ልጇን በጀርባ አዝላ ድምጿን ለማሰማት የወጣች ሴት

February 23rd, 2014      
ልጇን በጀርባ አዝላ ድምጿን ለማሰማት የወጣች ሴትudj_lady
አንድነት እና መኢአድ በባህር ዳር የጠሩት ሰልፍ፣ በሶሻል ሜዶያዎች ዋን መነጋገሪያ ሆኗል። ኢትዮጵያዊያን የሰማቸውን ደስታ እየገልጹ ሲሆን ፣ በባህር ዳር ሕዝብ ኩራት እንደተሰማቸው እየጻፉ ነዉ። ኢሳትን ጨመሮ በርካታ ሜዲያዎች፣ ፓልቶክ ክፍሎች፣ ድህር ገጾች ትኩረታቸው ጎጃም ሆኖ የባህር ዳሩን ታሪካዊ እንቅስቅሴ እየዘገቡም ነዉ።
አንዲት ኢትዮጵያዊት ልጇን በጨርባዋ አዝላ ፣ ለመብቷ፣ ለነጻነቷ፣ ድምጿን ለማሰማት ሰልፉን ተቀላቅላ ትታያለች። በሶሻል ሜዲያዎችም ብዙዎች ለዚች እህት አድናቆታቸውን እየገለጹ ነዉ።
እኛም ለዚች እህታችን ያለንን አክብሮትና አድናቆት እንገልጻለን። በአሥር ሚሊዮኖች ለምንቆጠር፣ በአለም ዙሪያ ሁሉ ለተበተንን፣ ዝምታን ለመረጥን፣ ትግል፣ አገርን መዉደድ፣ ለነጻነት መቆም ምን ማለት እንደሆነ ያስተማረችን፣ ጀግና ሴት ናት።

የኢትዮጵያን ገጽታ አደባባይ ያወጣው አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ

ልማታዊ ግስጋሴ እስከ ግድበ ህዳሴ በደረሰበት ታሪካዊ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በፈጣን የእድገት መስፈርት ውስጥ ከአፍሪካ አንደኛ ከአለም ከቻይና ቀጥሎ ሁለተኛ ነች እየተባለ በመሪዎቿ በሚነገርላት ጊዜ። አሸባሪዎችን ከመነሻቸው ለማምከን በአይነቱ ልዩ የሆነ የአንድ ለአምስት አደረጃጀት የሰዎችን ድርጊት ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብን ጭምር የሚመረምር ምትሃታዊ ሃይል ተደራጅቶ ባለበት ሁኔታ የዴርቶጋዳን ልብወለድ መሰል ነገር መታየቱ ብዙዎችን አስደምሟል። ለመሆኑ የዛሬ ልጆች ጀግና አይደሉም የሚል ማን ነው?
በውጭ ሃገር የዜና ማሰራጫዎች ወሬው እንደተሰማ አስተያየት ለመክተብ ጣታቸው እንደ ክላሺኒኮቭ ፊደል የሚያንጣጣ ሁሉ ፓይለቱ ጥገኝነት ለማግኘት ብሎ እንዲህ ማድረጉ አሳፋሪ ነው፣ አላዋቂ አፍሪካዊ መሆን አለበት፣ ይቀጣ! ይቀጣ! የሚሉ ሃረጎች በርክተው ነበር። እነዚህ በአብዛኛው አፍሪካ ማለት አንድ ሃገር የሚመስላቸው የእውቀት ብርሃን የጨለመባቸው ናቸውና ምንም ማድረግ አይቻልም።Ethiopian Airlines plane Co-Pilot Hailemedehin Abera Tagegn.
