Wednesday, 12 March 2014

ሃረር እየታመሰች ነው


(EMF) በሃረር ከተማ ውስጥ አለመረጋጋት ተፈጥሯል:: ዋናው ምክንያት ከትላንት በስትያ በተለምዶ “መብራት ሃይል” ተብሎ በሚጠራው ህንጻ ላይ የተነሳው ቃጤሎ ነው:: የእሳቱ መነሻ… ራሱ መንግስት ነው የሚሉት ሰዎች ተቃውሟቸውን የዚያኑ እለት አሰምተዋል:: ይህንን ተቃውሞ ተከትሎ ከተማዋ በተኩስ ድምጽ ስትናወጥ ቆይታለች:: ከዚያው ጋር ተያይዞ, ዜጎችን መደብደብ እና ማሰር ክልሉን የሚያስተዳድሩት ሃረሪዎች የስራ ድርሻ ሆኖ ነበር የቆየው::
በሃረር ከተማ ውስጥ ጉልህ የሆነ የዘር መድልዎ ይደረጋል:: እንደወትሮው መስቀል ደመራ ጥምቀት ማድረግ ብዙም አይታሰብም:: የአማራ ዝርያ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሚገፉበት ከተማ ነው:: ከዚያም አልፎ በኦሮሞ ተወላጆችም ላይ ተመሳሳይ ተጽዕኖ ይደረጋል:: ይህ የእሳት ቃጠሎ ከመነሳቱ በፊት የሃረሪ ተወላጆች በዚያ ገበያ ስፍራ የሚገኙ ሱቆቻቸውን ሲሸጡ እንደነበርና በአንደኛው ሱቅ ውስጥ ብዙ ተቀጣጣይ ጋዝ ሲቀመጥ ነበር ተብሏል:: ውጭ አገር በሚገኙ የቀድሞ የከተማው ነዋሪዎች የተገዛው የእሳት አደጋ መኪናም በቂ ውሃ አለመርጨቱን ነው – ታዛቢዎች የሚናገሩት::
Shot by Police (Harer)
Shot by Police (Harer)

በሃረር ከተማ ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ችግር ለማስረዳት በሃረር ነዋሪ የሆነ አንድ ወጣት.. ለጋዜጠኛ አቤ ቶኪቻው የጻፈውን ደብዳቤ መመልከት ጠቃሚ ነው:: እንዲህ ሲል ነበር ደብዳቤውን የጻፈለት::“አቤ ዛሬ ይህን ጽሁፍ የምጽፍልህ ከመንግስትም ሆነ ከተበዳይ ወግኜ አይደለም፡፡ ትውልዴ አና እድገቴ አዛው ሀረርጌ ነው ነገር ግን ለትህምርት ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ ሰነባብቻለሁ፡፡ በቅርብ እንደሰማነው የሀረር መብራት ሀይል ገበያ ላይ በተነሳው እሳት ምክንያት ምስኪኑ ህዝባችን ለምን የሚለውን ጥያቄ ለማቀረብ ሰለፍ እንደወጣ ሰምተናል አይተናል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ሀረር ለየት ያለ ክስተት አጋጥሟታል ፡፡ በትላንትናው ቀን ለሰልፍ የወጡ ወጣቶችን በካሜራ ቀርጸው ዛሬ ከ400 በላይ ወጣቶችን አፍሰው ወህኒ ከተዋል፡፡
“የክልሉ መንግስት በአማራዎቸ አና በአሮሞዎች ላይ ከባድ ጥላቻ አለበት፡፡ ሀደሬ ካለሆንክ መንኛውም አይነት ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ አገልግሎቶች ቅድሚያ አታገኝም፡፡ ወጣት ነኝ፣ 20 አመቴ ነው፣ ነገር ግን አዝች መሬት ላይ ከ እንደዚ አይነት መንግስት ጋር መኖር መሮኛል፡፡ ከኔ ያንተ ድምጽ ከፍ ይላል በዬ ነው የምጽፍልህ… ማንነቴ ካንተ ባያልፍ ደስ ይለኛል፡፡ የሰጠሁክን መረጃ ያገኘሁት ሀረር ከሚኖር የሱቅ ነጋዴ ከሆነው አጎቴ ነው፡፡
ሰላም ሰንብት!”

