አባል 4- መም/ ታደሰ ቢተውልኝ የዓረና ማእከላዊ ኮሚቴ አባል 5- አቶ አስገደ ገብረ ስላሴ 6 – መም/የማነ ንጉሴ 7 አቶ ሃይለ ኪሮስ ታፈረ 8- መም/ ሃይለ 9 አቶ ቴወድሮስ 10 – መምህር ክፍሎም እና ሌሎች የአረና አባላትና 61 የስብሰባው ተሳታፊ የአከባቢው ገበሬዎች ናቸው፡፡
ዓረና ትገራይ ፓርቲ ይህንኑ ዘግናኝ የገዢው ፓርቲ የዓፈና ተግባር እንዲቃወምና እንዲያጋልጥ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ፣ ለሰብአዊ መብት መከበር የሚሰሩ ተnማት ፣ በኢትዮጵያ ለሚሰሩ የውጭ መንግስታት ኢንባሲዎች እንዲሁም ድምፃቸው ለታፈኑ ድምፅ ለመሆን ለሚሰሩ የሃገር ውስጥና የውጭ ሚድያዎች ጥሪውን ያቀርባል ፡፡ በተጨማሪም እነዚህ የጠራራ ፀሃይ ወንጀለኛች በሕግ ፊት ለመፋለም ይረዳ ዘንድ የቻለ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ለዓረና ትገራይ ፓርቲ የገንዘብና የሙ ድጋፍ እንዲያደርጉ ለሁሉም ወንጀል የሚፀየፉ ወገኖች ጥሪውን ያቀርባል ፡፡
ይህ ዓይነቱ ዓይን ያወጣ ወንጀል የትግራይ ህዝብ ከደርግ አፈና ለመታደግ በ 17 የትጥቅ ትግል ዓመታት ሂወታቸውና ንብረታቸው ለከፈሉ በሂወት ያሉ ለውጥ ፈላጊዎቹ የህወሓት አባለትና ደጋፊዎች እንዲሁም መላ የትግራይ ህዝብ በአማራጭ ሰላማዊ ትግል ለሚያካሂድ ፓርቲ የሚፈፀም ጭፍጨፋ በእራሱ መብት የተቃጣ ወንጀል መሆኑን አውቆ ብምሬት እንዲቃወመው ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ጭፍን ዓፈና የነፃት ባለ ራአዮችን በማጠናከር የነፃነት ራእይ ገዳዮችን የሚያዳክም ግብዝ ውሳኔ መሆኑን የትግራይ ህዝብ አኩሪ ፀረ ባእዳዊ ገዥዎችና ፀረ ፋሽት ደርግ ተጋድሎ በሚገባ ያስተማረን በመሆኑ በዚሁ እኩይ የደርግን አሻራ የወረሱ የአምባገነኖች ተግባር ዓረና ፓርቲና አባላቱ እንደማይንበረከኩ ሁሉም ሊያቀው ይገባል ፡፡ የዓረና ሃገራዊ ራኢ የሃገር አጀንዳ ሆኖ በሃረዊ ለውጥ ይደምቅ ዘንድ ዓረና ጠንክሮ እንደሚሰራም ደግሞ ያረጋግጣል ፡፡
ዓረና ትገራይ ፓለዴሞክራሲና ለሉእላዊነት ፓርቲ
መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ/ም ከቀኑ 10፡20