ሁለተኛው ሰሞኑን ነገረ ስራው አያምርም ነበር የሚልና አእምሮው ለየት ያለ ነገር የሚያሳየው ‘ሺዞፍሬንያ’ እሚሉት ነገር እየጀማመረው ነበር የሚለው ነው። እህት ሁሉም ይስማልኝ በማለት በመረጃ መረቦች በተነች የሚባለውን ያነበበ ሰው ለበረራ ብቁ ነው የሚለውን ፈቃድ ሰጪም ወፈፍ ያደረገው መሆን አለበት ቢል አላጋነነም። ይሄ እብድ እየመሰለ ሲሰልል የኖረ ወያኔ ወፈፌነትን በጣም ስለተለማመደው አማኑኤል ሆስፒታልን የደህንነት ማሰልጠኛ ኮሌጅ አድርጎ ቢመለከት አይፈረድበትም ብለን መሳቅም መብታችን ነው። ቁም ነገሩ ግን የበረራውን ደህንነት ለማስጠበቅ የአብራሪዎችንምጤናና ደህንነት መከታተል ስለሚገባው ያንንም ማድረግ ባለመቻሉ ወደ ትልቅ ስህተት ራሱን እየጨመረ ነው። በዚህ ሁኔታ ምን  ያህል ወፈፌ ፓይለቶች ይኖሩ ይሆን ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል። ከሆነም ምን አይነት አስተዳደር ቢኖር ነው ጨርቅ ጥሎ የሚያሳብደው፣ ሃገር ጥሎ የሚያስኮበልለው ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው። የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ እንደሚባለው በአንድ-ለአምስት ተጋግዞ መዋሸት ይቻል ይሆናል ከዚያ መረብ ውጪ ላለነው ግን አስቂኝ ትዕይንት ነው።
እኔ አውሮፕላኑን ጠለፈ የሚለው አገላለጽ እጅግም አልተመቸኝም።  ረዳት አብራሪው ድምጼ ይሰማልኝ በማለት ማቆም የማይገባው ስፍራ ላይ አውሮፕላኑን አቆመ ለዚያውም ያለ ፍርሃትና ሽብር መደናገጥና መርበትበት ተሳፋሪውም ኮሽታ ሳይሰማ። አቅጣጫ በቀየረው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ ሰራተኞች ለተሳፋሪዎቻቸው ቡና ሻይ እያቀረቡ ምቾታቸውን እየጠበቁ ዋናው አብራሪ ጋዜጣቸውን እያነበቡ ምቾታቸው ሳይጓደል አረፉ። ተሳፋሪዎች የሆነውን ሁሉ ሳያዩ ረዳቱ አብራሪ በገመድ ወርደው ለፖሊሶች እጃቸውን ሰጡ። እንግዲህ የአእምሮ በሽተኛ እንደዚህ ከሆነ ተጋግዘን ብንታመምስ ምን ነበረበት?
ረዳት አብራሪው ሃይለመድህን አበራ ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ስለመኖሩ መጠራጠር አውቆ መጨፈን ይሆናል። በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የሀገሪቱ አስተዳደርን ገጽታ የሚያበላሽ ድርጊት ተከናውኗል። ስለምን የሃገሪቱን ገጽታ የሚያጎድፍ እንደሚባል አይገባኝም። የሀገሪቱን ገጽታ የሚያጠለሹት ጎጠኞችና አምባገነኖች ናቸው። የነርሱ አስተዳደር መበስበሱን፣ ሁሉንም ዘርፍ ማለትም ብዙሃኑን የሀገሪቱ ሕዝብ ማሳዘኑን በዚህም ምክንያት ምሬት መኖሩን ነው ይህ ወንድማችን አደባባይ ያወጣው። አዎ የአስተዳደሩን ብልሹነትና እንዳይድን ሆኖ መታመም ነው አደባባይ ያወጣው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ገጽታ ሳይሆን ዓለም የተመለከተው የአስተዳደሩን መጥፎነት ነው።
ቤተሰቦቹ ተገድደው የሚያወጧቸው መግለጫዎች ይበልጥ የሚያጋልጡት ይህ ማፍያ ቡድን እስከምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችልና በቤተሰብ ችግርና ሃዘን ውስጥ እንኳን በመግባት ሊፈጽም የሚችለውን አረመኔያዊ ድርጊት ነው። ቤን የሚሉት ለማጅ ጋዜጠኛ ወሎ ሄዶ ባላቸውን አለቆቹ ገድለው እርሱ ደግሞ በሙስሊም አክራሪዎች እንደተገደሉ ለማስመሰል ሃዘንተኛዋን ባለቤት ሌላ ፖለቲካ ሲያሰራ እንደነበረው ያለ ዜናን ማስታወስ ተገቢ ነው። ያለንበት ዘመን የራሽያ አብዮት የፈነዳበት ጊዜ አይደለም በአይነቱ በተለይም በመረጃ ቅብብሎሹ ረገድ እጅግ በጣም የተለየ ዘመን ነው። የዚያን ጊዜ ታክቲክ በመጠቀም አሁን የሚታየውን አመጽ ማፈን አይቻልም። ይልቁኑ እብዶቹ መንግስት ነኝ ባዮችና ወፈፌዎቹ ጋዜጠኛና ካድሬዎች ከአሳፋሪ ተግባር ቢታቀቡ ነው የሚሻላቸው።
ረዳት አብራሪው ሃይለመድህን አበራ ቃል ሳይተነፍስ ማለት የሚፈልገውን የተናገረ ይመስለኛል። የምቾት ህይወትን ትቶ ሙያውን ተሰናብቶ መሄዱ ጀግንነት ነው። የብዙዎችን ሰቆቃና ቁጣ ያለውን የአስተዳደር በደልና ዘረኛነት ማጋለጡ ጀግንነት ነው። ራሱን ከዚህ ጨቋኝ ስርዓት ነጻ ማውጣት ለርሱ ቀላል እጅግ በጣም ቀላል ነገር ሆኖ ሳለ በሙያው በክህሎቱ የአለምን ትኩረት የሚስብን ነገር የአንድ ሰው ሕይወት ሳያጠፋ ማስተላለፍ መቻሉ ጀግንነት ነው። ይልቁንም ደግሞ የታወከ አእምሮ ኖሮ(አዋኪውና አስቀዋሹ ምክንያት ምን እንደሆነ ይታወቃልና) በዚህ አይነት የተረጋጋ መንፈስ እንዲህ ያለ መልዕክት ማስተላለፍ መቻሉ ይበልጥ አስደናቂ ያደርገዋል። ምናልባትም በሽታ መሆኑ ቀርቶ ልዩ ስም የሚሰጠው የመንፈስ ጥንካሬ ተብሎ የሚታወስ ይሆናል።  ለወንድማችን ሃይለመድህን አበራ መልካም ጤንነትና ፍትህን እመኛለሁ። ቤተሰቡና ወዳጆቹ ተመሳሳይ የመንፈስ ጥንካሬ ያድርባቸው ዘንድም አሳስባለሁ።

ወያኔን ተሸክሞ መኖር ይብቃን!