ከላይ የገለጽነውን ደብዳቤ የላከው ነዋሪነቱ በሃረር የሆነ ወጣት ሲሆን; አሁን በከተማው ያለውን ችግር እና ውጥረት በከፊል የሚያሳይ ነው:: ከትላንት ጀምሮ ጉዳያቸውን ለማስረዳት ወደ ክልሉ ሃላፊዎች የሄዱ ተጎጂዎች የተረፋቸው ነገር; መታሰር ሆኗል:: የክልሉ አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ አብዱላሂም ቢሆኑ ሰዎች መታሰራቸውን አልካዱም:: በአሁኑ ወቅት ከሰላሳ በላይ ወጣቶች መታሰራቸውን የቅርብ ምንጮች ይናገራሉ:: በሞት እና በህይወት መሃል ሆነው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱትም ብዙ ናቸው:: የሃረር የሰሞኑ ውሎ ይህን ይመስል ነበር::

አንድነት ፓርቲ 2ኛውን ዙር የሚሊዮኖችን እንቅስቃሴ በተለያዩ ከተሞች ሊጀምር ነው

March 12th, 2014
ማጋቢት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ለሦስት ወራት በሚካሄደው ክፍል ሁለት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ሪፎርም” በሚለው ዘመቻ፣ በዋነኛነት በተመረጡ 14 ከተሞች እና በሦስት ተጓዳኝ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ ይካሄዳል።
የመሬትን አጀንዳ የሁለተኛው ዙር የመታገያ አጀንዳ ለምን እንዳደረገ ፓርቲው ሲያብራራ፣ “በባለሃብት ስም ገበሬው ከይዞታው መፈናቀሉ፤ በከተሞች በልማት ስም ዜጎች እየተፈናቀሉ ለጎዳና ላይ ኑሮ መዳረጋቸው፤ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መበቶቻቸው እየተጣሱ ለማህበራዊ ቀውስ መዳረጋቸውው ዛሬም ተጠናክሮ መቀጠሉንና በተበጣጠሰ ትንንሽ የመሬት ይዞታ ላይ በኃይል የመፈናቀል ተራቸው እስከሚደርስ እየተጠባበቁ ያሉትም ቢሆኑ ዛሬም በዶማ እና በበሬ አፈር እየገፉ ከአቅማቸው በላይ በሆነ የማዳበሪያ እዳ ተቀፍድደው አንገታቸውን ደፍተው በሰቀቀን ለመኖር ተገድደዋል” ብሎአል።
“መሬትን ዋነኛ የሙስና ማዕከል ያደረገውን ሥርዓት በመቃወም የህዝብ የለውጥ ፍላጎት እንዲከበር አደባባዮች በለውጥ ፈላጊ ሰላማዊ ታጋይ ህዝብ እንዲሞሉ እንዲሞሉ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀስ የሚገልጸው አንድነት፡ አምባገነናዊ ሥርዓቱ በሰላማዊ ትግል ተሸንፎ ዜጎች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት እንዲሆኑ፤ ሃብት የማፍራት፤ የመያዝ እና የማስተላለፍ መብታቸው እንዲጠበቅ፤ በኮሚኒቲ /በማህበረሰብ/ በጋራ ከተያዘ፤ በመንግስት ይዞታነት ከተከለለ እና በተቋማት ይዞታነት ከታወቀ መሬት በቀር በዜጎች የተያዘ መሬት የግል ይዞታ ሆኖ እንዲከበር ለማድረግ እንደሚታገል አስታውቋል።
በህዝባዊ ንቅናቄው የአደበባይ ህዝባዊ ስብሰባ እና ሰላማዊ ሰልፍ የሚደረግባቸው ቦታዎች አዲስ አበባ፣ ደሴ፣ ሐዋሳ፣ አዳማ/ናዝሬት/፣ መቀሌ፣ ደብረታቦር፣ ደብረማርቆስ፣ ድሬዳዋ፣ ጂንካ፣ ቁጫ፣አሶሳ፣ ነቀምት፣ ለገጣፎ፣ ወልዲያ፣ ጋምቤላ፣ ምዕራብ አርማጭሆ/ አብርሃ ጅራ/፣ይሆናሉ ብሎአል።
አንድነትና መኢአድ ፓርቲዎች በቅርቡ በባህርዳር በብዙ ሺዎች የሚቀጠር ህዝብ ለተቃውሞ እንዲወጣ አድርገዋል። ፓርቲው በመጀመሪያ ዙር የሚሊዮኖች ድምጽ በተለያዩ ከተሞች የተሳካ የተቃውሞ ሰልፎችን ማድረጉ ይታወቃል።993754_546619252089680_666940779_n

አሸባሪዎቹ የጣይቱና የሚኒሊክ ሴት ልጆች

March 11, 2014
ቹቸቤ
የሰማያዊ ፓርቲ ቢጫ ለባሽ ወጣት ሴቶች መታገታቸውን ሰምተን ነበር። አንጋፋው ክስ ደግሞ እናትና አባታቸውን ጮክ ብለው መጥራታቸው መሆኑ ሲነገረን የጥፋታቸው ልክ ታሰበን። የትግራይ ናፃ አውጪዎችና ለነርሱ ለመታዘዝ ፈቃዳቸውን ያሳዩ ገባሪዎች በሙሉ ለተልዕኮ ትምህርት የማይመቹትን እነ ባዮሎጂንና ኬሚስትሪን ዞር አላሉባትም። በርካቶቹ የራሳቸውን ስም ከረሱ የቆዩ ስለሆኑ ዘር በጅምላው እንጂ ቤተሰብ በነጠላው አይገባቸውም። እናም እነዚህ ወጣቶች የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆች ነን ማለታቸው አሸበራቸው።Arrested Semayawi party members and supporters
ትንሽ እወቀት ያለን እኛ ግን በመጀመርያ ሴቶች ወላጅም አዋላጅም መሆናቸውን እናውቃለንና የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆች ነን ቢሉ አይደንቀንም። እንዲያውም “ጎሸ ሰው ጫካ በቀል አጉራ ዘለል ሲሆን ነው እንጂ የመጣበትን ሲያውቅ ጥሩ ነው።” ብለን ያደነቅን እናቅፋለን የወደድን ለጋብቻ እንጠይቃለን። ወጉ እንደዚህ ነዋ! በጋብቻ ተደራጅቶ የሚኒሊክና የጣይቱን ስም ማቆየት ስለምን ያስፈራል? ዘር መተካት ደግ ነው እንላለን። እንዴ ፌዴራሎች ጠለፋ ይሆን እንዴ የፈፀሙት?
ቢሆንም ልካቸውን ያውቁታልና በሚኒሊክና ጣይቱ በሚሸበሩትም አንፈርድም። ግንቦት ሃያ የተወለዱት ራሳቸውን የፋብሪካ ውጤት አድርገው ስለሚቆጥሩ ተጋዳላይ ድርጅት እንጂ እናትና አባት እንዴት ሊኖረው ይችላል ብለው የመቆጣት መብታቸውንና የማስፈራራት አቅማቸውን ተጠቅመዋል። እናም ድንጋይ ሰባሪ ቅሎቹ ወይም ባለጊዜዎቹ እነዚህን የሚያማምሩ የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆችን ተመሳስለው የገቡ ጠጉረ ልውጦች ብለዋቸዋል።
ነገር ግን በቁም ነገር የክሶች ሁሉ ክስ ተብሎ በታሪክ መዝገብ እንዲሰፍር  የክስ መዝገብ ቅጂው ሊቀመጥ የሚገባው ሰነድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እንግዲያው የሙሶሎኒና የግራዚያኒ ወይም የሳሊኒ ነን እንዲሉ ይጠበቅባቸው ነበር እንዴ? በማለት ቁጣዬን ሳሰማ አንድ እውቀት ዘልቆ የገባው ጓደኛዬ “… ወይ ቹቸቤ ወይ አልገባህ ወይም ግራ ተጋብተህ ይሆናል እንጂ እነሱ ከመስመርዋ ዝንፍ አላሉም አዎ አንድና አንድ ነገር ብቻ ለሙሶሎኒና ግራዚያኒ ነው የሚሉህ አራት ነጥብ።” ብሎ ሲናገር የመለስ መንፈስ ያደረበት ይመስል ነበር። ቀጠለና “… ሃይለማርያም ኢየሱስና መለስ ተምታቶበት ዘለዓለማዊ ክብርና ሞገስ ሲል የምትሰማው ትንሽ የተጋነነ ነው” ብሎ ሳቅ እያለ በረድ ሊያደረግኝ ሞክሯል።