February 23, 2014
በዳዊት መላኩ ( ከጀርመን)
የሰው ልጅ ካመረረ ቀጥሎ ምን እንደሚመጣ ማሰብ አይችልም፡፡ ለነፍሱም ፈጽሞ አይሳሳም፡፡ ወቅቱ 1998 ዓ.ም ነው፡፡ የ97 ሰባቱን ምርጫ ተከትሎ በተነሳው ብጥብጥ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረ ስሙን  ለጊዜው የማላስታውሰውን ወጣት ሁኔታ ላካፍላችሁ፡፡ በእለቱ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ረባሻ ነበር፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብጥብጡ ተዛምቱዋል፡፡ ቀደም ብሎ ተማሪዎች ወደ ክፍል እንዳይገቡ ስጋት ተፈጥሩዋል፡፡ ግቢው በፌዴራል ፖሊስ ተከቡዋል፡፡ የከተማው ወጣቶች  ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብተው ተማሪዎችን ይዘው መውጣት ያፈልጋሉ፡፡ ተማሪዎችም ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው ድምጻቸውን ማስማት እና ተቃዉሞአቸውን መግለጽ ይፈልጋሉ፡፡ በመሀል ዙሪያውን የከበበው የፌዴራል ፖሊስ በታጠቀው መሳሪያ በማስፈራራት እየተከላከለ ያገኛል፡፡ ከውጪ ወደውስጥ እንዳይገቡ ሲከላከሉ ከውስጥያ ያለው ደግሞ ወደ ውጪ እንዳይወጣ በመሀል ሆነው  ይከላከላሉ፡፡ ማሪዎች ያሳደባሉ፤ ይጮሀሉ፡፡ በዚህ መሀል በአዲሱ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ህንጻ በኩል አንድ ረዘም ያለ  መልካማ ወጣት መሳሪያ ደግነው ለግዳይ የሚጠባበቁትን ወታደሮች ከምንም ሳይቆጥር ከወደ ስላሴ ቤተክርስቲያን አቅጣጫ በከፍተኛ ፍጥነት እየሮጠ መጣ፡፡ ወታደሮች ተመለስ! ተመለስ! ትሞታለህ እያሉ ይጮሀሉ፡፡ በለው! በለው! ያባባላሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ያ ነፍሱ ፍትህ የተጠማች ወጣት ግቡ ወደ ግቢው በመምጣት ድምጹን ማስማት  በመሆኑ  የወታደሮችንም ጩኸት ሆነ የተደቀነውን መሳሪያ ከምንም አልቆጠረውም፡፡
የወጣቱን ድፍረት ላየ ሰው ሞት የሚባል ነገር ከምድር  እንደሌለው የተረዳው ይመስል ነበር፡፡ ሩጫውን ቀጠለ፡፡ መግደል የተካኑት ወታደሮችም በሁለት ጥይት አከታትለው መቱት፡፡ እንደኛው ጥይት ትክሻውን የመታው ሲሆን ሁለተኛው ጥይት ኩላሊቱን አካባቢ ነው የመታው፡፡ እንደዚህም ሁኖ ወጣቱ አሁንም እየሮጠ በሸቦ ከታጠረው የዩኒቨርሲቱው አጥር ሲደርስ አጥሩን አልፎ መግባት አልቻለም፡፡ ሽቦው እጥር ስር ወደቅ፡፡ በዚህ ጊዜ ተማሪዎች የወደቀውን ወጣት ለማንሳት ከያሉበት  ሮሩዋጡ፡፡ የሽቦውን አጥርም ፈልቅቀው ወደ ውስጥ ይዘውት ገቡ፡፡ወደያው ወደተማሪዎች ክሊኒክ ይዘውት ሄዱ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ክሊኒክ  የሚሰሩት ዶ/ር ታጀበ አለሙ እና ነርስ በላይነሽ እርዳታ ቢያደርጉለትም ማትረፍ አልቻሉም፡፡ ወጣቱ ህይወቱ አልፋለች፡፡ ግቢው ታመሰ፡፡ ለቂሶ ዋይታ እየዩ ሆነ፡፡ በመሀል የምሳ ሰሀት ስለደረሰ  የተወሰኑ ተማሪዎች ምግብ እንብላ ሲሉ ሌሎች ደግሞ እሬሳ አጋድመን መብላት የለብንም ሲሉ እንብላ የሚሉት ከላይ ትእዛዝ ተላለፎላቸው ኑሮዋል እናንተ ምን ትሰራላችሁ ለምን ዝም ብላችሁ ታያላችሁ ስለተባሉ ጉዳዩ ወደ ብሄር ጠብ ተቀይሮ  ተማሪዎች ጎራ ለይተው ድብድብ ተጀመረ፡፡ ከዚያም ግቢው ሙሉ በሙሉ በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ ለተወሰኑ ቀናት ሽንት ቤት እንኩዋን ለመውጣት የወታደሮችን ፈቃድ ተጠይቆ ነው፡፡ ከዶርም እንዳይወጣ ተከለከለ፡፡ ትምህርትም ተቁዋረጠ፡፡ ከሳምንት በላይ በዚህ መልኩ ቀጥሎ ቀስ በቀስ ተረጋጋ፡፡
እንግዲህ እንድትረዱልኝ የፈለግሁት የሰው ልጅ ትግስቱ ገበድ እንዳለው ነው፡፡ ከዚያ ገደብ በላይ ማለፍ እንደማይቻል በዚህ ወጣት ታሪክ ይነግረናል፡፡ ማናኛውም ነገር ገደብ (tolerance limit) አለው፡፡ ለምሳሌ አንድ ላስቲክ ስንስበው እስከተወሰነ ደረጃ ይለጠጣል፡፡ ከዚያ ደረጃ በኃላ ይበጠሳል፡፡ ውኃ በፈሳሽነት ደረጃ የተወሰነ ሙቀትን ወይም ቅዝቃዜን ተቁቁም ይቆያል፡፡ ከዚያ ደረጃ ሲያልፍ ወይ  ይተናል ወይ ወደ በረዶነት ይለወጣል፡፡ የአንድ ብረት ጥንካሬው የተወሰነ ሀይልን ለመቁዋቋም ነው፡፡ የሀይል መጠኑ ሲበዛ ይጣመማል ወይም ይሰበራል፡፡ የወያኔ አፈና እስከተወሰነ ደረጃ ህዝቡን ለማስጊንበስ ረድቶታል፡፡ የወያኔ የመከላከያ ሰራዊት ያለፉትን ጊዜያት በስልጣን ተደላድሎ የሀገርን ሀብት እየዘረፈ እንዲቆያ አግዞታል፡፡ ነገር ግን ዘላልም ስልጣን ላይ እንዲቆይ አያደርገውም፡፡ ማናኛውም ነገር ከገደቡ ማለፍ ስለማይችል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔን መሸከም የሚችለውን  ያክል ታክሻው እስኪጎብጥ ግፍ እና በደሉን ችሎ ተሸክሞትል፡፡ ላለፉት 23 አመታት ሲያነቋሽሹት፤ ሲገድሉት፤ ሲዘርፉት፤ ከመኖሪያው፣ ከቤቱ ፣ከስራው ሲያፈናቅሉት፤ ከሀገር ሲያስወጡት፤ በእምነት በጎሳ እየከፋፈሉ ሲያጫርሱት ብዙ ብዙ ታግሷቸዋል፡፡ አሁን  ህዝቡ መሸከም ከሚችለው በላይ ስለሆነበት ከራሱ አሽቀንጥሮ መጣል ያፈልጋል፡፡ ዛሬ አንድነት እና መኢአድ  በጠሩት ሰልፍ የታየው የህዘብ ስሜት ምን ያክል እየገነፈለ እንደሆነ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የሚነግረን ህዝቡ ምን ያልክ ለውጥ እንደሚፈልግ ነው፡፡ እንግዲህ አወዳደቁ እንዳይከፋ ቀስ ብሎ ትንሸራቶ መውረድ ከቻሉ ለወያኔ እና ለደጋፊዎች እሰየው ነው፡፡ ካለሆነ ግን ህዝቡ በግድም ቢሆን አንኮታኩቶ ጥሎ መሰባባሩ የማይቀር ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ ወያኔ ወይ በራሳቸው ጊዜ ቀስ ብለው ይውረዱ ወይ  በግድ ይወገዱ፡፡

የመከላከያ ተቋም ተግባር አገርን መጠበቅ ነዉ ወይስ አገርን መዝረፍ?