እና ካልጠፋ ውሸት ልጁ ቀማኛ አባቱ ዳኛ በሆነበት አገር የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆች ነን እያሉ ሮጡ ማለት የሩጫ ዝግጅት ላይ ሩጫን ሁከት ፈጠራ ማድረግ የሚያስቅ ብቻ ሳይሆን የሚያሳዝንም ነው። እነዚህ ወጣቶች ተጠርጥረው አልተያዙ ሲሮጡ ሸንቆጥ የሚያደርጉ ቃላትም አብረዋቸው ከሮጡ መረጃው ያው ነው የሚሆነው። ሩጫ ደግሞ እንደዚህ ነው አንዳንድ ሰው ያልበዋል፣ አንዳንድ ሰው ቁና ቁና ያስተነፍሰዋል ለመታሰቢያ ገንዘብ ለመሰብሰብያም ይሮጣል። እነዚህ ቆነጃጅት ደግሞ ጮክ ብለው አሰቡ ይህንንም አላልንም ብለው አልካዱም የምን ምስክር ያስፈልጋል? እርግጥ ነው ቁመናቸው ያምራል ግን አስፈሪ ጡንቻ አላየሁባቸውም ምን ይሁን ብለው ነው ምስክር የሚያስፈራሩት? እንዲያውም ምስክሮቻቸው ያሉትን መልሰው ሲያሰሙ “ወይኔ ጉዴ አንቺም ሰምተሽ ነበር? ደስ ሲል” እስቲ ድገሚው ይሉ ይሆናል እንጂ። በመጀመርያ አገር እንዲሰማ አይደል እንዴ ጮክ ብለው የተናገሩት? እዚያ መንደር የቂል ክምር ነው ያለው? እኔ እምለው ባንዳነት በ’ጂን’ ይተላለፋል እንዴ? ተጋዳላዮች በአረቄው ማለቴ አይደለም በዘር ግንድ ለማለት ነው። የባንዳ ልጆች ተደራጅተውብን ሚኒሊክን አሸባሪ ፋይል ውስጥ ጨመሩት።
የዘር ግንድ እኮ እውነትም አስገራሚ ነው። የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆች ዛሬን ድረስ የባንዳ ልጆችን ማሸበራቸውና ማስጨነቃቸው ይደንቃል። “… እንኳንም አደባባይ ወጥተው አየናቸው እንዲያውም ትንሽ የፈዘዝነው ከባንዳ ተኝተን ይሆናል….” የሚሉ ወንዶች መነቃቃትም እየታየ ነው። እኛም በሩቅ ያለነው እንዲህ እንላለን የሚኒሊክና የጣይቱ የሀገር ወዳድና የጀግና ኢትዮጵያውያን ዘር ይብዛልን። አሜን በሉ!

አባ መላ እና መላ ያጣው ንግግራቸው

March 12, 2014
በዳጉ ኢትዮጵያ
አቶ ብርሃኑ ዳምጤ (አባ መላ) በቅርቡ ስላደረጉት የአቋም ለውጥ ለቢንያም ከበደ (ቤን) የሰጡትን ቃለ መጠይቅ አነበብኩት፡፡ ላልተጠበቀው የ180 ዲግሪ የአቋም ለውጥ በመንስኤነት ከጥቅመኛ ፖለቲከኝነት እስከ የጠበቁትን አለማግኘት በርካታ ምክንያቶች እየተጠቀሱ በብዙዎች ትንታኔ እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ እኔ በዚህ ረገድ ምንም ለማለት አልፈልግም፡፡ ይልቁንስ በቃለ ምልልሳቸው ኢሳትን በተመለከተ በሰነዘሯቸው አንዳንድ የተሳሳቱ ነጥቦች ላይ ጥቂት ብል እመርጣለሁ፡፡ የትኩረት ነጥቦቼን በተናጠል ተራ በተራ እዘረዝራለሁ፡፡ESAT interview with Aba Mela (activist)