February 22, 2014
Ginbot 7 weekly editorialየአዉሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ሲቀራመቱ ባህር ተሻግረዉ በመጡ የነጭ ባዕዳን ኃይሎች መገዛትን መርጦ የአዉሮፓን ወራሪዎች በሰላም በሩን ከፍቶ ወደ አገሩ ያስገባ እንድም የአፍሪካ አገር አልነበረም፤ የኋላ ኋላ ተሸንፈዉ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ስር ቢወድቁም ሁሉም የአፍሪካ አገሮች እንደ አቅማቸዉ ከወራሪ ኃይሎች ጋር ተፋልመዋል። በአንድ ወቅት የቅርብ ጎረቤቶቻችንን ጨምሮ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች በወራሪ ኃይሎች ተሸንፈዉ የቅኝ ገዢዎች ቀንበር ጀርባቸዉ ላይ ሲጫን አገራችን ኢትዮጵያ ብቻዋን የአለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ሆና የኖረችዉ ጣሊያኖች፤ እንንግሊዞችና ፈረንሳዮች ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለይተዉ ስለወደዷት ወይም ስላከበሯት አይደለም። ይልቁንም ነፃነታችንና የግዛት አንድነታችን ተከብሮ የኖረዉ ኢትዮጵያ እናት አገሩ በጠላት ስትደፈር ከሚያይ ምትክ የሌላት ህይወቱ ብታልፍ ደስ የሚለዉ የኩሩና የጀግና ህዝብ አገር በመሆኗ ነዉ። የሚገርመዉ ይህ ኩሩና ጀግና ህዝብ ጣሊያንን የመሰለ በዘመናዊ መሳሪያ የታጀበ ኃይል ዉርደቱን ተከናንቦ ወደመጣበት እንዲመለስ ሲያስገድድ እንደ ዛሬዉ የተደራጀ ዘመናዊ የመከላከያ ሰራዊት አልነበረዉም። ዛሬ አራት ኪሎና ስድስት ኪሎ ላይ የተተከሉት ሁለቱ ታሪካዊ ሀዉልቶቻችን የሚነግሩንም ይሀንኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በዘመናዊ መልክ የተደራጀ ሠራዊት ሳይኖረዉ የጎበዝ አለቃ እየመረጠ በጣሊያን ፋሺስቶች ላይ የተጎናጸፈዉን አኩሪ ድል ነዉ።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘመናዊና የተደራጀ መከላከያ ሠራዊት ጥንስስ የተጣለዉ በዳግማዊ ሚኒልክ ዘመነ መንግስት ሲሆን እሱም ቢሆን ከአድዋ ድል በኋላ ቆይቶ የመጣ ክስተት ነዉ። በአፄ ኃ/ሥላሤና በደርግ ዘመነ መንግስት ኢትዮጵያ ለአንድ ፓርቲና ይህ ፓርቲ እወክለዋለሁ ለሚለዉ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሙያዊ ብቃት የነበረዉ፤ሙያዉን የሚያከብርና ለአገሩና ለወገኑ ታማኝ የሆነ የመከላከያ ሠራዊት ነበራት። የወያኔ ዘረኞች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ የመጀመሪያ ኢላማቸዉ አድርገዉ ካወደሟቸዉ ዋና ዋና የአገራቸን ተቋሞች ዉስጥ የመጀመሪያዉ ይሄዉ የአገርና የህዝብ ደጀን የነበረዉ ተቋም ነበር። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ የአገር መከላከያ ሠራዊት እየተባለ የሚጠራዉ ተቋም ለጎጠኞች ጥቅምና የስልጣን መራዘም የቆመ፤ በዘረኝነት የተካፋፈለ፤ ይህ ነዉ ተብሎ የሚጠቀስ ሙያዊ ብቃት የሌለዉና የወገንና የአገር ፍቅር እንዳይኖረዉ ተደርጎ የተደራጀ ሰራዊት ነዉ። ይህንን ሠራዊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሳይሆን የወያኔ ሠራዊት እያልን የምንጠራዉም በዚሁ ምክንያት ነዉ።
ዛሬ ሙሉ በሙሉ በወያኔ ዘረኞች ቁጥጥር ስር የወደቀዉ የአገር መከላከያ ተቋም የሚታማዉ በዘረኝነት፤ በሙያ ብቃት ማነስና የአንድ ፓርቲ ጥቅም አስከባሪ በመሆኑ ብቻ አይደለም፤ ተቋሙ ከእነዚህ ዋና ዋና ጉድለቶቹ በተጨማሪ በቀድሞዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ተቋም ላይ በፍጹም ያልታዩ ሌሎች ትላልቅ ጉድለቶች አሉበት። ከእነዚህ ጉድለቶች ዉስጥ አንዱ የወያኔ የመከላከያ ተቋም ህገ መንግስቱ ከሰጠዉ ኃላፊነት ዉጭ በንግድና በንብረት ይዞታ ላይ ላይ መሰማራቱ ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ ከዚህ ፀባዩ ጋር ተያይዞ በመከላከያ ሠራዊት ተቋም ዉስጥ ከላይ እስከታች የሰፈነዉ ቅጥ ያጣ ሙሰኝነት ነዉ። ዛሬ የወያኔን የመከላከያ ተቋም፤ የህወሀትን ፓርቲና ኤፎርት በሚል ምህጻረቃል የሚታወቀዉን የወያኔን የገንዝብ ማምረቻ ድርጅት ነጣጥለን ወይም አንዱን ከሌላዉ ለይተን ማየት የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።
በላፈዉ አመት ወያኔ እራሱ ያቋቋመዉ ፀረ ሙስና ኮሚሺን የገንዘብ ዝርፊያን፤የንብረት መባከንንና መዝረክረክን አስመልክቶ ለፓርላማዉ ባቀረበዉ ሪፖርት ላይ ከጠቀሳቸዉ መንግስታዊ ተቋሞች ዉስጥ ቀዳሚዉን ደረጃ የያዘዉ የመከላከያ ተቋም ነዉ። ሆኖም ፓርላማዉም ሆነ የወያኔ አገዛዝ ለዚህ ሪፖርት የሰጡት ምላሽ የመከላከያና የደህንነት ተቋሞች ከአሁን በኋላ ያሻቸዉን ያክል ገንዝብ ቢዘርፉ የሂሳብ መዝገባቸዉ “ለአገር ደህንነት” ሲባል በኦዲት ኮሚሺን አይመረመርም የሚል ምላሽ ነበር። እንግዲህ ይህ በሙሰኝነት የተጨማለቀ፤ ለህግ የማይገዛና መጠበቅና መንከባከብ የሚገባዉን የአገር ኃብትና ንብረት የሚዘርፍ ተቋም ነዉ ባለፈዉ ሳምንት “የመከላከያ ቀን” ተብሎ አመታዊ በዐል የተከበረለት።
መናገሻ ከተማችን አዲስ አበባ ዉስጥ በየቦታዉ የሚታዩትን ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች ሰርተዉ የሚያከራዩት የወር ደሞዛቸዉ ከ2500 ብር የማይበልጥ መከላከያ ሠራዊት ዉስጥ የተሰገሰጉ የወያኔ ጄኔራሎች ናቸዉ፤ኢትዮጵያ ዉስጥ ትርፋማ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ትላልቅ ሆቴሎች፤ የአገልግሎት ተቋሞችና የንግድ ድርጅቶች ከፍተዉ ቁጥር ስፍር የሌለዉ ኃብት የሚያጋብሱት የወያኔ ጄኔራሎች ናቸዉ፤ ድሃዉና የወያኔ ዘረኝነት ሰለባ የሆነዉ ኢትዮጵያ ሰራዊት ለተመድ ተልዕኮ በተሰማራባቸዉ ቦታዎች ሁሉ ተመድ የሚከፍለዉን የቀን አበል ኪሳቸዉ ዉስጥ እየከተቱ ሚሊዮነሮች የሆኑትና በየዉጭ አገሩ ዉድ መኖሪያ ቤቶችንና የንግድ ተቋሞችን የሚገዙት የወያኔ ጄኔራሎች ናቸዉ። የወያኔ መከላከያ ተቋም ጉድ በዚህ ብቻ አያበቃም፤ ይህንን ወንጀለኛ ተቋም ቃላት እየደረደሩ ለመግለጽ ከመሞከር ይልቅ በጥቅሉ ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ኃብትና ንብረት እንዳሻዉ መዝረፍ እንዲችል የኃይል ሽፋን የሚሰጥ ተቋም ነዉ ማለት የሚበቃ ይመስለናል።
ወያኔና ስር የሰደደዉ ዘረኛ ስርዐቱ ከኢትዮጵያ ምድር ላይ እስካልተነቀሉ ድረስ ወያኔ ዝርፊያዉን የወያኔ መከላከያ ተቋምም የወያኔንና የደገፊዎቹን ዝርፊያ በመሳሪያ ማጀቡ አይቆምም። የወያኔን ዝርፊያ ለማስቆምና አገራችንን ከተጋረጠባት አሳሳቢ አደጋ ለመታደግ ብቸኛዉ መንገድ ወያኔን ከሥልጣን ማስወገድ ብቻ ነዉ። ግንቦት 7 የፍትህ፤የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የጀመረዉ ህዝባዊ ትግል እንደ አገር መከላያከያ አይነቶቹ ቁልፍ የአገር ተቋሞች በሚሰሯቸዉ ስራዎች ሁሉ የአገርንና የህዝብን ጥቅም እንዲያስጠብቁ ለማድረግ ነዉ። የግንቦት 7 ትግል አላማ የመከላከያ፤ የደህንነት፤ የፖሊስና የፍትህ ተቋሞች የአንድ ፓርቲ ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያዎች መሆናቸዉ አብቅቶ የአገርና የህዝብ አለኝታ እንዲሆኑ ነዉ፤ ሆኖም ይህንን ቅዱስ አላማ ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ተግባራዊ ማድረግ ስለማይቻል ነፃነት፤ ፍትህ፤ዲሞክራሲ፤ ሠላምና እኩልነት የናፈቀዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወያኔን በፍጥነት እናስወግድ ከሚለዉ የአገር አድን አላማ ጎን እንዲሰለፍ ግንቦት 7 የትግል ጥሪዉን ያስተላልፋል።