“ምንም አይነት የዜና ምንጭ የሌላቸው”
አቶ ብርሃኑ ስለኢሳት ከተናገሯቸው ነጥቦች የመጀመሪያው “ኢሳት ምንም አይነት የዜና ምንጭ የለውም” የሚል ነው፡፡ እውነት ለመናገር ራሳቸው አቶ ብርሃኑም በዚህ ንግግራቸው የሚያምኑበት ከሆነ አስቂኝ ነው፡፡ እንዴ አቶ ብርሐኑ፡- መቼም የጠቅላይ ሚኒስትርዎትን ሞት ቀድመው የሰሙት ከኢቲቪ አልያም ከፋና አይደለም፡፡ የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነውን አስፀያፊ ንግግር ከዝግ የካድሬዎች ስብሰባ ላይ ቀድቶ አየር ላይ ያዋለው የሰሞኑን ወዳጅዎ (መቼም እርስዎ በዚህ ተለዋዋጭ አቋምዎ ዘላቂ ወዳጅ አይኖርዎትም ብዬ ነው) አቶ ቢንያም አይመስለኝም፡፡ ኸረ ስንቱ ስንቱ… ከጉራ ፋርዳ የአማራ ተወላጆች መፈናቀል እስከ የኦህዴድ ውስጣዊ ህንፍሽፍሽ… ኢሳት ይህን ሁሉ ከህዝብ ተደብቆ የነበረ መረጃ አደባባይ ያወጣው ያለአንዳች የመረጃ ምንጭ ነው ካሉን በአመክኒዮ ሳይሆን በስሜት እንደሚነዱ በራስዎ ላይ እየመሰከሩ ነው፡፡
“የዜና ምንጫቸው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው”
ይህ ነጥብ ደግሞ አስቂኝነቱ ያመዝናል፡፡ ኢሳት የኢቲቪን ዜና “ትዊስት እያደረገ የመጀመሪያውን መጨረሻ የመጨረሻውን መጀመሪያ” አድርጎ የሚያቀርብ ከሆነ አራተኛው የኢቲቪ ቻናል ሆነ ማለት ነው፡፡ የኢቲቪን ዜና ዳግም የሚያሰራጭ (Rebroadcast) ጣቢያ ከሆነ ደግሞ እኔን ጨምሮ በሚሊዮን የምንቆጠር ኢትዮጵያውያን አማራጭ የመረጃ ምንጭ ባላደረግነው ነበር፡፡ ለምን ቢሉ ኢቲቪን ዲሽ መትከል ሳያስፈልገን፤ አንዱ የስርጭት ሞገድ ሲዘጋ በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠር ብር ከእለት ጉርሳችን ነጥቀን ለዲሽ አስተካካዮች ሳንከፍል መከታተል እንችላለን፡፡ እውነቱን ለመናገር የኢሳት የተሰሚነት ሚስጥር እርስዎ ከተናገሩት ተቃራኒው ነው፡፡ ከአሰልቺውና ከእውነት ከተጣላው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮፖጋንዳ የሚያስጥል አማራጭ አድርጎ ኢሳት ራሱን ማቅረቡ ነው የተሰሚነቱ ምክንያት፡፡ እስኪ ለዛሬ ለእውነት ታማኝ ለመሆን ይሞክሩና የኢቲቪንና የኢሳትን የዜና ፕሮግራሞች ይከታተሉ፡፡ ኢቲቪ የሐረር የውኃ ችግር እንደተቃለለ “አንዳንድ ነዋሪዎችን” እማኝ አድርጎ ሲዘግብልዎት ኢሳት ግን በህዝቡ አዕምሮ ውስጥ የሚብሰለሰለውን የሐረር የግንብ መደዳ ሱቆች ቃጠሎ ክስተት ተጎጂዎቹን እያነጋገረ ያስደምጥዎታል፡፡ እርስዎ በሐረር ከተማ ቢኖሩ አሊያም በከተማው ውስጥ የሚኖር አንዳች የቅርብ ዘመድ ካለዎት  የኢቲቪን “ሐረር ሠላም ነው ምንም አልተፈጠረም” የዘወርዋራ ፕሮፖጋንዳ ለመስማት የሚያስችልዎት አንዳች ፍላጎት ይኖርዎ ይሆን?
“ተአማኝነት የሌለው”
በቅርቡ የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የአቶ አለምነውን ስድብ-አዘል ንግግርና የፓርቲያቸውን የዝምታ ስምምነት በመቃወም በባህር ዳር ከተማ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት ደማቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሒዶ ነበር፡፡ ሠልፈኞቹ ለተቃውሞ የወጡበትን የአቶ አለምነውን ንግግር የሰሙት በሌላ በማንም ሚዲያ ሳይሆን በኢሳት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በ500 ኪ.ሜ ርቀት የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በኢሳት የሰሙትን መረጃ አምነው ለተቃውሞ የባህር ዳር ከተማን ጎዳናዎች አጥለቅልቀዋል፡፡ ተአማኝነት ማለት እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን ማለት ይሆን?
“ኢሳት ከግንቦት ሰባት ውጪ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን አያስተናግድም”
አቶ ብርሐኑና እኔ የምንሰማው ሁለት የተለያዩ ኢሳቶችን ካልሆነ በቀር በየእለቱ የኢሳት ፕሮግራሞች የአንድነት፣ የሠማያዊ፣ የአረና ወዘተ እንቅስቃሴዎችና መግለጫዎች ሰፊ ሽፋን የሚያገኙት በኢሳት ነው፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስኩት የባህር ዳር የአንድነት ፓርቲና የመኢአድ የተቃውሞ ሠልፍ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ያገኘው በኢሳት ነበር፡፡ ኢቲቪማ በሠልፉ ተደናግጦ ስለሰልፉ አንዳች ቃል ሳይተነፍስ ይልቁንስ “መድረክ አንድነትን ከአባልነት ማገዱን” እያጋነነ ሲዘግብልን ነበር፡፡ “ተቃዋሚዎች ተከፋፈሉ” ነው መልዕክቱ፡፡ ሁለት ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች (አንድነት ፓርቲና መኢአድ) በትብብር መሬት-አርዕድ የተቃውሞ ሠልፍ ማድረጋቸው ሳይሆን አንድ ፓርቲ ለጊዜው ከመድረክ መታገዱ ለገዢው ፓርቲ የሚጠቅም ዜና ስለሆነ ሽፋን ያገኛል- በኢቲቪ መስፈርት፡፡
“በኢሳት ከግንቦት ሰባት ውጪ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሽፋን አያገኙም” ለሚለው የአቶ ብርሐኑ አስተያየት ራሱ ገዢው ፓርቲ ከሳምንታት በፊት በሐገር ውስጥ በህጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መሪዎች በኢሳት መግለጨ መስጠታቸው ህገወጥ ነው ሲል መክሰሱና አንድነትና ሠማያዊ ፓርቲም “ይህን ማድረግ መብታችን ነው”ሲሉ በጽኑ መቃወማቸው ጉልህ ማስተባበያ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ግንቦት ሰባት “ከኤርትራ በማገኘው ድጋፍም ጭምር ተጠቅሜ የአገዛዝ ስርዓቱን አወርዳለሁ” ሲል በሰጠው መግለጫ ላይ ጊዚያዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ተቃውሞ ማሰማቱን ከዋና ፀሐፊው አንደበት የሰማነው በዚሁ በኢሳት እንደነበት አቶ ብርሐኑ አይዘነጉትም ብዬ አምናለሁ፡፡
በአጠቃላይ የያዙትን የፖለቲካ አቋም በማናቸውም ምክንያት ትቶ የአቋም ለውጥ ማድረግ ሊከበርለት የሚገባ የማንም ሰው መብት ነው፡፡ ነገር ግን አዲስ የተቀላቀሉት ካምፕን ደስ ለማሰኝትና ድርጎ ቢጤም ለማግኘት በማሰብ የባሰ ትዝብት ላይ የሚጥል ንግግር መናገሩ ፋይዳው ብዙም አይታየኝም፡፡ አገዛዙ እንደሆነ ደጋፊህ ነኝ ብሎ ለሚመጣለት (በተለይም ከተቃዋሚው ጎራ) ከህዝብ አንጡራ ሐብት ላይ ዘግኖ ላለመስጠት የሚያስችል አንጀት እንደሌለው የታወቀ ነውና አቶ ብርሐኑም ያሰቡትን ለማግኘት ብዙ መቀባጠር የሚኖርብዎት አይመስለኝም፡፡ አበቃሁ!