ከ15 ሺህ ህዝብ በላይ የተሳተፈበት ሰላማዊ ሰልፍ በባህር-ዳር [ፎቶ]

February 23, 2014

Update: Watch Video

የተለያዩ መፈክር ያነገቡ ሰልፈኞች በባህር ዳር የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት አካባቢ በመገኘት ሰልፉን ሲጠባበቁ ነበር በአሁኑ ሰዓት ከ15 ሺህ የሚበልጥ ህዝብ ሰልፉን ተቀላቅሏል:: የአንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፣ የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ አበባው መሃሪ እንዲሁም የትብብር ለዴሞክራሲ ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር ኃይሉ አርአያን ጨምሮ ሰልፉን በቀዳሚነት እየመሩ ይገኛሉ::
በአማራ ክልል የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አለምነው መኮንን በአማራ ህዝብ ላይ የሰነዘሩትን ዘለፋ በመቃወም ነው የባህር ዳር ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረገው።
ድል የህዝብ ነው!! ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ከልዩነታችን በላይ ነው!!  ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል!!  ብአዴን የአማራውን ሕዝብ አፍኖ መግዛት ያቁም!! የኢሀደግ አምባገነን አገዛዝ ሰልችቶናል!! የሚሉ መፈክሮችን እያሰሙ ይገኛሉ።

የሲድኒ ኢትዮጵያዊያን የተሳካ የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ፣ አዲሱ አምባሳደር ሀፍረት ገጠማቸው

February 23, 2014
አቢይ አፈወርቅ (ሲድኒ, አውስትራልያ)
በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አረጋ ሀይሉ ትላንት (ቅዳሜ ፌብሯሪ 22 ቀን) የሲድኒ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያንን በልማት ዙሪያ ለማነጋገር የያዙት ፕሮግራም በአሳፋሪ ሁኔታ ተደመደመ።
ይህ በሜሪላንድ ሲቲ ካውንስል የተካሄደው ስብሰባ አምባሳደሩንና የስብሰባውን አስተባባሪዎች ጨምሮ በድምሩ 20 ሰዎች እንኳ ያልተገኙበት ሲሆን በርካታ ቁርጠኛ ኢትዮጵያዊያን ግን ለሰዓታት በአዳራሹ በር ላይ ቆመው ደማቅ የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ ውለዋል።  ቪዲዮ ክሊፑን ለመመልከት
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲያስፖራውን ለመከፋፈል ከዓመታት በፊት ያወጣውና በሲድኒም የአገዛዙ ወኪሎች ለረጅም ጊዜ የደከሙበት ዕቅድ ‹ውጤት አስገኝቷል› በሚል ያለአግባብ የተመኩት አምባሳደር አረጋ መላው የሲድኒ ነዋሪ እንዲገኝላቸው መወትወት የጀመሩት ከ2 ሳምንታት አስቀድሞ ነበር። ይሁንና የወገኖቻቸው ሰቆቃ እንደ የእግር እሳት የሚያንገበግባቸው የሲድኒ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን ግን ሳምንቱን ሙሉ ‹የስብሰባው አጀንዳ የዲሞክራሲ መታፈንና የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ መሆን ይገባዋል› በሚል እርስ በርስ በስልክ የጸሁፍ መልዕክቶችና በሶሺያል ሚዲያዎች ኃሳብ ሲለዋወጡ ነበር የቆዩት። በዚህም የነዋሪው የቁጣ ልክ ከፍተኛ መሆኑ ድንጋጤ ውስጥ የከተታቸው አምባሳደር አረጋ ከስብሰባው አንድ ቀን አስቀድመው ለፖሊስ በመደወል ሀሳባቸውን መቀየራቸውንና በግል አዘጋጆቹ ከሚመርጧቸው ሰዎች በቀር ማንም ወደ አዳራሹ እንዳይገባባቸው ለመጠየቅ ተገደዋል።
Ethiopians in Sydney, Australia protest
ገና በመጀመሪያ ጉዟቸው በፈጸሙት የስሌት ስህተት ለሀፍረት የተዳረጉት አዲሱ አምባሳደር በይፋ የጋበዟቸውን ሰዎች ለማየት እንኳን ባለመድፈራቸው ከስብሰባው አንድ ሰዓት ዘግይተው ወደአዳራሹ በጓሮ በር ገብተዋል። ሰልፈኛውም በሳቅና በወረፋ ተሳልቆባቸዋል።
በስሜት ንዳድ የጋሉት ኢትዮጵያዊያን ከአዳራሹ በር ላይ ቆመው በከፍተኛ ድምጽ መፈክሮችና አገራዊ መዝሙሮችን ያሰሙ ነበር። ባኳያው ደግሞ እየተንጠባጠቡ ወደ ስብሰባው በማምራት ላይ ከነበሩ አናሳ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች መሀል አንዳንዶቹ የተቃውሞውን ጥንካሬ በመመልከት ከቅርብ ርቀት ፊታቸውን እያዞሩ ሲመለሱ ታይተዋል።
Ethiopians in Sydney, Australia protest against Ethiopian government
የአገዛዙ ወኪሎች ‹ለተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ይሸነፋሉ› በሚል የገመቷቸውን ኢትዮጵያዊያን በማባበልና በመደለል ለረጅም ጊዚያት የደከሙበት ይህ ዝግጅት፤ ነባር የህወሀት ደጋፊዎችን፣ አምባሳደሩንና የዝግጅቱን አስተናባሪዎች ጨምሮ 20 የሚሞሉ ሰዎችን እንኳ ማሰባሰብ ያለመቻሉ ለኤምባሲው ሀፍረትን፣ ለተቃዋሚዎች ደግሞ እርካታን ሊያጎናጽፍ በቅቷል።
በሚያስተዛዝብ ደረጃ አብዛኞቹ ታዳሚዎች ከተመሳሳይ ብሄር የፈለቁ ቢሆኑም ተቃዋሚዎቹ ግን እየደጋገሙ “እናንተ የትግራይን ብሄር አትወክሉም!” “የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችን የአገር ፍቅርን የሚያውቁ ኩሩዎች ናቸው። እናንተ ግን ሆዳሞች ናችሁ።” ሲሏቸው ተደምጠዋል። አስገራሚ የአቋም ለውጥ አድርጋ ‹ዓይንሽ ለዓፈር› የተባለችውን አርቲስት አይናለም ተስፋዬን ጨምሮ አራት ያህል የሌላ ብሄር ተወላጆችም ወደ አዳራሹ ሲገቡ ታይተዋል።
ከስብሰባው ታዳሚዎች በቁጥር ከአራት እጥፍ በላይ የሚልቀውና አንገቱን ቀና አድርጎ በከፍተኛ የስሜት ንዳድ ድምጹን ሲያሰማ የቆየው ተቃዋሚ ከያዛቸው መፈክሮች መሀል ፦”ያለ ዲሞክራሲ ልማት የለም” “የጸረ ሽብር አዋጁ ሽብር ማራመጃ ነው።” “የመሬት መቀራመቱ ይቁም!” “በኢህአዲግ ፖሊሲ ሙሰኞች እንጂ አገር አይለማም” የሚሉና ሌሎችም ይገኙበታል። በግፍ እስር ላይ የሚገኙት ንጹሀን የህዝብ ልጆች እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም በጋለ ስሜት ሲጠቀሱ ውለዋል።
ባስመዘገቡት ውጤት እርካታ የተሰማቸው የአገዛዙ ተቃዋሚ ኢትዮጵያዊያን የዕለቱን ተልዕኳቸውን አጠናቀው ወደ የቤታቸው ከመመላሳቸው በፊት በአገራቸው ጉዳይ ከመቼውም በላይ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባቸው ተወያይተዋል። መልካም ትብብርና ወንድማዊ ስሜት ያልተለያቸው የአውስትራሊያ ፖሊሶችም ልባዊ ምስጋና የቀረበላቸው ሲሆን እነሱም በአጸፋው ሰልፈኛው ሰልፉን በፍጹም ጨዋነት በማካሄዱ ምስጋና አቅርበውለታል። ይህን የተሳካ የተቃውሞ ሰልፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚያኮራ ቅንጅት ያስተናበሩት የሰልፉ አዘጋጆችም ተገቢው አክብሮት ተችሯቸዋል።